Thursday, November 5, 2015

ለምን አታገባም? (ክፍል-02)

እንደምን አላችሁ፡ እስኪ ወጋችንን እንጠርቅ፡፡ ወጋችንን ያቆምነው 45 ዓመቱ ጓደኛዬ ላይ ነው፡፡                                            ልቀጥል……

ምነው ጋሸ ነገር እምቢ አለህ እንዴ?
ኧረ!…..አንተ!……እሱማ…………ጥዋት ጥዋት የአባቴን ጎራዴ እየመሰለ እያስቸገረኝ ነውአለ ደስ በሚል ፈገግታ፡፡ ደሃ ፈገግ ሲል እንዴት ደስ ይላል መሰላችሁ፡፡
ቀላል አልሳቅሁም፡፡ ምንም እንኳጥዋት ጥዋትየሚሉት ቃላት ባይዋጡልኝም፤ ሌላ ጊዜስ ብዬ ለመጠየቅ ግን ድፍረቱን አጣሁ፡፡
ያም ሆነ ይህ ጎራዴ መምሰሉ የስሜት ይሁን የሽንት ባይታወቅም፤ የጓደኛዬ መልስ ወንዶቹ እስከ 45 ዓመት ድረስ ጥሩ ተስፋ እንዳላቸው የሚያበስር ነው፡፡
ታዲያ ለምን አታገባም፣ እንዴት ለአንተ የምትሆን ሴት ታጣለህ?
ኧረ እሱስ አላጣሁም፡ እኔ ምመጥናት ሴት አትገኝም ነው እንጂ?”
ምን ማለት ነው እሰኪ አብራራልኝ?

አየህ የመጀመሪያው ችግሬ የወር ገቢዬ ነው፡፡ እስኪ ንገረኝ 1500 ብር ደሞዝ እንዴት ነው ትዳር የሚታሰበው፡፡ እኔ እንደፈረደብኝ ልቃጠል እንጂ እሷ ምን በወጣት ከእኔ ጋር ትሰቃይ! ሁለተኛው ምክንያቴ፡ 40 አመት በላይ የሆኑ አቻዎቼን ልጥበስ ብዬ ሳስብ የመውለዳቸው ነገር ያሳስበኛል፡፡ በዚያ ላይ ብዙዎቹ አግብተው የፈቱና ቢያንስ አንድና ከዚያ በላይ ልጅ ያላቸው ናቸው፡፡ 1500 ሌላ ተጨማሪ ቤተስብ ደግሞ አይታሰብም፡፡ ሶስተኛው ምክንያቴ፣ ወጣቶችን ለመጥበስ ሞክሬ ነበር፡፡
እሺ ምን አሉህ?
““ሂድ ጥፋ ከፊቴአሉኝ፡፡ዘመንህን ሙሉ ስትማግጥ ጨርሰህ አሁን እኔን ትጠይቃለህ! እኔ ልጅህ አልሆንም? ስንት ሎጋ ወጣት ሞልቶ የአንተን ወገብ ሳሽ እንድኖር ለምን ፈረድህብኝ?” እያሉ ያገኘኋቸው ሁሉ ማኪያቷቸውን ጨልጠው ከሃሳቤ ጋር ጥለውኝ ይፈተለካሉ፡፡ ቆይ እኔ ምለው ባላገባስ? ግን ደግሞ ዘሬን በዚህ ምድር መተካት አለብኝ፡፡ ዘሬ መቀጠል አለበት፡፡አለ በትካዜ፡፡
ከገባበት የሀዘን ስሜት እንዲወጣ ብዬ በማሰብእና አሁን ምን አሰብህ?” አለሁት፡፡
እስኪ በቤተሰብ ገጠር እያስፈለግሁ ነውአለኝ፡፡
እኔም በሆዴየፈረደባቸው የገጠር ሴቶች እዚያ አዛባ ከመዛቅ አዲስ አበባ ሲሏቸው ሁሉ ነገር አበባ መስሏቸው ይመጣሉ፡፡ብዬ ለራሴ ሳወራ ድምፅ ነገር አሰማሁናምን አልህ?” ብሎ ጠየቀኝ፡፡
