Monday, May 16, 2016

"ከ ምስራቅ ሰማይ ስር_ክፍል 2..."

(አወዳይ፣ ባቢሌ፣ ካራማራ....)
መኪናችን ፊት ላይ የሚል ድምፅ ከምናቤ መለሰኝ፡፡ ሹፌራችን ተደናግጧል፡፡ በዚህ ቅፅበት አንድ ሚዳቋ መኪናችን በቀኝ በኩል ወጣ ስትሮጥ አየሁ፡፡ ሹፌራችን አንድ ጫት በልታ የመረቀነች ሚዳቋ ጋር ተጋጭቶ ነበር፡፡ እንደ እርግቧ እስከመጨረሻው አላሸለበችም፡፡ ህመሟን ዋጥ አድርጋ ወደ ጫካው ተምዘግዝጋ ገባች(ደግነቱ የዱር እንስሳ ጥበቃ በአካባቢያችን አልነበረም)፡፡ የሹፌሩን አነዳድ ሳየው የመረቀነ ይመስለኛል፡፡ ጫት ባይቅምም ጥብሷን የበላናት ፍየል በጫት ያደገች ስለሆነች በዚያ በኩል ደርሶታል፡፡ አሰበ እስከ ሀረር ድረስ በምርቃና አስፓልት ላይ እየዘለሉ የሚገቡ ፍየሎችንና ሰዎችን ማዬት የተለመደ ነው፡፡ ቀስ ብለህ ንዳ ልለው ብዬ መልሸ ዋጥሁት፡፡ በኋላ ግን  ዓይን ተነጋግረን አስተውሎ እንዲነዳ ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር አዋጠን ለገስነው፡፡

Saturday, May 7, 2016

"ከ ምስራቅ ሰማይ ስር_ክፍል 1…"

ሰኞ ጥዋት 12 ሰዓት-ከፋሲካ ማግስት፡፡ ጦር ሃይሎችና ወይራ ሰፈር የተምታታበት ሹፌር እንደምንም ከያለንበት ለቃቅሞ ከጥዋቱ አንድ ሰዓት አዲስ አበባን የኋሊት ትቶ ወደ ወደ ምስራቅ ተምዘገዘገ፡፡ ከዚያም የፍጥነት መንገዱን 120 ረግጦ መሪውን ወደ ምስራቅ ወደረ፡፡ ናዝሬትን በግራ አይናችን ሾፈናት በፈጣን መንገዱ በቀኝ በኩል አለፍናት፡፡ የወንጂ ሸንኮራ አገዳ ማሳ ከሩቅ ለዓይን ያሳሳል፡፡ ለአፍታ አቁመን መተሃራ ከተማ ቡና ቀመስን፡፡ የከረዩዎች ሰፈር በደራሽ ዝናብ በመጣ ጎርፍ ተጥለቅልቋል፡፡ በጥዋቱ የደነበረው ሹፌራችን አዋሽ መዳረሻ አንዲት ምስኪን እርግብ እስከወዲያኛው አሰናበተ፡፡
ከሜጫ ታራሮች ተነስቶ በዝምታ ወደ ምስራቅ የሚያዘግመውን የአዋሽ ወንዝ በዘመዶቻችን ቻይናዎች በተሰራው አዲስ ድልድይ ቆርጠነው አለፍን፡፡ አፍታ የሎሬት ፀጋዬ /መድህንን አዋሽ የተሰኘ ግጥም በውስጤ ማነብነብ ጀመርሁ፡፡
"አስከመቼ ይሆን አዋሽ? 
አዋሽ
የሜጫ ስር ፍሳሽ
አዋሽ ህመምህ ምንድን ነው?
ህመምህስ አንተስ ምንድን ነህ
?
...................