Wednesday, July 4, 2018

ሻምበል አስረስ ገላነህ ብዙነህ [ጎጃሜው]

                                          (የግፍ ጥግ የተፈፀመበት የጦር መኮንን)
ለመጀመሪያ ጊዜ በአማራ ህዝብ ላይ እየተሰራ ያለውን አሻጥር ፊት ለፊት የተጋፈጠ የጦር መኮንን ይህ ሰው ይመስለኛል፡፡ ‹‹ሳሞራ››ን ፊት ለፊት የተጋፈጠ፣ ባህርዳር በተደረገው ስብሰባ ከእነ በረከት እና ህላዌ ጋር ‹‹በአማራ ስም አትነግዱ›› ብሎ ፊት ለፊት የተፋጠጠ የመጀመሪያው ሰው ይህ ይመስለኛል፡፡ በዚህም ድርጊቱ ‹‹ ጎጃሜው›› የሚል ቅፅል ስም እንደተሰጠው ባለታሪኩ ይገልጻል፡፡ በዝሆኖች ጥርስ የተነከሰበት ይህ ቆፍጣና የጦር መኮንን የማታ ማታ ‹‹ የአልጋ ቁራኛ›› የሚያደርገው ግፍ፣ እላዩ ላይ ነዳጅ አርከፍክፎ ፓርላማ ፊት ለፊት እራሱን እንዲያቃጥል ያስወሰነው መከራ ተፈፀመበት፡፡  ይህ ሰው ‹‹የካድሬው ማስታወሻ›› የተሰኘ ግለ ታሪክ 2005 ዓ.ም አካባቢ ለንባብ አብቅቷል፡፡ መፅሃፍ አንብቤ ያለቀስኩበትን፣ ከመጠን በላይ ልቤ የተነካበትን ጊዜ አላስታውስም፡፡ የዚህን ጀግና ግለታሪክ ሳነብ ግን አልቅሻለሁ፡፡ በማልቀስ ብቻ አላለፈም፣ ከውስጥ የሆነ ተስፋ ሲሰበር ይታወቀኝ ነበር፡፡ የጭካኔን ጥግ ያየሁበት ትርክት ስለሆነ!

Tuesday, July 3, 2018

የሀገሬ መንገድ

                              (Photo: Google)
ወገኛው በኃይሉ ገ/መድህን ‹‹የእኔ እና የሀገሬ ነገር መሬት አልረገጠም›› ብሎ ነበር ከአንድ ሁለት ሶስት ሳምንት በፊት፡፡ አንዳንዱ በቃ ኢትዮጵያ መቼም ወደማይቀለበስ የዲሞክራሲ አስተዳደር ተሸጋገረች ብሎ ይዘምርና ትንሽ ቆይቶ ‹‹እነ እንትና አለቀላችሁ!፣ እነ እንትና እንዲህ መደረግ አለባቸው፡፡ እንዲህ እንዳደረጉንማ በዋዛ አንለቃቸውም፡፡ እንትና ይታሰር፡፡ እንትና ይመርመር! እንትና ይሰቀል››  እያለ ይፎክራል፡፡ ወገን ዲሞክራሲ እና ፉከራ አብሮ አይሄድም፡፡ ዲሞክራሲ ‹‹ከፍፁም ይቅርታ እና መቻቻል የሚፈጠር የማህበረሰብ ደልድይ ነው››፡፡  የሆነ ቦታ ላይ ሁሉንም ነገር በይቅርታ ማራገፍ ካልተቻለ፣ ቂምና በቀል ጅረት ነው-ማቆሚያ የለውም፡፡ ጅረቱ ውቅያኖስ ውስጥ ተጠራቅሞ አንድ ቀን ነፋስ ሲንጠው፣ ማዕበሉ የሚያመጣው ቀውስ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በትንሹም ቢሆን ቀምሰነዋል፡፡ 

Monday, July 2, 2018

ጠ/ሚ/ዶ/ር አብይ አህመድ በሀገሪቱ ለተደረጉ የድጋፍ ሰልፎች ያቀረቡት ምስጋና


የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች ሆይ!
ምስጋና ከሚቀበል ሰው ይልቅ ምስጋና የሚሰጥ ታላቅ ነው! ያለ ጥርጥር ይህንን እንረዳለን፡፡ ባለፉት ሶስት ወራት በሀገራችን እየታየ ያለው የለውጥ ጭላንጭል፣ አሁን የሀገራችን ህዝብ እየሰጠን ካለው ወሰን አልባ ድጋፍ እና ፍቅር ጋር የሚወዳደር እንዳልሆነ ብንገነዘብም መንግስት ይሄንን ድጋፍ ፍቅር ክብር እና አለኝታነት ለተሰሩ ስራዎች እንደተሰጠ ምስጋና ብቻ ሳይሆን በቀጣይ እንሰራቸው ዘንድ ለሚገቡን በርካታ ስራዎች ተግባራዊነት የተላለፈ የአደራ መልእክት እንዲሁም የአጋርነት ማሳያ አድርጎ በመቁጠር ከምን ጊዜውም በላይ በፍጹም ቁርጠኝነት እና ትጋት ለማገልገል በጽናት ይሰራል፡፡