‹‹ኢትዮጵያ›› በሰቆቃ እንድትኖር የተፈረደባት ምድር ትመስለኛለች፡፡ ቅድመ አያቶቻችን ልጆቻቸውን
በፋሽት አረር አጡ፡፡ ‹‹ጥዋ ተርታቸው እድል ፈንታቸው›› ገና የሆኑ አያቶቻችን በህይወት ተርፈው አባቶቻችንን ወልደው አሳድገው
ለአብዮት እሳት ገመዱ፡፡ ከአብዮቱ የተረፉ አባቶቻችን በፈንታቸው ልጆችን ወልድው በዘረኝትነት ቋያ አቃጠሉ፡፡ የዘረኝነት ቋያ እያደረ
ብዙዎችን ወደ እሳቱ ገመደ፡፡ እስከዛሬ ብዙ ህልም ጨነገፈ፡፡ ብዙ ተስፋ ነጠፈ፡፡ ብዙ የንፁሃን ነፍስ ተቀጠፈ-እዚች ባልቴት ሀገራችን
ኢትዮጵያ ውስጥ፡፡
እንዴት አንድ ሀገር ተመሳሳይ የሆነ ለቅሶ ከመቶ ዓመት በላይ ታለቅሳለች? እንዴት አንድ
ሃገር ለመቶ ዓመት በተመሳሳይ በሽታ ታማ ትሞታለች? ውሎ ሲያደር ሞት ሲለመድ፣ የሰው ልጅ ደም እንደውሻ ደመ ከልብ እየሆነ ቀረ፡፡
እንዴት ሰው የራሱን ወገን ይገላል? ብዬ የሞኝ ጥያቄ አልጠይቅም ግን እንዴት ከመግደሉ በፊት ትንሽ ማሰብ ያቅተዋል?