(የሌቦች ጥበብ)
የሆነ ቦታ ነኝ-ከ ኦሮሚያ ሰማይ ስር፡፡ ትዕቢት
የሚባል ምግብ 1-5 ተደራጅተን እየበላን ነው፡፡ ……(ለምን ትዕቢት የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ግን የሚያውቅ የለም……ምን አልባት
ይህን ምግብ የፈለሰፈው “ትዕቢት” የሚባል ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ ምን አልባትም “ትእቢተኛ” ሰው ሊሆን ይችላል፡፡) ከመሃከላችን
በቅርቡ የተሾመ የአንድ ትልቅ ተቋም ሀላፊ አለ፡፡ በተቋሙ ስለነበረው ስር የሰደደ የሙስና መረብ ማውራት ጀመረ፡፡ መረቡን ለመበጠስ
እየሞከረ እንደሆነም ነገረን፡፡….ግን ብዙ ውሾች እየጮሁ እንዳስቸገሩትም ነገረን፡፡ …..የትኞቹ ውሾች? ለምን ጮሁ? ብለን ጠየቅነው፡፡
“ነገር በምሳሌ ጠጅ በብርሌ”…… እንዲሉ በምሳሌ
ሊያስረዳን…… “ነገሩ አንዲህ ነው” ሲል ጀመረ፡
“……..አንድ
የጥንት የበሬ ሌቦች ጥበብ አለ፡፡ ሌቦቹ በሌሊት ከመንጋው መሃል በሬዎችን ለይተው ለማውጣት ሲሄዱ ከ ቀራተኛው በ ከፋ መልኩ ፈተና
የሚሆኑባቸው ውሾች ናቸው፡፡ ስለዚህ የእነሱን ጩኸትና ልፊያ ለማለፍ ሲሉ ትንሽ ቁርጥራጭ ስጋ ለውሾች ይዘው ይሄዳሉ፡፡ መጮህ ሲጀምሩ ትንሽ ስጋ ጣል ያደርጉላቸዋል፡፡
አሁንም ሲጮሁ ትንሽ ስጋ ጣል ያደርጉላቸዋል፡፡ አንደኛው ሌባ ውሾችን ሲያታልል አንደኛው በሬውን ይፈታል፡፡ ውሾችም በተደጋጋሚ
ቁርጥራጭ ስጋ የሰጣቸውን ሰው እየተላመዱ ይሄዱና መጮህ ያቆማሉ፡፡ በቁርጥራጭ ስጋ ልሳናቸው ተዘግቶ የ ጌታቸውን በሬ ከመንጋው
ለይተው ይዘው ሲሄዱ ዝም ይላሉ፡፡ በትንሽ ስጋ ብዙ ስጋ የያዘውን በሬ አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡ አንድ ቀን ጌታቸው ይህን በሬ አርዶ
ከዚህ በላይ ስጋ እንደሚያበላቸው ለ አፍታ ማሰብ አይችሉም፡፡ ጊዜያዊ ጉምጅታው በ አደራነት የሚጠብቁትን ታላቁን በሬ አሳልፈው
እንዲሰጡ ያርጋቸዋል፡፡ ከዚህም አልፎ ሌባውን እንደጌታቸው ይቀርቡታል፡፡ …..” ሲል አስረዳን፡፡
የ ኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ የተሻለ የሚገልፀው
ምሳሌ የለም፡፡ ማህበረሰብ ውስጥ ሁሉም ሰው የነቀዘ አእምሮና አስተሳሰብ የለውም፡፡ ትንሽ መርዝ ብዙውን ውሃ አንደምትበክለው ሁሉ፤
