Sunday, June 14, 2015

ዳማካሴ

                 click here for PDF
የኢትዮጵያ የባህል ህክምና ታሪክ ሲነሳ በፈዋሽነቱና በተደራሽነቱ በቀዳሚነት ብቅ የሚለው ዳማካሴ ነው፡፡የኢትዮጵያውያን ፈውስ፣ የረጅም ዘመን የጤና ወዳጅ-ዳመካሴ፡፡ታሪክ ጠቅስን መረጃ ተንተርስን መናገር ባንችልም ኢትዮጵያ ውስጥ በባህል ህክምና ባለሙያዎች ለፈውስ ከተገኙት ቀዳሚ ቅጠሎች አንዱ ዳማካሴ መሆኑን መገመት አያዳግትም፡፡አንድ ሰው የህመም  ስሜት ሲሰማው የሰፈር አዛውንቶች የሚሰጡት የመጀመሪያው ምክር ዳማካሴ ውሰድበት ነው፡፡ በመሆኑም ዳማካሴ፤ ጤና አዳምን፣ ፌጦንና ነጭ ሽንኩርትን አስከትሎ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በፈዋሽነቱና በተደራሽነቱ በቀዳሚነት ይታወቃል፤ ምንም እንኳ የቅጠሉ ዝርያና አበቃቀል ከቦታ ቦታ ቢለያያም፡፡ ታላቁ ገጣሚና የወግ ቀማሪ በውቀቱ ስዩም “ኢትዮጵያዊ ነኝ” በተሰኘ ግጥሙ እንዲህ ሲል ተቀኝቷል፡፡
                                               ……………..                     
“ግትር ጠላቴን በአጭር አንካሴ
ራስ ምታቴን በዳማካሴ
ነቅዬ ምጥል
አገር በነገር የማብጠለጥል
ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡”
……………….
ዳማካሴ ከሌሎች የመድሀኒትነት ባህርይ ካላቸው ዕፅዋት ለየት ይላል፡፡ 
በመጀመሪያ ደረጃ ዳማካሴ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ይገኛል፡፡ 2ኛ፡ ዳማካሴ ከሌሎች እፅዋቶች በተለየ ድርቅን የሚቋቋም፣ከፍ ያሉ ቦታዎች ላይ የሚበቅል፣ በጋ ከከረምት የሚገኝ ነው፡፡ 3ኛ፡ ዳማካሴ ዘር፣ ወገን፣ ቋንቋ፣ ሐይማኖት ሳይለይ ለሁሉም የሰው ዘሮች የእውቀት ተከፍሎት ሳይኖር የፈውስ ችሮታን የሚያድል የእፅዋት ዘር ነው፡፡ 4ኛ፡ ዳማካሴ ለማንኛውም አይነት የሰው ልጅ ህመም በማስታገሻነት የሚያገለግል፣ ያለምንም ዋጋና ውጣውረድ የሚገኝ እፅዋት ነው፡፡ እኛስ እንደ ዳማካሴ ያሉ ሰዎች እጥረት አልገጠመንም፡፡ ጥላቻን፣ መለያየትን፣ አድመኝነትን፣ ሀገወጥነትንና ስግብግብነትን የሚያክሙ የሰው ዳማካሴዎች፡፡ “ለሰው መድሃኒቱ ሰው ነው” እንዲሉ አበው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት በአንድነትና በአብሮነት መንፈስ አንዱ ለአንዱ መድሃኒት፣ አንዱ ለሌላው ድጋፍ በመሆን ፍፁም ባህላዊና ሃይማኖታዊ በሆነ የመረዳዳት ባህል ኑሯል፡፡ ምንም እንኳ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ አንዳንድ “በስንዴ ውስጥ እንክርዳድ” እንዲሉ መጥፎ የሆኑ ታሪኮች ቢኖሩንም፤ አብዛኛው የታሪካችን ክፍል የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህላዊ እሴት የሰፈነበት ነበር፡፡ አሁን ዘመን ተቀየረ፡፡ ሌላው የዓለም ክፍል በውህደተ ዓለም (Globalization) ጨርቁን ጥሎ አበደ፡፡ ጭራቅ የሆኑ የምዕራባውያን አስተምህሮዎችና ባህሎችም በመላው ዓለም ከ ሸቀጡ ጋር አብረው ተራገፉ፡፡ የኔ ዘመን ትውልድም ያለፈበትን አኩሪ ባህል በጫማው ረግጦ የምዕራባውያን ባህልና እብደት ማማ ላይ ወጣ፡፡ ሁሉም ተያይዞ በጥላቻ፣ በመለያየት፣ በአድመኝነት፣ በሀገወጥነትና በስግብግብነት ወንዝ ፈሰሰ፡፡ የራሳቸውን ምቾትና ድሎት ብቻ በሚያሰላስሉ (self-centered) ስግብግቦች ዓለም ተሞላች፡፡ያንዱ ትራጄዲ ህይወት ለሌላው ኮሜዲ ሆነ፡፡ ዓለም የምትመራበትን የቻርለስ ዳርዊን “ the fittest will survive” የሚለውን መርህም ይሁን የካፒታሊዝሙ “ the rich becomes more rich and the poor becomes more poor” የሚለው አስተምህሮ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በዘመናት የተገነባ አኩሪ የመተጋገዝ ባህል ላላቸው አገሮች በቀጥታ ተግባራዊ ማድረግ ፍፃሜው አስከፊ ሊሆን ይችላል፡፡ እነሆ ሃብታም ለመሆን፣ አሸናፊ ለመሆን፣ ኃላፊ ለመሆን ያልሰራነው ግፍ፣ ያላንኳኳነው የድሃ በር፣ ያልተበተብነው የነገር ድር የለም፡፡ አሁን የቅጠል ሳይሆን የሰው ዳማካሴ ደረቀብን፡፡ ይህ መጥፎ ነው፣ ይህ ጥሩ ነው፣ ይህ ለሀገርና ለወገን አይበጅም ብሎ የሚያስተምረን የእውቀት መድሃኒት አጣን፡፡ ዳማካሴ ድርቅን ተቋቋቁሞ ለሰው ልጆች መድሀኒት እንደሆነው ሁሉ መከራና ችግርን ተቋቋቁሞ አጥንት ሳይቆጥር ለሀገርና ለወገን የሚከራከር፣ የወገንን የህሊና ቁስል የሚያክም ዳማካሴ ጠፋ፡፡ ሁሉም በውሸትና በሸፍጥ በሰለጠነ አንደበት ቃላትን እየደረደረ፣ አነጋገሩን እያሳመረ የራሱን ኑሮ ከማመቻቸት ባለፈ ለወገን ተቆርቋሪ የሚሆን ዳመካሴ ጠፋ፡፡ “ውሸት ሲደጋገም…..” እንዲሉ ቃላትን እደረደረ በውሸት ዶሴ የሚከራከር እንጂ መረጃን ተንተርሶ፤ ታሪክን ጠቅሶ ስለእዉነት የሚያወራ ብሎም ወደ እውነት ማማ የሚወጣ ዳማካሴ ጠፋ፡፡ ዳማካሴ መራራ ነው፤ ግን ፍቱን መድሀኒት ነው፡፡ እውነት መራራ ናት፤ ግን ጣፋች ናት፡፡ ይችን መራራ እውነት ታግሎ የሚያሸንፍ ብርቱ ዳማካሴ ያስፈልጋል፡፡ ለራሱ ሳይሆን ለሀገርና ለህዝብ ልዕልና የቆመ፣ እንደ ዳማካሴ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ሚገኝ፣ ከሩቅ እንደ አክሱም ሐውልት የሚታይ ጀግና፡፡ የነበሩን ዳማካሴዎች በአቅራቢያቸው በበቀሉ ሌሎች እፅዋት ተዋጡ፡፡ ማንነታቸውንና መድሃኒትነታቸውን ሌሎች ሸፈኑት፡፡  “ከአህያ ጋር የዋለች…….”እንዲሉ ሌሎችንና ዳማካሴዎችን መለየት አቃተን፡፡ ዳማካሴ ነው ብለን ስንቀምሰው መርዝ እየሆነ ተቸገርን፡፡ ሙስናን፣ ዘረኝነትን፣ ትዕቢትን፣ ምቀኝነትን፣ አድመኝነትንና ስግብግብነትን በውስጡ ያረገዘ መጥፎ መርዝ፡፡ አባካችሁ ዳማካሴዎች ተለዩ፡፡ ሀገሬ ብዙ ዳማካሴ ያስፈልጋታል፡፡ ዳማካሴ ባለስልጣን፣ ዳማካሴ ምሁር፣ ዳማካሴ ሽማግሌ፣ ዳማካሴ ነጋዴ፣ ዳማካሴ ገበሬ፣ ዳማካሴ ወጣት የስፈልጋታል-ከህመሟ ትፈወስ ዘንድ፡፡ አይመስላችሁም?
                            ሰኔ 7፣ 2007 ዓ.ም
                      zelatilahun@gmail.com

                               ዘላለም 

No comments:

Post a Comment