Showing posts with label የጉዞ ማስታወሻ (Journey’s log). Show all posts
Showing posts with label የጉዞ ማስታወሻ (Journey’s log). Show all posts

Monday, February 20, 2017

ከ ቢሾፍቱ ሐይቅ አፋፍ ላይ

(ከ ፕሮፌሰሩ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ)

ቢሾፍቱ ነፍስን የሚገዙ ትንንሽ ሀይቆችን በተፈጥሮ የተቸረች ምርጥ ከተማ ናት፡፡ በተደጋጋሚ ጎብኝቻታለሁ፡፡ ግን አልጠግባትም፡፡ ሐይቆቿ ነፍሴን ይገዙታል፡፡ ከ እራሴ ጋር እንዳወራ እድል ይሰጡኛል፡፡ ከ ዓለም ጫጫታ ወጥቼ ከ ማዕበሉ ጉዞ ጋር ነፍሴን አስማምቼ በምናብ እንድመጥቅ፣ ከ ሀሳቤ ህመሜ ለ አፍታም ቢሆን እንድላቀቅ ይረዱኛል፡፡ ሐይቅ እወዳለሁ፡፡ ጣና፣ ደብረዘይት፣ ዝዋይ፣ ሐዋሳ፣ ዘንገና፣ አለማያ……በተጋጋሚ ባያቸውም አልጠግባቸውም፡፡ ሁሌም ከጉያቸው ቁጭ ብዬ የሚተነፍሱትን አየር ወደ ውስጤ መማግ ያረካኛል፡፡ ንፁህ አየራቸውን ስስብ፣ አዲስ ተስፋና አዲስ ህይወት ይታየኛል፡፡ ከ ጀርባዬ ያለ ሸክም የተራገፈ ያክል ነፃነት ይሰማኛል፡፡ ጥሎብኝ ሐይቅ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮን አደንቃለሁ፡፡
ከ ቢሾፍቱ ፈርጦች ውስጥ በ ርዕሰ ከተማዋ ስም የተሰየመችው ቢሾፍቱ ሐይቅ አፋፍ ላይ ቁጭ ብዬ ከማዕበሉ ጋር በመጫወት ላይ ሳለሁ እርዳታዬን ፈልጎ አንድ አሮጌ ፈረንጂ ወደ ተቀመጥሁበት ወንበር መጣ፡፡ (እዚህ ጋ ያዝ ላድርገውና ስለ ቢሾፍቱ ሐይቅ ትንሽ ልበል፡፡)

Thursday, September 29, 2016

"ትንሽ ስጋ ይዞ ወደ በሬ ጠጋ…"

                                           (የሌቦች ጥበብ)
የሆነ ቦታ ነኝ-ከ ኦሮሚያ ሰማይ ስር፡፡ ትዕቢት የሚባል ምግብ 1-5 ተደራጅተን እየበላን ነው፡፡ ……(ለምን ትዕቢት የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ግን የሚያውቅ የለም……ምን አልባት ይህን ምግብ የፈለሰፈው “ትዕቢት” የሚባል ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ ምን አልባትም “ትእቢተኛ” ሰው ሊሆን ይችላል፡፡) ከመሃከላችን በቅርቡ የተሾመ የአንድ ትልቅ ተቋም ሀላፊ አለ፡፡ በተቋሙ ስለነበረው ስር የሰደደ የሙስና መረብ ማውራት ጀመረ፡፡ መረቡን ለመበጠስ እየሞከረ እንደሆነም ነገረን፡፡….ግን ብዙ ውሾች እየጮሁ እንዳስቸገሩትም ነገረን፡፡ …..የትኞቹ ውሾች? ለምን ጮሁ? ብለን ጠየቅነው፡፡
 “ነገር በምሳሌ ጠጅ በብርሌ”…… እንዲሉ በምሳሌ ሊያስረዳን…… “ነገሩ አንዲህ ነው” ሲል ጀመረ፡ 
 “……..አንድ የጥንት የበሬ ሌቦች ጥበብ አለ፡፡ ሌቦቹ በሌሊት ከመንጋው መሃል በሬዎችን ለይተው ለማውጣት ሲሄዱ ከ ቀራተኛው በ ከፋ መልኩ ፈተና የሚሆኑባቸው ውሾች ናቸው፡፡ ስለዚህ የእነሱን ጩኸትና ልፊያ ለማለፍ ሲሉ ትንሽ ቁርጥራጭ  ስጋ ለውሾች ይዘው ይሄዳሉ፡፡ መጮህ ሲጀምሩ ትንሽ ስጋ ጣል ያደርጉላቸዋል፡፡ አሁንም ሲጮሁ ትንሽ ስጋ ጣል ያደርጉላቸዋል፡፡ አንደኛው ሌባ ውሾችን ሲያታልል አንደኛው በሬውን ይፈታል፡፡ ውሾችም በተደጋጋሚ ቁርጥራጭ ስጋ የሰጣቸውን ሰው እየተላመዱ ይሄዱና መጮህ ያቆማሉ፡፡ በቁርጥራጭ ስጋ ልሳናቸው ተዘግቶ የ ጌታቸውን በሬ ከመንጋው ለይተው ይዘው ሲሄዱ ዝም ይላሉ፡፡ በትንሽ ስጋ ብዙ ስጋ የያዘውን በሬ አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡ አንድ ቀን ጌታቸው ይህን በሬ አርዶ ከዚህ በላይ ስጋ እንደሚያበላቸው ለ አፍታ ማሰብ አይችሉም፡፡ ጊዜያዊ ጉምጅታው በ አደራነት የሚጠብቁትን ታላቁን በሬ አሳልፈው እንዲሰጡ ያርጋቸዋል፡፡ ከዚህም አልፎ ሌባውን እንደጌታቸው ይቀርቡታል፡፡ …..” ሲል አስረዳን፡፡

