እለተ ሰንበት ግንቦት 16፣ 2007 ዓ.ም፡፡ እናት ሀገሬ 5ኛውን አገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ ና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ አጠናቃለች፡፡ምንም እንኳ የሀገራችንን ልማትና ዲሞክራሲ ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ፀረ ልማት ኃይሎች ምርጫው ምርጫ ሳይሆን በገዢው ፓርቲ ፊታውራሪነት በአጋር ፓርቲዎች ግራአዝማችነት የተጠናቀቀ ቅርጫ ነው ቢሉም፡፡ “ውሾች ይጮሃሉ፤ ግመሎችም መጓዛቸውን ይቀጥላሉ ”፡፡ ጠንካራና ከመጮህ ያለፈ ራዕይ ያላቸው ውሾች እስካልተፈጠሩ ድረስ፡፡ በትናንቱ የምርጫ እለት የተፈጠረ አንድ ፈገግ የሚያሰኝ ክስተት ልንገራችሁ፡፡
አክስቴ ናት፡፡ አክስቴ የምትኖረው ክ/ሀገር (የገጠር ግዛት) አንዲት የወረዳ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ረፋዱን ትንሽ አመም አድርጓት ነበር፡፡ እኔን አክስቴ! ከቤተስኪያን መልስ ውጡና ምረጡ እያሉ ሰፈር ለሰፈር በሚዞሩ አመር-አሮች ተጣድፋ ወደ ምርጫ ሄደች፡፡ሰልፍ ነበር፡፡ ረጅም፡፡ ወይ ሰልፍ እቴ፡፡ ሰልፍ ብርቅ ነው እንዴ፡፡ አልሰሜን ግባ በለው፡፡ያውም በአምስት አመት አንዴ፡፡ እኛ አለን አይደል እንዴ ለዳቦ ሰለፍ፣ ለታክሲ ሰለፍ፣ ለካፌ ሰለፍ፣ ለፍተሻ ሰለፍ፣ ለስብሰባ ሰልፍ፣ መንገድ ለማቋረጥ ሰለፍ፣
ለኮንዶሚኒየም
ሰልፍ፣ ለመ………..ሌላውን ተውት፡፡ ወደ ነገሬ ልመለስ፡፡ ወግ ወጉንማ ልብ አንጠልጣይ ምናምንቴ ሚባል ነገር አለ አይደል፡፡ ለማንኛውም አክስቴ ወረፋው ደርሷት ወደ አስተባባሪው ተጠጋች፡፡ የምርጫ ካርዱን ለአስተባባሪው አስረከበች፡፡ አስተባባሪው ካርዱን ተቀብሎ ካገላበጠው በኋላ ከትከት ብሎ ሳቀ፡፡ ጥርሱን ያሳምረው በአክስቴ ይስቃል! እድሜ ልክ ስንራገም ኖርን እስኪ አንዳንዴ እንመርቅ ብዬ ነውኮ፡፡ መስሎሻል “የውሸት ምርቃት እርግማን ነው ” ብሏል፡፡ ማን ነበር፡፡ እኔ እንጃ፡፡
አክስቴ በሁኔታው ተበሳጭታ ምነው ብላ ጠየቀች፡፡ ይህ እኮ የምርጫ ካርድ ሳይሆን የህክምና ካርድ ነው አላት፡፡በሰልፉ የተሰላቸው ወገኔ በአክስቴ የኮሜድ ትወና እራሱን እያዝናና ኢህአዲግን መረጠ፡፡ ምነው ሌላ ፓርቲ የለም እንዴ ስለ
ጠየቅሁ፡፡የአክስቴን ሰፈር ንቀዋት ነው መሰል ጠንካራ ተቃዋሚ አልተወዳደረም አለችኝ፡፡ እኔም አንድ ምክር ጣል አደረግሁ፡፡ ለሚቀጥለው
እንዲጠነክሩ በደንብ አብሉአቸው ወይም ጅምናዜም ይስሩ ብዬ ተቀኘሁ፡፡ በካርዱ መመሳሰል ድራማ የሰራችው አክስቴም አብራ ስቃም ተሳቃም (እኔንም አሳቀቀችኝ እንጂ-ወይ አለመማር አለች ሻሸ) እንደገና ከቤቷ ካርዱን አምጥታ የተነገራትን መረጠች፡፡የአክስቴ ስተት ለእኛ ትርጉም ይኖረው ይሆን? እንደፈለጋችሁ ተርጉሙት፡፡ የማሰብ፣የመፃፍ፣የመናገር፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት አላችሁ (አንቀጽ…….)::
የህክምና ካርድ ያላችሁ እንደ አክስቴ በጥንቃቄ አስቀምጡ-የሆስፒታል መረጃ ክፍል ሰራተኞችን ምሬትና ቁጣ ለመቀነስ፡፡ በነገራችን ላይ ዘንድሮ የምርጫ ካርዳ ያላወጣችሁ የህክምና ካርድ የሚያስፈልጋችሁ ይመስለኛል፡፡ አይመስላችሁም? መልስ ወይም ስድብ ያለው መብቱን መጠቀም ይችላል-ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቴን እስካልነካ ድረስ፡፡
ለማንኛውም ለሚቀጥለው 5 ዓመት (2012) ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንገናኝ! ባይ ባይ አለ የሸገሩ ጋዜጠኛ!!!!
ግንቦት 17፣ 2007 ዓ.ም, ሸገር
No comments:
Post a Comment