ከውስጥ በገነፈለ ስሜት፣ በተመረጡ
ውብ ቃላት፤ የተፃፈ ልብ አንጠልጣይ እውነተኛ የፍቅርና የትግል ታሪክ፡፡ ባለታሪኩ እንዲህ ብሎ ይጀምራል፡
“ከልብ በመነጨ ፍቅርና ቁርጠኝነት በለጋ እድሜየ የጀመርኩት ጉዞ አቅጣጫውን የቀየረው ባላሰብኩት ሁኔታና ወቅት
ነበረ፡፡ ማንኛውም ሰው በሁኔታዎች አስገዳጅነት ያላሰበበትንና አልሞ ያልመረጠውን ሕይወት እንደሚቀበል ሁሉ እኔም እጣ ፈንታዬን
ከተቀበልኩና በመራኝ ጎዳና መንገድ ከጀመርኩ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡”
የዚህ ታሪክ ባለቤትና ፀሀፊ ካህሳይ አብርሃ ነው፡፡ አጋሜ የተወለደው፤ አሁን ኮላራዶ የፋርማሲ ባለሙያ የሆነው ካህሳይ ታሪክ፡፡ ካህሳይ የ60ዎቹ ትውልድ አካል ነው፡፡ በለጋነት እድሜው ኢህአፓን ተቀላቅሎ ከአሲምባ ተራሮች እስከ ተከዜ በረሃ፣ ከዋግምራ እስከ ራያ፣ ከሰሜን ተራሮች እስከ ሱዳን የታገለ የዛ ዘመን ነፀብራቅ ነው፡፡ ይህ የካህሳይ ታሪክ ብቻ አይደለም የ60ዎቹን ትውልድ ማንነት የሚዘክሩበት፤ የታሪክ ፍሰቱን ጠብቆ የተጻፈ ምርጥ መፅሃፍ፡፡ ቆራጥ ትውልድ! ለአላማቸው የቆሙ ወጣቶች! ግን ደግሞ በፈጠሩት ርዕዮተ ዓለም እርስ በርሳቸው የተጫረሱ የአንድ እናት፣ የአንድ መንደር፣ የአንድ ሀገር ብርቅየ ልጆች፡፡ “አብዮት ልጆቿን በላች” የተባለበት ዘመን፡፡ከደርግ የጥይት እራትነት ይመር ንጉሴ በተባለ ገበሬ የተረፈው ካህሳይ የትግል ብቻ ሳይሁን ድንቅ የሆነና ልብ አንጠልጣይ የሆነ የፍቅር ታሪክ ከወሎዋ ቆንጆና ቆራጧ ጀግና ድላይ ጋር በትግል ውስጥ አሳልፏል፡፡ ድላይ ምስራቅ በለሳ ህይወቷ ያለፈ ጀግና ታጋይ ነበረች፡፡ በስሟ ተራራ የተሰየመላት የሴት ጀግና፡፡ ካህሳይ የተለያዩ ድርጅቶችን አነሳስና ማንነትም ይዳስሳል፡፡ ኢህአፓ፣ ሕወሃት፣ ሻቢያ፣ ኢዲዩ፣ ጀብሃ፣ ኢሕአሰ…፡፡ የተለያዩ ሰዎችን ማህደርም ያስቃኛል፡ ዶ/ር ተስፋየ ደበሳይ፣ ድላይ፣ ሀጎስ ማንጁስ፣ ደጀኔ፣ ሽፈራው፣ ብርሃነ፣ ጌታሁን፣ ሮምሃ፣ እንግዳወርቅ፣ የውቅሮው አብኢዩ፣ መለስ ዜናዊ፣ አረጋዊ በርሄ፣ ……….
ስለዚህ መፅህፍ ታዋቂው ፀሀፊ፣ ደራሲ፣ገጣሚና ተርጓሚ ነብይ መኮነን እንዲህ
ይላል፡፡
“ካህሳይ በትግል ውስጥ ፍቅር እንዳለ ያሰየናል፡፡ ፍቅር ከትግል ያዘናጋል ብሎ ከማፍቀር አልተቆጠበም፡፡ ሲያፈቅርም
ተፈጥሮን አልዋሸ፤ ሲፅፍም ተፈጥሮን አልዋሸ፡፡ ነብሱን ለትግሉ ሲሰጥ፤አልሳሳም፡፡ለሰው ነብስ ግን በንፁህ ልቦናውና ለህዝብ ካለው
ፍቅር በመነሳት ሳሳ፡፡ይህንኑም ሳይሳሳ ፃፈ፡፡መፃፍ፤ ሳይሳሱ ለራስ ታማኝነትን መግለፅ ነውና!”
እኔ መፅሀፉ እንደታተመ በአንድ ትንፋሽ አንብቤዋለሁ፡፡አሁን ለሁለተኛ
ጊዜ ለማንበብ እድሉን አግኝቻለሁ (ምስጋና ለአማርኛ መፅሃፍት ገፅ)፡፡ አንብባችሁ ስጨርሱ እናንተንም እንደ ካህሳይ ከአሲምባ ጋር
ፍቅር ይይዛችኋል፡፡ ታሪክን ማወቅ ካለፈው ጥፋት ለመታረምና ወደፊት እንዳይደገም ለመከላከል እንዲሁም ከመልካም ጎኑ ለመማር ይጠቅማል፡፡
ስለዚህ በእንቶፈንቶ ወሬ የሚያነበንብ ትውልድ ሳይሆን በውነተኛ ማንነትና ታሪክ ላይ የተመሰረተ ትውልድ እንፍጠር!
መፅሐፉን በፒዲኤፍ ለማግኘት
ከላይ ያለውን ወይም ማህደረ መፃህፍት ውስጥ ያለውን የመፅሐፉን ምስል ይጫኑ፡፡
ዘላለም ፡ ግንቦት 29፡
2007 ዓ.ም
ሻሎም! መልካም
ንባብ!
No comments:
Post a Comment