Monday, July 13, 2015

“ጠብሰው አንገረገቡኝ”








(ከአባቴ ተረቶች-፩)፡ ተረት ተረት...
በአንድ ወቅት አንድ ባልና ሚስት አንዲት ትንሽ የገጠር መንደር ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡ ባል ሁልጊዜም ራቅ ካለ ቦታ ስንቅ ቋጥሮ፣ ውሃ በኮዳ አንጠልጥሎ ጥዋት ለእርሻ የወጣ ማታ ይመለሳል፡፡ሚስት ከቤቱ ስራ በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ ባልንም በጉልጓሎና በአረም ታግዛለች፡፡ ባል ብዙ ጊዜ  በስራና በመንገዱ እርቀት ደክሞት ይመጣል፡፡ በዚህም ምክንያት የወንድነት ስራውን መዘንጋት ጀመረ፡፡ በዚህ ክፍተት ስሜቷን ለባል መናገር ያፈረች ሚስት ቤት ለቤት ሲያውደለድል የሚውል አንድ ወስላታ የሰፈር ሰው አሽኮረመመችና ወሸመች (ጠበሰች)፡፡ ውሽምየ የባልን ወደ ስራ መሄድ ሰልሎ ቤት ይመጣና ሲያስደግስ ይውላል፡፡ የልቧንም አድርሷት ይሄዳል፡፡ ምስኪን ባል ከውሽምየ የተረፈውን ቀማምሶ እንደለመደበት ድብን ብሎ ይተኛል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሚስት ለባል ያላት ፍቅር እየቀነሰና የሚዘጋጅለት ምግብም በአይነትና በመጠን እየወረደ ሲመጣ ባልዬም መጠርጠር ጀመረ፡፡ ጎረቤት መጠየቅ አልፈለገም፡፡ እራሱ አንድ ቀን በአሳቻ ለመያዝ አሰበ፡፡

