Wednesday, October 17, 2018

"ቆፍቁፍን ሰድጄ፥ ሸርድምን አመጣሁ"

አባቴ ከሚያውቀው የባሰ ነገር ወይም የባሰ ወዳጅ ሲገጥመው "ቆፍቁፍን ሰድጄ ሸርድምን አመጣሁ" ይተርታል፡፡ ተረቱ እንዲህ ነው፡
"አንድ ሰው ነበር፡፡ ሚስቱ በየቀኑ ለከብቶች ብሎ የገዛውን አሞሌ ጨው እየቆፈቆፈች ትፈረካክስና ለምግብ መስሪያ ትጠቀማለች፡፡ ባል ተቆጣና ፈታት፡፡ ሌላ ሚስት አገባ፡፡ ይችኛዋ ሚስት የበፊቱን የፍች ታሪክ ታውቅ ነበርና አሞሌ ጨውን በመቆፍቆፍ መፈረካከስ አልፈለገችም፡፡ ፍች ሊያመጣባት ይችላል፡፡ ስለዚህ የተሻለው አማራጭ ድምፅ ሳታሰማ በጥርሷ መሸርደም ነው፡፡ አደረገችው፡፡ Just she was a "silent killer". ባል ብዙ ቀን ከተሞኘ በኋላ አንድ ቀን እውነቱን አወቀ፡፡ ከዚያም ሰዎች አንድ ቀን አዲሷ ባለቤትህ እንዴት ናት አሉት? ኧረ ተውኝ "ቆፍቁፍን ሰድጄ ሸርድምን አመጣው" አለ ይባላል፡፡
ምን ማለት እንደፈለግሁ ይገባችኋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ካልገባችሁ አሞሌ ጨው ተሸርድሞ ሲያልቅ ይገባችኋል፡፡

Wednesday, September 12, 2018

ሀሳብና ሰብዕና ቢለያዩስ?


/ መስፍን ወልደማሪያም ለኢትዮጵያ ውለታ ከዋሉ አንጋፋ ምሁራን ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ ከአፄው እስከ አሁኑ ስርዓት ድረስ የታሪክ ማጣቀሻ ሆነው በህይወት ካሉ ምሁራን ውስጥ አንዱ እኒህ ጎምቱ የታሪክ ምሁር ናቸው፡፡ 1960ዎች ኢትዮጵያ በረሃብ አለንጋ ስትገረፍ ከፕ/ ጌታቸው ኃይሌ እና መሰል የወገን ተቆርቋሪዎች ጋር በመሆን ታላቅ ውለታ ውለዋል፡፡ እኒህ ምሁር ‹‹አማራ የሚባል ብሔር/ ነገድ የለም›› በሚል አቋማቸው አማራ ነህ ተብሎ እንደ ኑግ በየቦታው እየተሰለቀ በነበረው ወጣት ዘንድ ትልቅ ተቃውሞ ሲሰነዘርባቸው እንደቆዬ ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ የአሁኑ ዘመን ትውልድ ከእሳቸው አቋም ጋር መስማማት ቢሳነው በማንም መፍረድ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በእሳቸው ትርክት እና በእኛ ትርክት መካከል ትልቅ የታሪክ መጋረጃ አለ፡፡ የታሪክ መጋረጃው ደግሞ ሰው በሰውነቱ ሳይሆን የደምና የአጥንቱን መሰረት ተከትሎ በዘውጌ ፖለቲካ እንዲተሳሰር ተደርጎ የተዘጋጀ መጥፎ መጋረጃ ነው፡፡ / መስፍን በሀሳባቸው ልክ ሆኑም አልሆኑም፣ ሰብዕናቸው መከበር አለበት፡፡ 

Monday, September 10, 2018

‹‹በደሃ እናቶች እምባና በወጣቶች ደም-የስልጣን ቁማር መጫወት ይብቃ!››

(የአዲስ ዓመት መልዕክት)
 
የፕ/ ብርሃኑ እናት ልጃቸውን ቦሌ ተቀብለው ለመሳም ታደሉ፣ የሌሎችም እንዲሁ፡፡ ያም ሆኖ ግን ስስታቸውን ምስሉ ይገልፀዋል፡፡ እናት ምንም ቢሆን እናት ናት፡፡ ለሴኮንድም የልጇን መከራ መስማት አትፈልግም፡፡ ከጀርባ ግን ታላቅ የእምባ ጎርፍ ይታየኛል፡፡ ልጆቻቸውን በአደባባይ በአገዛዙ በግፍ የተነጠቁ እናቶች፣ መሰል ምስሎችን ሲያዩ የሚያነቡት እምባ!  ከአንጀት ተንሰቅስቆ የሚወርድ ትኩስ አምባ! በበቃሽ የማይቆም እምባ!

Saturday, August 18, 2018

‹‹የአገው ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት›› የአገው ህዝብ ወይስ የፖለቲካ ቁማርተኞች ጥያቄ?


                         (ሳይቃጠል በቅጠል፤ በዘላለም ጥላሁን) Must read!
እስኪ ልጻፍ፡፡ ዛሬ ካልጻፍሁ መቼ ልፅፍ ነው፡፡ እናቴ ጓዳውን፣ አባቴ ጋጣውን ተከፋፍለው እስኪለያዩ መጠበቅ የለብኝም፡፡ ምን ማለት እንደፈለግሁ አዊ ዞን የሚኖሩ ወጣቶች ይረዱኛል፡፡ ወደ ዋናው ነጥብ ከመግባቴ በፊት አንዴ ጠብቁኝ ‹‹የዘር ፖለቲካን ሰፈር ድረስ የዘራውን ሰው ሁሉ ልራገም››….‹‹ልጅ አይውጣላችሁ!›› ጨርሻለሁ!.....

እኔ ግን ይች ሀገር ታሳዝነኛለች፡፡ እንደ ዶሮ ብልት ተከፋፍላ ተከፋፍላ ማለቋ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ዛሬ ማንሳት የፈለግሁት ‹‹ጉዳዩ እየገፋ ስለመጣና የእዚህ ጉዳይ አራማጆች ዛሬ አዲስ አበባ ‹‹ራስ አምባ ሆቴል ›› ሲመክሩ ስለዋሉ ነው››

አሁን ‹‹አገው ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት›› የሚሆነው በየት በኩል ነው?……..ይህን ስል የአገውን ማህበረሰብ ማንነት ማሳነሴ አይደለም፡፡ ራሴን ማሳነስ ስለሚሆን፡፡ ሃቁ የአገው ህዝብ የራሱ ቋንቋ አለው፡፡ አብሮት ከሚኖረው አገውኛ ከማይናገረው ህዝብ የተለዬ ባህል እና ትውፊት ግን የለውም፡፡ ለጊዜው ትኩረቴን ‹‹የአዊ ዞን ህዝብ›› ላይ ላደርግ፡፡ ተከተሉኝ፡፡ ወደ ጉዳዩ ለመንደርደሪያ እንዲሆን እና ምሁራን ጉዳዩን በትኩረት እንዲያዩት ፍንጭ ለመስጠት ያህል እንዳንድ አሃዛዊ መረጃዎችን ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