Saturday, June 24, 2017

የ ሲኦል ነፍሳት: ክፍል ፪

አቤት የሰው ዓይን ንደዚህ ያስፈራል? ዓይን የሌለበት አካባቢ ስፈልግ-ኮርነር ጋር አንድ ወንበር አገኘሁ፡፡ በፍጥነት ወደዚያ ሄጄ ተቀመጥሁ፡፡ አስተናጋጁ ገና ወንበሩ ላይ ሳልቀመጥ እየተንደረደረ መጦ ምን ልታዘዝ አለኝ፡፡ 
ቢራ አልኩት፡፡ 
‹‹
ምን ቢራ ይሁንልህ››….
የተገኘውን ብዬ መለስኩለት፡፡ 
ፍራት ውስጤን ሲያርደው ይሰማኛል፡፡ ትንሽ ቀና ስል ስገባ ያፈጠጠብኝ 7 እንስቶች 14 ዓይን አሁንም እኔ ላይ አፍጧል፡፡ መልሼ አቀረቀርሁ፡፡ ቢራው መጣ፡፡ ቀና ላለማለት ቢራውን ደጋግሜ ወደ አፌ መላክ ጀመርሁ፡፡ ድፍረት እየተሰማኝ ሲመጣ ቀና አልሁ፡፡ እኔ ውጭ ምንም አይነት ተስተናጋጅ የለም፡፡ ወዲያ የመጠጥ መደርደሪያ ይታያል፡፡ ከጎን ዲጄው የፍስክ ዘፈኖችን ወደ አየሩ ያስወነጭፋል፡፡ ጀርባ በር አካባቢ ሁለት አስተናጋጆች በተጠንቀቅ ቁመዋል፡፡ ቤቱ እኩል እርቀት 7 እንስቶች ባለጌ ወንበር ላይ ቁጭ ብለው ይቁለጨለጫሉ፡፡ አብዛኞቹ ጡታቸው ገና በአግባቡ ያላጎጠጎጠ፣ እድሜአቸው 18 ያልረገጠ ብላቴናዎች መሆናቸውን ቦግ እልም እያለ የሚያሳያቸው ዲምላይት ብርሃን ያሳብቃል፡፡…..እኒህ እንስቶች፣ ‹‹ሲኦልም ድንበር አለ እንዴ?›› በሚያሰኝ መልኩ ቦታውን እኩል የተከፋፈሉ ይመስላል፡፡

Thursday, June 22, 2017

የ ሲኦል ነፍሳት:ክፍል ፩

አዲስ አበባ ከቤቴ ይዞኝ የወጣው ሹፌር፣ በመካኒሳ በኩል አቋርጦ ወደ ፈጣን መንገዱ ገባ፡፡ ከዚያም መኪናዋን እንደ ኮሪያ ሚሳኤል ያስወነጭፋት ጀመር፡፡ ሩቅ ከሄድሁበት ሀሳብ ብንን ያልሁት ሹፌሩ የሚሰቀጥጥ ‹‹ክላክስ›› ድምፅ ሲያሰማ ነው፡፡ ፍጥነት ታጥፎ ወደ ፈጣን መንገዱ ከሚገባ መኪና ጋር ሊላተም ለትንሽ ተረፍን፡፡
ከዚህ አሰፋ መዝገቡ እለት የመኪና አደጋ ሞት ወይም አካል ጉዳት ሪፖርት የተረፍነው፣ የሌላኛዋ መኪና ሹፌር መሪውን ጠምዝዞ ከመንገዱ በመውጣቱ ነበር፡፡ መኪናዋ ትንሽ ብትጎዳም ሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አልነበረም፡፡ አዲስ ዜና አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በየቀኑ ከሚደርሱ አሰቃቂ አደጋዎች በጣም ቀላሉና ለወሬ የማይበቃ ነው፡፡ ችግሩ ግን ‹‹ የዛሬ ንጥሻ ወደ ከፋ ጉንፋን ከማደግ አይመለስም››፡፡ እኛም ስለጉንፋኑ ማውራት እንጂ ንጥሻውንና ጉንፋኑን የሚያመጡትን ነገሮች ስለመከላከል ስንደክም አይታይም፡፡

Monday, June 19, 2017

እነሆ በ ክረምት-የቅኔ በረከት


በውቀቱ የ‹‹ኦሾ›› መፅሃፍ ከ እምነቱ ሳይሆን ከ ሃይማኖቱ እንዳቆራረጠው ‹‹ ከ አሜን ባሻገር›› ላይ ሹክ ብሎን ነበር፡፡ ምን አልባት በውቄ የ ‹‹ Der Antichrist›› ፀሐፊ የሆነውን የ ጀርመኑን ‹‹ፍሬዲሪክ ኒቼ››ን እጣ ፈንታ ካነበበ በኋላ ሃሳቡን የቀየረ መሰለኝ፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ከሁሉም በላይ የቀደመ ሃይማኖቱ ‹‹የማለዳ ድባብ›› ከተኛበት ቀስቀሶ፣ ከሄደበት መልሶ፣ የቅኔ ጣእሩን አስተንፍሶ ለመድብሉ የወል ስም እንዲሆን ያሰገደደው፡፡ በ ቆመበት ማን ይኖራል! በውቀቱ ገጣሚ መሆኑ ብቻ ሳይሆን እይታው በጣም ይገርመኛል፡፡ ለማኛውም እምነትህ የራስህ ነው፣ ግጥምህን በ ቶሎ ወዲህ በል!….ከፈለግህ በ ‹‹ኦሾ››…አሊያም በ‹‹ኒቼ›› ማመን ትችላህ፡፡ አይመለከተኝም! ይችን ነገር ልጠቀም መሰለኝ (lol)

አለ እንጂ ደግሞ ያ በላይ በቀለ ‹‹አንቅልፍ እና ሴት›› የሚለውን ክሽን ግጥም ሸበሌ መርቀን አጣጥመን ዓመት ሳይሞላን ‹‹ከ ሴተኛ አዳሪ የተኮረጀ ሳቅ›› ብሎ ሊያስቀን ይሁን ሊያሳቅቀን ከተፍ ብሏል፡፡  ይህ ብላቴና የራሱ የሆነ ድንቅ እይታና የ ግጥም ቆጠራ ዘዴ ያለው ልጅ ነው፡፡ ‹‹መልሱን ጠጣሁበት››፣ ‹‹እንቅስቃሴዎች ሁሉ ፖለቲካ ናቸው›› በጣም የመሰጡኝ ግጥሞች ናቸው፡፡ የግጥም ከራማው ይጠብቅህ!