Thursday, December 31, 2015

“ትርጉሙን የማላውቀው ህይወት በ___ብር”

የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በዓል ማግስት ምሽት የባቡሩን መንገድ ተከትዬ ከሜክሲኮ ወደ ቡናና ሻይ እያዘገምሁ ነው፡፡ በአካባቢው የመኪና፣ የሰውና የባቡር ድምፅ ነግሷል፡፡ ቡናና ሻይ አካባቢ ስደርስ አንድ ተባራሪ መፅሐፍ ነጋዴ….

“ትርጉሙን የማላውቀው መፅሃፍ በ 20 ብር….”
“ትርጉሙን የማላውቀው መፅሃፍ በ 20 ብር…..”

እያለ አልፎ ሂያጁን ይጣራል፡፡ ወደ ቦሌና ወደ አራ ኪሎ የሚሄድ ታክሲ ፈላጊ ልጁን ገረፍ አድርጎት ፈገግ ብሎ ያልፋል፡፡

እኔ ትንሽ ቆም ብዬ መፅሀፎችን ገረፍኋቸው፡፡ ነገር ግን ከፅሁፋቸው መብዛት የተነሳ ርዕሳቸውን በደንብ ማስታወስ አልቻልኩም፡፡ የተፃፉት ግን በእንግሊዝኛ ነው፡፡ የማንበብም የመግዛትም ሙድ ውስጥ ስላልነበርሁ እኔም ገረፍ አድርጌው ሄድሁ፡፡

Monday, December 28, 2015

“ቱቦ አትሁኑ…ቱቦ አትሁኑ…”


“ልጆቼ ቱቦ አትሁኑ፡፡ ቱቦ ባዶ ነው፡፡ የሚይዘው ነገር የለም፡፡ ማስተላለፍ እንጂ መያዝ አይችልም፡፡ ቱቦ ካልሰጡት በራሱ የሚያመነጨውና የሚያስተላልፈው ነገር የለም፡፡ ቱቦ ሁሌም ጥገኛ ነው፡፡ ልጆቼ ቱቦ አትሁኑ፡፡ቱቦ አትሁኑ፡፡ ልጆቼ መተላለፊያ አትሁኑ፡፡”
ይህ ንግግር በአንድ ወቅት አንድ አባት የተናገሩት ነው፡፡ በወቅቱ ንግግራቸውን ከቁብ አልቆጠርሁትም፡፡ ሌሎቹም እንደዚሁ፡፡ ምክንያቱም ሰው እራሱ ቱቦ ነው፤ በአፉ አስገብቶ በ ‘እንትኑ’ የሚተፋ የምግብና የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦ፡፡ ከዚህ ያለፈ ሰውን ከቱቦ ጋር ሊያመሳስለው የሚችል አንዳች ነገር በጊዜው አልታየኝም፡፡ ይህ ደግሞ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ስለዚህ በጊዜው ሀሳባቸውን ውድቅ አደረግሁት፡፡ መብቴ ነው መቀበልም አለመቀብልም (አንቀፅ---)፡፡

Thursday, December 17, 2015

እኔ ምለው……

 ያልበላሽን አከሽ ባመጣሽው ጣጣ
የታከከው ሳይሽር ያልታከከው ወጣ”.....
የምትል የኩርፊያ ግጥም ለዚያች እከክ አካኪ ልፅፍላት ፈልጌ ነበር፡፡ ማከኩን ላታቆም ምን አስለፈለፈኝ ብዬ ከራሴ ጋር ስሟገት ያበደ ነፋስ ሃሳቤን በተነው፡፡ ይገርማል ነፋስ የሚበትነው ሃሳብ ተሸክሜ የምጓዝ ከንቱ ፍጡር መሆኔን አላውቅም ነበር፡፡ በነፋስ የሚመራ የነፋስ ትውልድ አካል! ኧረ መፈላሰፍ! የሰው ልጅ ከነፋስ አይደል እንዴ የተሰራው፡፡ ነፋስነቴን ልክድ ነው እንዴ! ቢሆንም ቢሆንም……ነፋስነታችንና መሬትነታችን ሚዛን ደፋ ወዳጄ! እሳትና ውሃ የት ሄዱ?

Sunday, December 13, 2015

እያነቡ እስክስታ....

       “የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ
        ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትም አልወጣ”
………ጥርስ ከምላስ፣ እጅ ከእግር፣ አይን ከጆሮ፣ ህሊና ከእውነት የከረረ ጥላቻና ጦርነት ውስጥ የገቡበት እኩይ ዘመን ላይ ደርሶ “የገደለው ባልሽ……” ብሎ መተረት ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡ ምን አልባት እንዲህ ብለን ብንተርት የተሻለ ይመስለኛል::
     “የገደለው ግራሽ የሞተው ቀኝ አጅሽ
      ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከራስሽ አልወጣ”
ከታሪክ ማኅደር
የቅርብ ታሪካችንን በጨረፍታ የኋሊት ስንመለከት በተለይ በደርግና በሻቢያ መካከል ናቅፋ ተራራ ላይ በተደረገው አስቀያሚ ጦርነት ብዙ ጀግና የኢትዮጵያ ልጆች ባሩድ እያሸተቱ ላይመለሱ የጥይት ራት ሁነዋል፡፡ በዚህ ጦርነት ከተከሰቱትና ታሪክ ከማይረሳቸው ሁነቶች መካከል በስጋ የአንድ እናት ልጆች በተቃራኒ ተሰልፈው የተረፈረፉበት ጦርነት መሆኑ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በወታደራዊው መንግስትና ጎን ለጎን በተፈለፈሉት የነፃነት ታጋዮች መካከል በተፈጠሩ የርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች ምክንያት ኢትዮጵያን አንድ እርምጃ ወደፊት ሊያራምዱ የሚችሉ ትውልዶች
      “ፋኖ ተሰማራ ፋኖ ተሰማራ
       አንደ ሆቺ ሚኒ አንደ ቼ ጉቬራ”፣ 
እያሉ እርስ በርስ እየተጠላለፉ እሳት ውስጥ ገብተው ላይመለሱ አሸልበዋል፡፡