Tuesday, August 3, 2021

ላለማልቀስ መጨከን‼️

 ወቅቱ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ነው። ጃፓን ክፉኛ ተደቁሳለች። ምድር የሬሳ ማሳ ሆናለች። የአሜሪካው ፎቶግራፈር አንድ ህፃን ላይ ቀልቡ አረፈ። ቤተሰቦቹን ያጣ፣ የሞተ ታናሽ ወንድሙን በጀርባው ያዘለ ህፃን። ሐዘኑን በእልህ የዋጠ፣ ላልማልቀስ የጨከነ ህፃን።

ወንድሙን ሬሳ ወደሚቃጠልበት ቦታ ይዞ ሄደ። የሚያቀጥለው ሰው "አምጣ የተሸከምኸውን ነገር ልቀበልህ" አለው።

ህፃኑም በንዴት "የተሸከምሁት ወንድሜን እንጂ ዕቃ አይደለም" አለው። ጨክኖ ከወንድሙ መለዬት አልቻለም። ነገር ግን ማልቀስ አልፈለገም። ከንፈሮቹን ነክሶ ሳጉን ወደ ውስጥ ሞጅሮታል። ይህ ምስል ዛሬ ድረስ በጃፓን እንደ ትልቅ የጥንካሬ ማሳያ ይቆጠራል። ጃፓን ከዚያ በኋላ ላለማልቀስ ወሰነች። እነሆ ላለፉት 80 ዓመታት ጃፓን አላለቀሰችም።

ኢትዮጵያ ሀገሬ መሰል አደጋ ፊቷ ላይ አንዣቧል። ከጦርነቱ ማግስት የሚኖረው የሞራል ስብራት ከባድ ነው። እልፎች ወላጆችን፣ ወንድምን፣ እህትን፣ ልጅን፣ ህፃናትን ያጣሉ።ትንቢት ሳይሆን እውነት ነው። ዛሬም በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች እንደ ሸክላ እየደቀቁ ነው። ነገ የባሰ ያስፈራል። ኢትዮጵያ በየ20 እና 30 ዓመታት ጉዞ፣ ወጣቶቿን እንደ ራባት ድመት ቀርጥፋ የምትበላ ምታተኛ ምድር ናት። መድኃኒት ያጣች የደም ምድር-አኬልዳማ።

መፍትሔው አንድ ነው። ላለማልቀስ መጨከን ነው። ለዚህ ያበቁን ለመሳቅ ሲከጅሉ፣ እኛ ላለማልቀስ መጨከን። ላለማልቀስ ካልተጨከነ፣ ከጦርነቱ ማግስት ያለው የስነልቦና ቀውስ ሌላ ጦርነት ነው። ሌላ የሀገር ስብራት ነው። ዛሬ በስሜት ፈረስ ላይ ሆነን አይታይም። ነገ ቆም ስንል፣ የሁላችንም ምስል የዚህ ህፃን ነው። ማዳን ባንችል፣ ላለማልቀስ እንጨክን-ኢትዮጵያ ትቀጥል ዘንድ🙏

©Zelalem Tilahun

♻️Telegram: https://t.me/ZelalemTilahun2011

♻️YOUTUBE: https://www.youtube.com/channel/UCuUyLFXfRQIqnR82iwa43bg

♻️Twitter: https://twitter.com/zelalem_tilahun?s=09

♻️Facebook: https://www.facebook.com/zelalem.tilahun.12

 

No comments:

Post a Comment