Friday, February 27, 2015

አድዋ-የጥቁር ህዝቦች ኩራት

ዝክረ ዓድዋ  (የዓድዋው ሰማዕት! የአምባላጌው ጀግና!! የጦር አበጋዙ ፊታውራሪ ገበየሁ አባ ጎራ)
የንጉሰ ነገስቱ የመሀል ጦር አዛዥ ፊታውራሪ ገበየሁ ከጣልያኖች ጋር በተደረገው በሁሉም ጦርነት የተመሰከረላቸው ጀግና ነበሩ። የአምባላጌውን ምሽግ በመስበር በጣልያን ላይ የመጀመሪያውን የድል ደወል ያሰሙት እና ዋናው የድሉ ባለቤት እርሳቸው ነበሩ። በዚህም ምክንያት በወቅቱ የፈረንሳይ ጋዜጦች “የአምባላጌው የኢትዮጵያ ጀግና” በማለት እንዳወደሷቸው ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ ፅፈዋል። የመቀሌውንም ጦርነት በደንብ ተካፍለው በጀግንነት ሲዋጉ እጃቸውን የቆሰሉ ሲሆን ከጦርነቱ በፊትም ራስ መኮነን የዕርቅ ነገር በሚነጋገሩበት ጊዜ ገበየሁ እየተዋጉ ስለ አስቸገሩ እንደ አምባላጌው እንዳይዋጉ አስረዋቸው ሳለ በኋላ ግን ላይዋጉ አስምለው አስለቀቋቸው።
በኢትዮጵያም ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ከሁሉም የላቀው የአድዋ ጦርነት የተጀመረው በየካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ከማለዳው ላይ ነበር።
ውጊያው ከጧቱ 11፡30 ላይ በአራት ጀኔራሎች የሚመራው የጠላት ጦር በፊታውራሪ ገበየሁ፣ በዋግሹም ጓንጉል፣ በራስ ሚካዔል እና በራሥ መንገሻ ጦር ላይ በሰነዘረው ጥቃት ተከፈተ። ፊታውራሪ ገበየሁ በዚህ ጦርነት ፊት ለፊት የገጠሙት በእንዳ ኪዳነ ምህረት በኩል የመጣውን እና በጀኔራል አልቤርቶኒ የሚመራውን የጠላት ጦር ነበረ።
 በጦርነቱ ፊታውራሪ ገበየሁ ከሠራዊታቸው በመለየት ጎራዴያቸውን መዘው በዋናው የትግል አውድማ፣ በተፋፋመ እና የቀለጠ እሳት ውጊያ ላይ ተወርውረው ገቡ። ዘለው እንደገቡም ከጀግናው ጓደኛቸው ከቀኝ አዝማች ታፈሠ ጋር እየፎከሩ የጠላትን አንገት በጎራዴ ሲቆርጡ እና ሲገነድሱት ቆይተው ከርቀት በተተኮሰ ጥይት ተመትተው ወደቁ። የገበየሁ መሞት ለጣልያን ጦር የድል በርን የከፈተ ስለመሰለው ጀኔራል አልቤርቶኒ ደስ ብሎት “ወደ ፊት! ወደ ፊት!” የሚል መልዕክት በየግንባሩ ያስተላልፍ ነበር። ከዚህ የምንረዳው ጀኔራል አልቤርቶኒ ፊታውራሪ ገበየሁ ማን እንደሆኑ እና ጀግንነታቸውን ያውቅ ነበር ማለት ነው። ገበየሁ ከመሞታቸው በፊትም እንዲህ ተገጥሞላቸው ነበር
የአድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው፥
ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው፥
ሥለ ገበየሁ አሟሟት በመማረኩ ምክንያት አዲስ አበባ የመጣው ዠዋቫኒ ቴዶኒ የሚባለው የጠላት የጦር መኮነን በፃፈው ማስታወሻ ላይ እንደዚህ ይላል “ . . . . . በቢያንኪኒና በማዘቶ በሚመሩት መድፎች እየተመቱ ኢትዮጵያኑ ወደኋላ ሲያፈገፍጉ አይቶ ‘ፈሪ ሁሉ እንዴት ታፈገፍጋላችሁ የአምባላጌው ጀግና ፊታውራሪ ገበየሁ እንዴት እንደምሞት ለንጉሱ ሄዳችሁ ንገሩ’ ብሎ እየጮኸ እንደ አንበሳ ተወርውሮ በሚዘንበው የመድፍ ጥይት መካከል ገባ። እርሱን ሲያይ ሁሉም እየሮጠ ተከትሎት ገባና ከመድፈኞቹ ጋር ተጨፋጭፎ እና ገድሎ መድፈኞቹን ማረከ። በዚያን ጊዜ በመትረየሥ ተመትቶ ወደቀ። የገበየሁ ሬሳ ከወደቀበት ቦታ የኛወቹም ጀግኖች ሬሳ አብሮ በመውደቅ የሱን ሬሳ አከበረው።”
በማለት ይቀጥልና ምርኮኛ በመሆን ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በንጉሰ ነገስቱ ሰፈር ሳለ በአይኑ እንዳየው ሥለ ፊታውራሪ ገበየሁ ሕዝቡ በሙሉ ያለቅስ እንደነበረ ከዕለታት አንድ ቀን ደግሞ ከሞት የተረፈው ሁሉም ተዋጊ በየአለቃው በየአለቃው ተሰልፎ ተሰልፎ በንጉሠ ነገስቱ ፊት ሲያልፍ የፊታውራሪ ገበየሁ ወጣት ልጅ የአባቱን የተጫነ በቅሎ ይዞ ሲያልፍ አፄ ምኒልክ አይተውት ስቅስቅ ብለው ማልቀሳቸውን ያረጋግጣል።