ከህሊናቸው የተጣሉ ትቂት ሰዎች ማህበረሰብን አብረው ያነቅዛሉ፡፡ ጥቂቶች የህዝብን ገንዘብ በ አካፋ ይዘርፉና በዙሪያቸው ላሉት
በ ማንኪያ ያቀምሳሉ፡፡ በማንኪያ ሲጎርሱ የሚያሳይ ምስልና ቪዲዮ ለማስፈራሪያ ያስቀምጡላቸዋል፡፡ ከዚያ የፈለጉትን ይዘርፋሉ…..ህዝብን
እራቁት ያቆማሉ፡፡ ….በዙሪያቸው ያሉ ሰዎችም እንደውሾች የበሉትን ቁርጥራጭ ስጋ እያሰቡ ከመጮህ ዝም ይላሉ፡፡ የበሉት በማንኪያም
ሆነ በአካፋ አብረው ከርቼሌ እንደሚወርዱ እያሰቡ ዝም ይላሉ፡፡ ….መጮህ ለሚጀምሩ አዲስ ውሾች ደግሞ ተመሳሳይ ቁርጥራጭ ስጋ ይወረወርላቸውና
ዝም ይላሉ፡፡ …..በማንኪያ መቅመስ ያልፈለጉ ሰዎች ደግሞ ሴራ ይፈጠርላቸውና ይባረራሉ ወይም በዛቻና በጉልበት አፋቸውን እንዲዘጉ
ይደረጋሉ…….እነሱም……
“ከመሞት
መሰንበት ይሻለኛል ብዬ
ባቄላ
ፈጨሁኝ ድመቴን አዝዬ”
……..እንዳለው ሰውዬ ህሊናቸው
እየደማ በዝመታ ይኖራሉ፡፡ ከዚህ የባሰ የሚገርመው ግን ቁርጥራጭ ስጋ
ያገኙት ውሾች ተገልብጠው ለሌባው ከለላ ሁነው በባለቤቱ ላይ መጮሃቸው ነው፡፡
ይች የሌቦች የሂሳብ ቀመር ከመንግስት ተቋማት
በላይ በግል ተቋማት መሻሻያ ተደርጎባትና ተጨማሪ ቀመር ተሰርቶላት በተግባር ውላለች፡፡ የባልስላጣኑን አፍ በቁርጥራጭ ስጋ አዘግተው
የህዝብን በሬ የሚዘርፉ፣ በደሃ ጉሮሮ እሾህ የሚሰኩ ሰግብግብ ግለሰቦች ተበራከቱ፡፡ …….ባለስልጣኑም የተቀበለውን የህዝብ አደራ
ለማፍያዎች አሳልፎ ሰጦ አፉን ዘግቶ ይኖራል፡፡ ግለሰቦች ህዝብን ገፈው እራቁቱን ሲያቆሙት ቁሞ ይመለከታል፡፡እዳይጮህ ልሳኑ ተይዟል፤
እንዳይሸሽ በሁለት በኩል በረጅም ገመድ ታስሯል (በስልጣንና በቁርጥራጭ ስጋ)፡፡ ይህን ሁሉ አሸንፎ ለ መጮህ ሲሞክር ተጨማሪ ቁርጥራጭ
ስጋ ይጣልለታል፡፡ ወይም ስኳር እንዲልስ ይደረጋል፡፡ አሊያም ትንሽ ስልጣን ይጨመርለታል፡፡……….በ አድርባይነት ኅሊናውን ረግጦ፣
ለቁርጥራጭ ስጋ ኖሮ ይሞታል፡፡
……. በዚህ መልኩ ግለሰቦች እየከበሩ ሀገር
ትዋረዳለች፡፡ ……..የብዙዎች ድምፅ በጥቂቶች ይዋጣል፡፡ ህሊና ያላቸው ሰዎች ስልጣንና ሃላፊነትን እየሸሹ ይሄዳሉ፡፡ ውሾቹም ለጌታቸው
ሳይሆን ቁርጥራጭ ስጋ ለጣለላቸው ሌባ በታዛዥነት ይኖራሉ፡፡ በሌባው ሳይሆን ዞረው ባሳደጋቸው ጌታ (ህዝብ) ላይ ይጮሃሉ……..ከፍ
ሲልም ጥርሳቸውን አሹለው ይናከሳሉ፡፡………ተነካሹም ቁስሉን በ እምባው እያጠበ ኖሮ ይሞታል!!!
ለሌቦችም ለውሾቹም ልቦና ይስጥልን!
No comments:
Post a Comment