Monday, May 16, 2016

"ከ ምስራቅ ሰማይ ስር_ክፍል 2..."

(አወዳይ፣ ባቢሌ፣ ካራማራ....)
መኪናችን ፊት ላይ የሚል ድምፅ ከምናቤ መለሰኝ፡፡ ሹፌራችን ተደናግጧል፡፡ በዚህ ቅፅበት አንድ ሚዳቋ መኪናችን በቀኝ በኩል ወጣ ስትሮጥ አየሁ፡፡ ሹፌራችን አንድ ጫት በልታ የመረቀነች ሚዳቋ ጋር ተጋጭቶ ነበር፡፡ እንደ እርግቧ እስከመጨረሻው አላሸለበችም፡፡ ህመሟን ዋጥ አድርጋ ወደ ጫካው ተምዘግዝጋ ገባች(ደግነቱ የዱር እንስሳ ጥበቃ በአካባቢያችን አልነበረም)፡፡ የሹፌሩን አነዳድ ሳየው የመረቀነ ይመስለኛል፡፡ ጫት ባይቅምም ጥብሷን የበላናት ፍየል በጫት ያደገች ስለሆነች በዚያ በኩል ደርሶታል፡፡ አሰበ እስከ ሀረር ድረስ በምርቃና አስፓልት ላይ እየዘለሉ የሚገቡ ፍየሎችንና ሰዎችን ማዬት የተለመደ ነው፡፡ ቀስ ብለህ ንዳ ልለው ብዬ መልሸ ዋጥሁት፡፡ በኋላ ግን  ዓይን ተነጋግረን አስተውሎ እንዲነዳ ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር አዋጠን ለገስነው፡፡

Saturday, May 7, 2016

"ከ ምስራቅ ሰማይ ስር_ክፍል 1…"

ሰኞ ጥዋት 12 ሰዓት-ከፋሲካ ማግስት፡፡ ጦር ሃይሎችና ወይራ ሰፈር የተምታታበት ሹፌር እንደምንም ከያለንበት ለቃቅሞ ከጥዋቱ አንድ ሰዓት አዲስ አበባን የኋሊት ትቶ ወደ ወደ ምስራቅ ተምዘገዘገ፡፡ ከዚያም የፍጥነት መንገዱን 120 ረግጦ መሪውን ወደ ምስራቅ ወደረ፡፡ ናዝሬትን በግራ አይናችን ሾፈናት በፈጣን መንገዱ በቀኝ በኩል አለፍናት፡፡ የወንጂ ሸንኮራ አገዳ ማሳ ከሩቅ ለዓይን ያሳሳል፡፡ ለአፍታ አቁመን መተሃራ ከተማ ቡና ቀመስን፡፡ የከረዩዎች ሰፈር በደራሽ ዝናብ በመጣ ጎርፍ ተጥለቅልቋል፡፡ በጥዋቱ የደነበረው ሹፌራችን አዋሽ መዳረሻ አንዲት ምስኪን እርግብ እስከወዲያኛው አሰናበተ፡፡
ከሜጫ ታራሮች ተነስቶ በዝምታ ወደ ምስራቅ የሚያዘግመውን የአዋሽ ወንዝ በዘመዶቻችን ቻይናዎች በተሰራው አዲስ ድልድይ ቆርጠነው አለፍን፡፡ አፍታ የሎሬት ፀጋዬ /መድህንን አዋሽ የተሰኘ ግጥም በውስጤ ማነብነብ ጀመርሁ፡፡
"አስከመቼ ይሆን አዋሽ? 
አዋሽ
የሜጫ ስር ፍሳሽ
አዋሽ ህመምህ ምንድን ነው?
ህመምህስ አንተስ ምንድን ነህ
?
...................