ድል መሰዋዕትነትን ይጠይቃል በዚሁ ጦርነት እነ ደጅ አዝማች ጫጫን፣ ቀኝ አዝማች ታፈሰን፣ ፊታውራሪ ዳምጠውን ጨምሮ ሌሎች ጥቂት ከፍተኛ መኮንኖች እና አዝማቾች እንዲሁም ብዙ ተራ ተዋጊወች ወድቀዋል። በነዚህ ጀግኖች ሞት መላው ሠራዊቱ ነበረ ያዘነው ። ይህንኑ የሀዘን ስሜት በግጥም ተገልጧል።
ያ ጎራው ገበየሁ ምን አሉ ምን አሉ፥
ያ ትንታግ ታፈሰ ምን አሉ ምን አሉ፥
እነ ደጃች ጫጫ ምን አሉ ምን አሉ፥
ተማምለው ነበር ከጦሩ ሊገቡ፥
አገሩን አቅንተው አድዋ ላይ ቀሩ፥
ሌላ ባለ ቅኔ ደግሞ እንዲህ ብሏል።
አዝማቹ ገበየሁ ነጭን ሲጋግር፥
ታፈሰ እያረደ ስጋውን ሲመትር፥
መትረው ጋግረው ሄዱ ሳያዩ ግብር፥
የጦር አበጋዙ ፊታውራሪ ገበየሁ የአድዋ ዕለት ወደር በሌለው ጀግንነት ለሀገራቸው ነፃነት ሕይወታቸውን በመስጠት ከፍተኛ ድል እንዲመዘገብ ያደረጉ የቁርጥ ቀን ልጅ ናቸው። በሠሩት የጀግንነት ተግባር እስከ ዛሬ ስማቸው ሥለ አድዋ በተነሳ ቁጥር ቀድሞ ይጠራል። ይልቁንም ጠላት የአድዋን ታሪክ በፃፈው መፅሀፍ ጀግንነታቸውን እና አይበገሬነታቸውን በሚገባ ይተርከዋል። ሻቃ ገበየሁ የሰናድር ያዥዎች ሹም እንደነበሩ እና በውስጣቸው የሚያዙት ጦር ቁጥሩ 3000 እንደነበረ በጣልያኖች መዝገብ ተፅፎ ይገኛል። ሲያስተዳድሩት የነበረው ግዛት አንድ ጊዜ አሣግርትን ሌላ ጊዜ ደግሞ የጉራጌን አውራጃ ነው።
የገበየሁን የፊታውራሪነት ማዕረግ መነሻ ተደርጎ ከዚያ በኋላ የጦር መሪ ሆኖ የሚሾመው ሰው ምንም ማዕረጉ ከፍ ያለ ቢሆን ፊታውራሪ እንዲባል ተወሠነ። ከአድዋ በኋላ ንጉሰ ነገስቱ ከጦራቸው ጋር ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሱ የፊታውራሪ ገበየሁን የጦር አዛዥነት ቦታ በሌላ ሰው ለመተካት ወሰኑ። ይህን ቁልፍ ስልጣን ብዙ የጦር አለቆች በተለይ እነ ሊቀ መኳስ (በኋላ ራስ) አባተ ቧ ያለው ሲመኙ ቢቆዩም ንጉሠ ነገስቱ አፄ ምኒልክ የራስ ወርቅ ጨምረው በመስጠት ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላን) በአዛዥነት ሾሙ።
©ብሩክ ሲሳይ (Abegaz Zė Wollo)
ምንጮች፡ ሥርገወ ሐብለ ሥላሴ፣ ራይሞንድ ጆናሥ እና ተክለፃዲቅ መኩሪያ

No comments:

Post a Comment