በዚህ መሃል አንድ ቀን ምሽት አካባቢ ከእርሻ እንደተመለሰ አንድ የመንደሩ ሰው አልፎ ሲሄድ ሰላምታ ካቀረበለት በኋላ አንድ ጥያቄ እንዲህ ሲል ጠየቀው፡፡ ቀን በዚህ በአንተ ቤት አካባቢ የእኛ አለሌ አህያ መጦ ነበር ብለውኝ፤ አላየህም? ኧረ እኔስ አላየሁም እርሻ ውዬ አሁን ነው የመጣሁ ብሎ መለሰ፡፡ ባል ፈሊጣዊ ንግግሩ ቶሎ አልገባውም፡፡ (አለሌ አህያ ስራ የማይሰራ ፣ ምርጥ ምግብ እየተቀለበ ብቻ ከፈረስ ጋር ተራክቦ ስጋ በመፈፀም በቅሎ ለመውለድ የሚያገለግል የአህያ አይነት (ዝርያ) ነው፡፡ ሹገር ማሚ፣ ሹገር ዳዲ ምናምን እንደምትሉት አይነት፡፡ አለሌ አህያ በብዙ የሰው ልመና ነው ከፈረስ ጋር የሚገናኘው፤ “አትለመን እንደ በቅሎ አባት”  እንዲሉ)፡፡ ባል ነገሩ በደንብ ገባው፡፡ የሚስቱ ውሽማ በሰፈሩ ሰዎች ዘንድ አለሌው እየተባለ ሲታማ ስለሰማ ቀን ከአንተ ቤት ነበረ ብሎ በፈሊጥ እንደነገረው ገባው፡፡ ቀድሞውንም ጠርጥሮ የነበረው ባል እውነቱን ለማረጋገጥ አንድ ቀን መመላሻ ሰዓቱ ሳይደርስ ከተለመደው ሰዓት ወጭ ከተፍ አለ፡፡ ገና ወደ ቤቱ  ሲጠጋ የጥሩ ምግብ መዓዛ አወደው፡፡ ቀጥሎም በሁለት ሰዎች መካከል የሚደረግ የለሆሳስ ሁካታ ሰማ፡፡ ባልም እህ እህ… ብሎ ወደ ቤቱ ዘው ብሎ ሲገባ አንድ ሰው ውልብ ብሎ ወደ ውስጠኛው የቤቱ ክፍል (ማጀት) ሮጦ ሲገባ ታየው፡፡ (ማጀት፡ በገጠር አካባቢ ሴቶች ብቻ የሚገቡበትና ምግብ ነክ ነገሮች የሚቀመጡበት የቤቱ የውስጠኛ ክፍል ነው፡፡ ባል ከሚስቱ ጋር ተጣልቶ ለመደባደብ ካሰበ ሚስት ቶሎ ብላ ወደ ማጀት ትገባለች፣ በባህሉ ወንድ ልጅ ማጄት ስለማይገባ እስክትወጣ ይጠብቃል እንጂ ገብቶ አይደባደብም፡፡ ሴቶችም የወንዶች ንዴት እስኪያልፍ ማጀትን በምሽግነት ይጠቀሙበታል፡፡ ከተማ የሴትም የወንድም ማጀት የለም፡፡ምሽግ አልባ ከተማ! ጎታ አልባ ከተማ!) ሚስት የባልን መምጣት ስታይ ያለድሮዋ ተንተባተበች፡፡ ለምን መጣህ ብላ በጥያቄ ወጠረችው፡፡ ባል በተረጋጋ መንፈስ እርሻ በቀን መጨረሱን አስረዳት፡፡ የእርሻ መሳሪያዎቹን ካስቀመጠ በኋላ፤ በይ ተዘጋጅ ስጋ ስላማረኝ ግልገል ላርድ ነው ብሎ ከጓሮ አንድ ትንሽ ግልገል ይዞ መጣ፡፡ እንደነገሩ ጠብሰውም ጥሬውንም መብላት ጀመሩ፡፡ በዚህ መሃል ውሽምየ ማጄት ውስጥ ካለው አንድ ትልቅ የእህል ጎታ (ጎተራ) ውስጥ ተደብቆ እየተቁለጨለጨ ነበር፡፡ ሚስት ውሽማዋ አሳዘናት፡፡ ስጋ ለመስጠት ምክንያት ፈለገች፡፡ አንድ ምክንያት አገኘች፡፡ ቆሌውም እንደኛ ያምረዋል እኮ ብላ የተዘለዘለ ቀይ ስጋ ወስዳ ወደ ጎታው ውስጥ ጨመረች፡፡ (ቆሌ ማለት በባህሉ ሰዎችን የሚጎዳም የሚያድንም እንደ አምላክ የሚቆጠር ባዕድ አምልኮ ነው፡፡)  ባል ውሽምየ የት እንዳለ በጨረፍታ ተመለከተ፡፡ ነቄ ያለው ባልም “ስጋውንስ ሰጠሽው በምን ጠብሶ ይብላው” ብሎ ከምድጃው ያለውን ፍም እሳት በገል አፍሶ ወደ ጎታው ውስጥ ወስዶ ደፋው፡፡ ውሽምዬ እሳቱን እንደምንም አራግፎ ወደጎን ካደረገው በኋላ የተሰጠውን ስጋ መብላት ቀጠለ፡፡ የድብብቆሽ ጨዋታውን ሚስት ቀጠለች፡፡ የልብ አድራሽ ውሽምየ በሳት ሲበላ ዝም ብላ ማየት አንጀቷ አልቻለም፡፡ ቶሎ ቆፍጠን ብላ “ውሃም ይጠማዋል እኮ” ብላ እሳቱን ለማጥፋት በማሰብ በውሽምየ ላይ ውሃ ደፋችበት፡፡ ይሄን ጊዜ ትንፋሹን አፍኖ የቆየው ውሽምየ መረረውና እንዲህ ብሎ ጮኸ ፤“እውይ …..እውይ ኧረ ጠብሰው አንገረገቡኝ” አለ ይባላል፡፡ ተረቴን መልሱ፣ አፌን በነገር…

አሁን እኛን ምን ጠብሶ ያላንገረገበን አለ፡፡ ቤት ኪራይ ሲጠብሰን፣ ታክሲ ያንገረግበናል፡፡ መንግስት ሲጠብሰን፣ ኑሮ ያንገረግበናል፡፡ ባል ሲጠብሰን፣ የመስሪያ ቤት አለቃችን ያንገረግበናል፡፡ ሚስታችን (እጮኛችን) ስጠብሰን፣ ቤተሰብ ያንገረግበናል፡፡ ቀን አሰሪዎቻችን ሲጠብሱን ውለው፣ ማታ ቤት አከራዮቻችን ያንገረግቡናል፡፡ የት/ቤት ክፍያ ሲጠብሰን፣ የልጆች ልብስና ደብተር ያንገረግበናል፡፡ ፖለቲካ ሲጠብሰን፣ ትምህርት ያንገረግበናል፡፡ የቢሮ ስራ ሲጠብሰን፣ የቤት ስራ ያንገረግበናል፡፡ ታክስ ሲጠብሰን፣ ቫት ያንገረግበናል፡፡ የአገር ፍቅር ሲጠብሰን፣ ስደት ያንገረግበናል፡፡ ድህነት ሲጠብሰን፣ ደህንነት ያንገረግበናል፡፡ መጠበስ…………..መንገርገብ………………መጠበስ…………..መንገርገብ………………ኢጪ አሁንስ በዛ አለች…….ማናት እሱ….፡፡ ለማንኛውም እንደ ውሽምየ ስጋ እየበላችሁ ምትጠበሱና ምትንገረገቡ አታማሩ!

No comments:

Post a Comment