አይዞህ ተስፋ አትቁረጥ በርታ፤ ትዳር እኮ በመረዳዳት ነው የሚገነባው፡፡ ሴቷ ስትመጣ እኮ ባዶ እጇን አትመጣም፡፡ ባይኖራትም ስራ ትሰራለች፡፡ ስለዚህ የአንተ ቢጤ የሆነችዋን ፈልግና በቶሎ በል፡፡ አሊያ ዕድሜህ ከርሞ 46 ከዚያ 47 እያለ መሄዱ አይቀርም፡፡
አሱስ ልክ ነህ፤ አሁንማ ቶሎ ጠብቶ ቶሎ እየመሸ ተቸገርሁአለኝ አንጀትን በሚያላውስ የድምፅ ቃና፡፡
ጀርባውን መታ መታ አድርጌ አይዞህ ጋሸ ብዬ ልለየው ስል፤ይልቅ አንተም እንደኔ አትጃጃል በቶሎ ብለህ ጥበስአለኝ አይኖቹ እንባ እያቀረሩ፡፡
እሺ ብዬው ተለያዬን፡፡ ወዲያው አንድ ሀሳብ ፊቴ ላይ መጥቶ ድቅን አለ፡፡ ወንዱ ልጅ 45 ዓመቱ እንደዚህ ከተጨነቀ ሴቶች 40 ዓመት ካለፋቸው እንዴት ይጨነቁ ይሆን? እነሱ ይመልሱት፡፡ ማግባት የሁሉም ፍላጎት ቢሆንም ሴት ልጅ 45 ዓመት በኋላ የመውለድ እድሏን ተፈጥሮ ስለሚገታባት ሀዘኗ እጥፍ ድርብ ይሆናል፡፡ ይህ ርዕሰ ጉዳይ በአንድ ወቅት አፋር ክልል ውስጥ ለስራ ከመሃል አገር የሄደች አንዲት ሴት አውቶብስ ውስጥ ከሌላ ሰው ጋር ስታወራ ጆሮዬን ጣል አድርጌ የሰማሁትን ንግግሯን አስታወሰኝ፡፡
ነገሩ እንዲህ ነበር፡፡ ከጎኗ የተቀመጠውለምን አታገቢም?” ብሎ ጠየቃት፡፡ መቼም እሱ ባለትዳር መሆን አለበት፡፡
ጠልቼ መሰለህ፡፡ ከዚህ በኋላ ማንስ ይጠይቀኛል? አግብቼስ ያምርብኛል? ባይሆን በቀረችኝ ጊዜ ልጅ የሚወልድልኝ ሰው ባገኝ እድለኛ ነኝአለችው፡፡
ሰውዬው አመዱ ቡን ሲል ታየኝ፤ ነጭ ላብ አላበው፡፡ ምን አልባት እኔን እባክህ ተቸገርልኝ ትለኛለች ብሎ የፈራ ይመስላል፡፡
ይቅርታ ረስቼብሎ ስልክ አውጥቶ መደወል ጀመረ፡፡
አሳዘነችኝ! የልቧን እየነገረችው አንድ የማፅናኛ ቃል እንኳ ሳይመፀውታት ከወዲያኛው ካለው ሰው ጋር በስልክ ማውራት ቀጠለ፡፡ እኔም ፌርማታዬ ስለደረስሁ ወረድሁኝ፡፡ እግዜር ከረዳት ወልዳ ይሆናል፡፡ ይህ ካልሆነ አሁን 45 ዓመት ያልፋታል፡፡
ከወንድ ይልቅ ሴት ልጅ ለጋብቻ መሽቀዳደም እንዳለባት የዚች ሴት ንግግር በቂ አይመስላችሁም፡፡ ምን ዋጋ አለው ታዲያ ብቻቸውን መወሰን አይችሉ፡፡ ጋብቻ የሁለቱን ወገኖች ውሳኔ ይፈልጋል፡፡ የአንድ ቀልደኛ ጓደኛ ጨዋታ ትዝ አለኝ፡፡ አንድ ጓደኛ ነበረችው፡፡ በተዋወቁ በሁለት ሳምንቱ እንጋባ ብላ ጠየቀችው፡፡ ልጁም ሲበር መጣና እንዲህ አለኝ፡
