Thursday, December 17, 2015

እኔ ምለው……

 ያልበላሽን አከሽ ባመጣሽው ጣጣ
የታከከው ሳይሽር ያልታከከው ወጣ”.....
የምትል የኩርፊያ ግጥም ለዚያች እከክ አካኪ ልፅፍላት ፈልጌ ነበር፡፡ ማከኩን ላታቆም ምን አስለፈለፈኝ ብዬ ከራሴ ጋር ስሟገት ያበደ ነፋስ ሃሳቤን በተነው፡፡ ይገርማል ነፋስ የሚበትነው ሃሳብ ተሸክሜ የምጓዝ ከንቱ ፍጡር መሆኔን አላውቅም ነበር፡፡ በነፋስ የሚመራ የነፋስ ትውልድ አካል! ኧረ መፈላሰፍ! የሰው ልጅ ከነፋስ አይደል እንዴ የተሰራው፡፡ ነፋስነቴን ልክድ ነው እንዴ! ቢሆንም ቢሆንም……ነፋስነታችንና መሬትነታችን ሚዛን ደፋ ወዳጄ! እሳትና ውሃ የት ሄዱ?

…… ደግሞስ ስንት መድሃኒተኛ በሞላበት አገር ስለ እከክ ማውራት አይደብርም፡፡ እናንተን ከደበራችሁ የራሳችሁ ጉዳይ አልላችሁም፡፡ እኔን ግን አልደበረኝም፣ ግን አሞኛል፡፡

አሞኛል ዘንድሮ ጤናም አላግንቼ
በነገር ሰላጤ ጎኔን ተወግቼ………. አለ ያገሬ ብሶተኛ (ብሶት የተኛ)፡፡

የአባይን ልጅ ውሃ ጠማውየሸክላ ሰሪ ልጅ በገል ይበላል……..” እያልን እየተረትን የመድሃኒተኛ ልጅ በበሽታ ቢሞት ምን ያስገርማል፡፡ ምን ዋጋ አለው ወዳጄ እኛ ቁጭ ብለን ተረት እየተረተርን ሆዳችንን ስናክ፣ ሌሎቹ በእኛ ተረት እየተዝናኑ ሰገነት ላይ ቁጭ ብለው ውስኪ ይጨልጣሉ፡፡ ይጨልጧ! መብልና መጠጥ ሆድን እንጂ አእምሮን አይሞላ፡፡ ጭንቅላትን ዘቅዝቆ ለሆድ የሚሮጥበት እኩይ ዘመን!...... ወዳጄ! እኛ የበላንን ቁጭ ብለን ስናክ ሌሎቹ ያልበላቸውን ያካሉ፡፡ ከዚያም እከካቸው ለእኛ፡፡ እኛ ያከክነው ወደ እነሱ አይተላለፍም፣ ሳይበላቸው ያከኩት የእነሱ በሽታ ግን ለእኛ ይተርፋል፡፡ እነሆ እንዶድና እምቧይ በሃገሩ በጠፋበት ዘመን አንዱ ለአንዱ እከኩን እያስተላለፈ የእከክ በሽታ ዓለምን ሞላት፡፡ እከክ ደግሞ ሲነኩት የሚያገረሽ፣ ሲነኩት ሌላ የሚወልድ፣ እንቅልፍ የሚነሳ መጥፎ በሽታ! ማከክ ለአንዱ በሽታ ለሌላኛው መድሃኒት ሆኗል ወዳጄ!...... ለማንኛውም ወዳጄ ማከኩ ይብቃ-የታከከው እስኪድን፡፡ አይመስልህም፡፡ አይምሰልህ ምን አገባኝ፡፡ እከኩ ሲይዝህ ወይም ከታከክህ በኋላ ይገባሃል፡፡…… አሁንም ሀሳቤን ነፋስ ወሰደው፡፡ ነገሩ ይበቃልነገር ቢበዛ በአህያ…………፡፡ ለጠቢብሰ………..፡፡

                        እስኪ አንዳንዴ ተውኝ ለብቻዬ ልሁን
                        ነገዬን ልመልከት በዛሬ ሰቀቀን
                            አይቀጥልም !


No comments:

Post a Comment