Monday, September 12, 2016

የ 2009_አብይ_መልዕክት

#በታደሰ_ቁጥር_የምንቀር_ከኋላው
       (
በውቀቱ ስዩም)
አንድ እግሬን 2008 ላይ ተክዬ፣ አንድ አግሬን ደግሞ ወደ 2009 ለማራመድ ድንበር ላይ ቆሜአለሁ፡፡ የዘመን ድንበር ላይ! ማቆም አይደለም አይን ጥቅሻ ማዘግየት የማንችለው የዘመን ድንበር ላይ! እንደ ዘንድሮ አዲስ ዓመት ግራ አጋብቶኝ አያውቅም፡፡
ይህን የምለው በዓሉ ድምቀት ሳይሆን ከልቤ ነው፡፡ ……..ሰው የተሻለ ነገር ሲናፍቅ አዲስ አመትን አይደለም ነገ መንጋት በጉጉት ይጠብቃል፡፡
.......
ልጅነቴ ዘመን መለወጫ ቀን የሚሰጠኝን አዲስ እጀጠባብ (ካሽመር ሙሉ ልብስ) በማሰብ የጳጉሜን ሌሊቶች ሙሉ እንቅልፍ አይወስደኝም ነበር፡፡ አሁን ግን በመኖር እንጂ ካሽመር የሚታለል ልብ የለኝም፡፡

…...የዘመን መለወጥ የሚደምቀው፣ የሰው ልጅ በኑሮ፣ በአስተሳስብ፣ አመለካከትና በሁለንተናዊ እሳቤ አብሮ ማደግና መቀየር ሲችል ነበር፡፡ አሊያ በውቀቱ እንዳለው የዘመን ሰንኮፍ ሆነን ሁሌም ወደኋላ እንቀራለን፡፡
………‹‹የደረደርነውን ብሎኬት፣ ያለንን የባንክ አካውንት›› እያዬን ያደግን መስሎ ከተሰማን ተሳስተናል፡፡ ያደግነው በቁስ እንጂ መንፈስ አይደለም፡፡ <ማህበራዊና መንፈሳዊ> እድገት ከሌለ <ኢኮኖሚያዊ> እድገት ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡ እንደ ሀገር እቃ እቃ ድምር ውጤት አድገን ሊሆን ይችላል፣ ማህበራዊና መንፈሳዊ እድገታችን ግን ቁልቁል እንደ ካሮት እንደ ወረደ ነጋሪ አያሻውም፡፡ ለዚያም ነው የምስኪኖች በደል፣ የንፁሃን ደም ሰከንዶች እንኳ ህመሙ የማይሰማን፡፡ 

................
አንዱ ህመም አንዱን ካልተሰማው ‹‹ሰውነት›› የሚሉት ነገር ወደ መቃብር አፋፍ እየወረደ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡ ሰውነት ሲካድ ቀጥሎ የሚመጣው ‹‹አውሬነት›› ነው፡፡ አራዊት ዓለም ደግሞ መጠፋፋት እንጂ መረዳዳትና ተሳስቦ መኖር የለም፡፡ “The fittest will survive” የሚለው የቻርለስ ዳርዊን አስተምህሮ የተነገረው አራዊት ነው፡፡ 

.......
ወደ ሰው ሲተረጎም ደግሞ ፍፃሜው ቂም፣ በቀልና እልቂት ነው፡፡ በሰው ልጆች እኩልነት የሚያምን ሰው እራሱን ከሌሎች አያስበልጠም አያሳንስም፡፡ የምናዬውና የምንሰማው ግን በተቃራኒ ነው፡፡
እኔም ለዚህ ነው፣ ከነገ ይልቅ ትናንት የተሻለ መስሎ ስለተሰማኝ ድንበሩ ላይ ግራ ገብቶኝ የቆምሁት፡፡ ለዚህ ነው ሁሉም ሰው ወደ አዲስ አመት ተስፋውን በኬሻ ተሸክሞ ለመራመድ ሲዘጋጅ፤ እኔ ግን ተስፋዬ በላይ ስጋቴ አይሎ ድንበሩ ላይ የቆምሁት፡፡ ለዚህ ነው በሰውነቴ ለመኖር ስል ወደ ነገ ለመራመድ ፈራሁት!
ማንም ነገን በትክክል መተንበይ ባይችልም መገመት ግን ይችላል፡፡ …….‹‹የቀበርነውን ማንነት፣ የገደልነውን ሰውነት፣ ያጨለምነውን መንፈሳዊነት›› መመለስ ባንችል እንኳ እንደ ገቦ አዝርዕት እንዲበቅል እድል መስጠት ካልቻልን ነገ ከዛሬ የባሰ እኩይ ቀን ላለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ የለንም፡፡
ስለዚህ ወገኖቼ……….ወደ አዲስ አመት ስንራመድ ያጠለቅነውን ጭንብል አውልቀን፣ አይነ ህሊናችንን ገልፀን በሁሉም አቅጣጫ መመልከት ካልቻልን ‹‹ተቀምጠን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ›› የሚቸግረን ቀን ይመጣል፡፡ ስለ ሰውነትና ስለ ፍቅር እንኑር፡፡ አንደበታችን ሳይሆን ስራችን ይመስክር! 21ኛው መቶ /ዘመን የሰውን ልጅ ማሸነፍ የሚቻለው ትዕቢት ሳይሆን ፍቅር ነው (አራት መቶ አርባ አራት ነጥብ)
ሁሉም ያልፋል ፍቅር ያሸኝፋል!
2009
. መልካም እሳቤ ዘመን ይሁንልን!
(
ዘላለም ጥለሁን
)


No comments:

Post a Comment