አይ ሴቶች! ሀና እንጋባ ብላ ጠየቀችኝ፡፡ መልኳን እንኳ በደንብ ሳላውቃት! አየህ ሴቶች በርገር ጋብዘኝ ብለው ከሚጠይቁህ ጥያቄ ቀጥሎ የሚጠይቁህ ጥያቄእንጋባነውአለኝ ፊቱ ላይ የመረበሽ መንፈስ ይታይበታል፡፡
ትንሽ ከሳቅሁ በኋላ፤ ወንዱስ ብዬ ጠየቅሁት፡፡
ወንዱማ ማትሪክ ውጤት መውደቁን ሲሰማ ከደነገጠበት በላይ የጋብቻ ጥያቄ ያስደነግጠዋል፡፡
ስጠይቅህ ምን ብለህ መለስህላት
አሱማ እኔም በፈንታዬ የጋብቻውን ጥያቄ ለመሸሽ ስል ድንግል መሆን አለመሆኗን እና እድሜዋን ጠይቄ አሸማቀቅኋት፡፡ ከዚህ በኋላ አጠይቀኝምአለኝ፡፡
ክፍተታችንን ተጋግዘን ከመሙላት ይልቅ አንዱ አንዱን እያሸማቀቀ፣ ሸምቃቃ ትውልዶች ሁነን እንቅር? ለማንኛውም እዚህ ላይ አንድ ትምህርት እንውሰድ፡፡ ወንዶች እንደፈለጉ ሲንዘላዘሉ ኑረው አንድ ቀን መንገድ ዳርም ቢሆን ለምነው ማግባት ይችላሉ፡፡ ሴት ልጅ ግን በቶሎ ካልተሰበሰበች እንቅፋቱ ብዙ ነው፡፡ በእርግጥ ለዚህ እኔ ተጠያቂ አይደለሁም፡፡ ምንም እንኳ አሁን ወንዱን ጠይቀው የሚያገቡ ሴቶች ቢበራከቱም፤ ባህላችንና ሃይማኖታችን ግን አይፈቅድም፡፡
ለምን ግን ወንዶች የሴቶችን ጊዜ በከንቱ ያጠፉባቸዋል? ለምን ያጃጅሏቸዋል? ይህን ጥያቄ እራሴን ስጠይቅ፤ በአንድ ወቅት አንድ ካፌ ውስጥ ከጓደኛዬ ጋር ሻይ ስንጠጣ የተፈጠረው ነገር ትዝ አለኝ፡፡
ፒያሳ አካባቢ አንድ ካፌ ውሰጥ ሻይ እየጠጣን ነው፡፡ አንድ ፉንጋ የጓደኛዬ ጓደኛ ስሙን አስተዋውቆኝ ተቀላቀለን (ስሙ ለጊዜው ይቅር)፡፡ ከዚያ አንድ ሁለት እያልንእድለኛው አጀንዳውስጥ ገባን፡፡ ከዚያማ የጓደኛዬ ጓደኛ እኔን እንኳ ሳይሳቀቅ ታሪኩን ይዘከዝክ ጀመር፡፡ አስካሁን እንኳን ስማቸውን መጥራትና ቁጥራቸውን ማስታወስ አይደለም መልካቸውን ቢያያቸው እንኳ መለየት የማይችላቸው የሴት ጓደኞች እንደነበሩት ደሰኮረ፡፡
ጓደኛዬየስንት ሴቶችን ድንግልና ወስደሃል?” ብሎ ጠየቀው፡፡
እስኪ ቆይ…..ከዚያ ….ሁለት….ከዚህ……ሶስት…..አምና…..አንድአጠቃላይ አስራሁለት፡፡
እኔ በጣም ደነገጥሁ ከአንድ ሰው በላ አውሬ ጋር የተፋጠጥሁ መሰለኝና ወንበሬን ሸሸት አድርጌ ተቀመጥሁ፡፡ ጓደኛዬ “….አስራሁለት ሰው አርደሃላብሎ ከትከት ብሎ ይስቃል፡፡ ጓደኛዬም አናደደኝና አሁን በዚ ዜና ይሳቃል አልኩት ኮስተር ብዬ፡፡
ምን ላድርግ እኔ አላደረግሁትአለኝ በፌዝ፡፡
