ማሪያና ትንሽ ሞቅ ብሏታል፡፡ ከለበሰችው ታኮ ጫማ ጋር ተዳምሮ ‹‹ደርደር…ደርደር›› ትላለች፡፡ ጠጋ ብዬ በ እጄ ጨበጥኋት፡፡ እጇ ያቃጥላል፡፡ የ አስፓልቱን ዳር ይዘን ባጃጅ መጠበቅ ጀመርን፡፡
ዝምታችንን ለመስበር …ይቅርታ ቅድም አስቀየምሁሽ አይደል አልኳት፡፡
‹‹ችግር የለም በ አንተ አልፈርድም፣ አልፏል እርሳው›› አለችኝ….ዝቅ ብላ መሬት መሬት እያየች፡፡
ማሪያና ወደ የት እንደምንሄድ እንኳን አልጠየቀችኝም፡፡ የምወስዳት ወደ ገነት እንዳልሆነ ልቧ ቢያውቅም፣ ከ ሲኦል ወደ ባሰ ገሃነም ይሆን ብላ እንኳ አትጠይቅም….‹‹የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም›› ብላ ይሆን? አላውም ፣ ምን እያሰበች እንደሆነ ማወቅ ይከብዳል፡፡