Tuesday, April 2, 2019

ዶ/ር አብይ አህመድ-ቲሸርት አልባው መሪ

እንደምንድን አላችሁ፡፡ አለበለዚያስ እንዴት ናችሁ፡፡ ሰሞኑን ነገሩ ሁሉ የጅብ እርሻ ሲሆንብኝ ከራሴ ጋር ለአንድ ሳምንት ሱባኤ ገባሁ፡፡ ከፌስቡክ ጡሉላትም ጦምሁ፡፡ ሱባኤ ገብቼ አንድ ሀሳብ ይጄ መጣሁ፡፡ ‹‹አንድ ጉዳይ-በአንድ ፀሐይ›› የሚል! የሀገሬ ባለሃገር ‹‹ይችንማ በአንድ ፀሐይ እጨርሳታለሁ፣ ቢያቅተኝ እንኳን እስከ ፀሐይ ግባት አፈፅማታለሁ›› ከሚለው የተወሰደ ነው፡፡ ነገሮቹን በየደቂቃው መስቀል ማውረዱ፣ መለጠፍ ማጋራቱ ብዙ የሚያስቀጥለን አልመሰለኝም፡፡ የእስክንድርን ቃል ልዋስና ‹‹መከራችን ገና አላለቀም››፡፡ ላላለቀ መከራ ደግሞ ጅብ ተከትሎ መጮህ ብቻ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ነገ ላለመጮህ ሰከን ብሎ በነገሮች ላይ አድምቶ መወያየት፣ መረጃ መለዋወጥ፣ ነገን ማደራጀት፣ አዳዲስ ሃሳቦች ማፍለቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በኋላ ሀሳቤን ከሚጋሩ የተወሰኑ የፌስቡክ ወንድምና አህቶቼ ጋር በሰከነ መልክ በአንድ ቀን አንድ ጉዳይ ላይ የሰከነ ውይይት አደርጋለሁ፡፡ ያለኝን አካፍላለሁ፡፡ ከብዙዎች ብዙ እማራለሁ፡፡ መረጃዎችን አሰባስባለሁ፡፡ በጨዋ ወግ እንድንወያይ አለምናለሁ፡

ዛሬ ያነሳሁት ርዕሰ ጉዳይ ‹‹ ከመጋቢት-እስከ-መጋቢት›› እንዲሉ የዶ/ር አብይ የአንድ አመት የስልጣን ጊዜ ላይ እንወያያለን፡፡
‹‹ዶ/ር አብይ አህመድ-ቲሸርት አልባው መሪ›› በሚል ርዕስ መነሻነት የሆነ ነገር ልበል፡፡ አይዟችሁ የዶ/ር አብይን ውስጥ እንጂ አለባበስ ለማየት አልሞክርም፡፡ በወንጌል ‹‹ እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል…›› የሚለውን ቃል ስለማውቅ እራሴን ለሸንጎ ዱላና ገጀራ ላለመጋበዝ ሰውን በአለባበሱ አልተችም፡፡