ባታደርገውስ የአህቶችህ ቁስል አንተን አያምህም ማለት ነውአልሁት፡፡
እኔ ምለው፤ አይኤስ (ISIS) ከዚህ በላይ ምን አደረገን? በጣም ስለተናደድኩ ፊቴን አኮሳትሬደግሞ ይሄን እንደ ጀብዶ ታወራለህ?” አልኩት፡፡ዋናው አሸባሪ አገር ውስጥ እያለህ እስካሁን መንግስት እንዴት አላሰረህም?” አልኩት፡፡
ምን አደረግሁ አስደሰትኋቸው እንጂ አልገደልኋቸው፡፡ እንዴውም እውነቱን ልንገርህ፤ ዝናዬን የሰማች አንድ ልጅ እራሷ መጣ አባክህ ድንግልናዬን ገርስስልኝ ብላ ጠይቃይኝ የተባበርኋት አለች፡፡ የስንቶችን እምባ አብሻለሁ መሰለህአለኝ ከትከት ብሎ እየሳቀ፡፡
እኔ ንግግሩ ክፉኛ ስላጥወለወለኝ (እናንተንም እንደኔ እደሚሰማችሁ እገምታለሁ) ከዚህ  በላይ መታገስ አልቻልኩም፡፡ እሳት በሚተፋ ቁጣ እንዲህ አልኩት፡
አባቶችህ ዳር ድንበር ለመጠበቅ አድዋ፣ መተማ፣ ዶጋሌ፣ ማይጨው፣ ሶማሊያ እየዘመቱ ጠላትን ገርስሰው በጀብዶ ይችን አገር አስረከቡህ፡፡ አንተ ደግሞ መንደር ለመንደር እየዞርክ ክቡር የሆነውን የሴት ልጅ ክብረ ንፅህና ገረሰስሁ ብለህ ጀብዶ ታወራለህ፡፡ አባቶችህ የጠላትን ደም አፈሰሱ፣ አንተ ደግሞ የእህቶችህን ደም አፍሰህ ደረትህን ትነፋለህ፡፡ አንተ ሰው አይደለህም፤ አውሬ ነህ አልሁትና ተስፈንጥሬ ወጣሁ፡፡
አህህህህህ…….ከትከት ብሎ ይሰቃል፡፡ ተናድጀ ዞር ስል፤እነሱ ክብር ያልሰጡትን እኔ እንዴት ክብር ልስጠውአለኝ፡፡ ከዚህ በላይ መናገር የለብኝም ጥያቸው ወጣሁ፡፡
ብቻዬን እተጓዝኩ ግንእነሱ ክብር ያልሰጡትን እኔ እንዴት ክብር ልስጠው”…የሚለው ቃል ወደ ውስጥ ያቃጭልብኝ ጀመር፡፡ በእርግጥ እውነቱን ነው፡፡ እንዴት ሴት ልጅ፤ እወድሻለሁ፣ አገባሻለሁ ስላላት ብቻ ወርቋን አሳልፋ ትሰጣለች፡፡ ይሄ ሁሉ ባህላችንን ንቀን ዘለን የአውሮፓ ዝባዝንኬ ውሰጥ መግባታችን ነው፡፡ በወጉ በማረጉ ከፈለጋት ቤተሰቦቿን በወላጆቹ ማስጠየቅ ነበረበት፡፡ ተናድጃለሁ፡፡ አዎን ይሄ የሴቶችም ችግር ነው፡፡ ምላሱ ጤፍ የሚቆላን ወንድ እንዴት በአንዴ አምነው አልጋ ላይ ይወጣሉ፡፡
ለአፍታ ከንዴቴ በረድ ስል የጥንቱ ባህል ትዝ አለኝ፡፡ በቤተሰብ የተዳረ የገጠር ሙሽራ የሚስቱን መልክ የሚያየው፣ ከሰርጉ በአስረኛው ቀን ፊቷን ስትገልጥ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ምን አልባት አካባቢውን ቤቱን ካወቀው በዛፍ ተጋርዶ ሊያያት ይችላል፡፡ እስከ አስረኛው ቀን (ጫጉላ እስኪፈርስ) ድረስ ግን በነጠላ በከፊል የተሸፈነውን አይኗንና አፍንጫዋን ብቻ ሲያይ ይቆያል፡፡ ሁለ ነገርዋን በሂደት ነው ማየት የሚችለው፡፡ ዛሬ በአራት አመት እጮኝነት የማይገኘውን ፍቅር የገጠር ሙሽራ በአስር ቀን ቆይታ ጽኑ ፍቅር ውስጥ ይገባል፡፡ ትዳራቸውንም ዘመድ መርቆታልና ዘለቄታ ያገኛል፡፡ ምን ይሄ ብቻ ሙሽራዋን ለማዬት የፈለገ ሰው ጥሎሽ (ብር) ይሰጥና ፊቷን ትንሽ ገለጥ አድርጋ እንድታሳይ ሚዜው ያዛታል፡፡ በገጠሩ የጋብቻ ባህል ሁሉም ነገር በስርዓት ነው፡፡ ወይኔ ልጅ ሁኜ ሙሽራ ለማዬት የከፈልሁት ብር ቆረቆረኝ፡፡ ዛሬ ከላይ እስከደረታቸው፣ ከታች እስከ….(ለመጥራም ይከብዳል) ገላልጠው ያለክፍያ ለመንገደኛ ያሳያሉ፡፡ ታድያ ለወንዱ ሁሉን ነገር በአንዴ ካሳየችውና ከሰጠችው፣ ምን ፈልጎ ከሷ ጋር ይቆይ፡፡ ፈረሱን በገመድ ለመያዝ ገብስ ማሳየት እንጂ ማብላት አይጠበቅባችሁም፡፡ ለምን እንደሆን አላውቅም ሴት ልጅ ሽፍንፍን ስትል ውበት አላት፡፡ ይህ የባህላችንም የሃይማኖቱም አስተምህሮ ነው፡፡ ይቅርታ ቄስ ቄስ ሸተትሁ መሰለኝ፡፡ ይህን ሃሳብ እያውጠነጠንሁ ታክሲ ውስጥ ስገባ ከቀሚስ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ወንዶች ባህሪ ትዝ አለኝ፡፡
አሁን አሁን የአዲስ አበባ ወንዶች ቀሚስ የለበሰች ገጠር ቀመስ ልጅ ካዩ እንደ ውሻ አሽትተው አይለቁም፡፡ አንዳንዶች ባለሱሪ ሲያባርሩ ኖረው፤ ለማግባት ሲወስኑ ወደ ቀሚስ ይዞራሉ፡፡ ምክንያታቸውን ስጠይቋቸው፡የገጠር ልጆች ብዙላይፍስላላዩ ይለምዳሉ፡፡ በዚያ ላይ እንደከተሜዎች ብዙ ሳንቲም አይፈልጉምይሏችኋል፡፡ ሰምታችኋል አዲስ አበቤዎች፤ ይችን ጥናት ተጠቀሙባት፡፡ ቀሚስ መልበስና ሽፍንፍን ማለት ባል ለማግኘት በቅርቡ አዲስ አበባ ውሰጥ የተገኘ አዲስ መፍትሔ ነው፡፡ ታየኝ ነገ የቀሚስ ገባያ እሳት ሲሆን፡፡ ለማንኛውም አርባ ሽንሽን እንዳትገዙና እነ እንትና….. ደግሞ ጠይቀዋችሁ እንዳትዋረዱ፡፡
ግን ሴቶች ለምን አያገቡም? ምን አይነት ወንድ ነው የሚፈልጉት? ገንዘብ ቅፈላው በሴት ነው በወንድ ይብሳል?

                  (((((((((((((((ይቀጥላል!!!)))))))))))))))))

3 comments: