Saturday, December 22, 2012

ተረት ተረትተረት በሀገራችን ትልቅ ቦታ አለው፡፡ የማህበረሰቡን ብስለት፣ ኑሮ ፣መስተጋብርና አመለካክት የማሳየት አቅም አለው፡፡ እስኪ ከዚህ በታች ስለ አንድ ብልጥ ልጅ የሚተርክ የአፋር ተረት ላውራችሁ፡፡

ተረት ተረት ---የመሰረት/የላም በረት

በአንድ ወቅት በጣም ብልጥ የሆነ 15 ዓመት እድሜ ያለው የአፋር ተወላጅ ልጅ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ልጅ በቤቱ ውስጥ ይደረግ የነበረውን መጥፎ ነገር ያውቅ ስለነበረ ሁልጊዜ ያዝንና ይበሳጭ ነበር፡፡ አባቱ ከእናቱ ገረዶች ከአንድዋ ጋር በድብቅ ይባልግ ነበር፡፡

እናቱም ከቤሰተቡ ውጪ ከአንድ ሰው ጋር ትማግጥ ነበር፡፡ ልጁም ይህንን ሁሉ ስለሚያውቅ በጣም ይናደድ ነበር፡፡ እናም ከእለታት አንድ ቀን በቤቱ ውስጥ አንድ ጥግ ላይ ተሸፋፋኖ ተኝቶ ሳለ የእናቱ ወዳጅ ወደ ውስጥ ሲዘልቅ ልጁን አላስተዋለውም፡፡ እናም እናቱን እንዲህ አላትአንቺ በጣም ደግ ሴት ነሽ፡፡ የጠየኩሽን ሁሉ ሰጥተሽኛል፡፡ አሁን ደግሞ የባለቤትሽን ትልቅ ነጭ በሬ በነገው እለት መብላት እፈልጋለሁ፡፡”  አላት፡፡ የልጁም እናትምንም ችግር የለም፤ አንተ ብቻ አስር የሚሆኑ ጓደኞችህን ይዘህ መምጣት አለብህ፡፡አለችው፡፡ በማግስቱም ወዳጅዋ አስር ጓደኞቹን አስከትሎ መጣ፡፡ እስዋም ወደ ባሏ ሄዳ እንዲህ አለችውይኸውልህ ዘመዶቼ በሙሉ ስለመጡ ልንመግባቸው ይገባል፣ ቁጥራቸውም በጣም ብዙ ስለሆነ እንጀራናሌላ ተራ ምግቦችን ማቅረብ አልፈልግም፡፡ ባልየውም እንዲህ አላትእንግዲያው ትልቁን ነጭ በሬዬን አርደን እናበላቸዋለን፡፡ እናም ባልየው ትልቁን በሬ ከአንድ ዛፍ ስር ወስዶ በትልቅ ቢላዋ ያርደው ጀመር፡፡ ልጁም በጣም ተበሳጭቶ ሳለ ወደ አባቱ ዘንድ ሲሄድ አባትየው የበሬውን ስጋ ቆራርጦ ጨርሶ ልጁን ስጋውን ለእንግዶች እንዲያደርስ ያዘዋል፡፡ ልጁም ስጋውን ይዞ ወደ ቤት በመመለስ ላይ ሳለ በመንገዱ ላይ ባገኛቸው ድንጋዮች በእያንዳንዳቸው ላይ አንድ የስጋ ቁራጭ እያስቀመጠ ያልፍ ጀመር፡፡ ይህንንም እያደረገ እንግዶቹ ድረስ ዘለቀ፡፡ አባትየውም የስጋውን ቁራጭ በየድንጋዩ ላይ ባየ ጊዜልጄ ምን ነካው?” ብሎ አሰበ፡፡ በአንድ እጁ ቢላዋውን እንደያዘ በሌላኛው እጁ ጎንበስ እያለ የስጋውን ቁራጮች እየሰበሰበ ልጁን ይከተለው ጀመር፡፡ ልጁ ወደ እንግዶቹ እየሮጠ በሄደ ጊዜ የእናቱ ወዳጅ እንዲህ ብሎ ጠየቀውአባትህ ምን እያደረገ ነው?” ልጁምአትመለከትም? ሳንጃውን ወድሮና ድንጋይ እየለቀመ ወደ እኛ እየመጣ ነው፡፡ ከእናቴ ጋር ያለህን ድብቅ ወዳጅነት ስለደረሰበት ሊገድልህ እየመጣ ነው፡፡አለው፡፡ ሰውየውና እንግዶቹም ተነስተው መሮጥ ጀመሩ፡፡ አባትየውም ተከትሎ ሊያስቆማቸው ሞከረ፡፡ በዚህ ጊዜ ልጁ ወደ እናቱ ሲሄድ እናቱይህ ሁሉ ብጥብጥ ምንድነው?” ብላ ጠየቀችው፡፡ ልጁም እንዲህ ሲል መለሰአባቴ ያንቺንና የወዳጅሽን ድብቅ ፍቅር ስለደረሰበት ወዳጅሽን በድንጋይ ሊደበድበው እያሳደደው ነው፡፡ ከዚያም ወደ ቤት ተመልሶ ጉሮሮሽን ይቆርጠዋል፡፡ በዚህ ጊዜ እናትየው በጣም ደንግጣ ወደ እናትዋ ቤት መሮጥ ጀመረች፡፡ አባትየውም እንግዶቹ ላይ እንደማይደርስባቸው ባወቀ ጊዜ ልጁን ጠርቶምን እየተካሄደ ነው?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ልጁምእናቴ ያንተንና የገረድዋን ድብቅ ፍቅር ስለደረሰችበት ለእናትዋ ልትነግር እየሮጠች ነው፡፡ይለዋል፡፡ አባትየውም ከኋላ ከኋላዋ እየሮጠእባክሽ፣ እባክሽ በፈጣሪ ስም ለእናትሽ አንዳችም ነገር እንዳትነግሪያትእያለ ይማፀናት ጀመር፡፡ ሚስቱም እየተከተላት መሆኑን ስታውቅ ሩጫዋን ቀጠለች፡፡እባክህ አትግደለኝ፣ ጉሮሮዬንም አትቁረጠውእያለች ትለምነው ጀመር፡፡ ልጁም ተከትሏቸው ይሮጥ ነበር፡፡ ሁለቱም ከሚስትየው እናት ቤት እኩል ደረሱ፡፡ እናትየውም ሚስትየዋን ተመልክተውምን ሆነሻል?” ብለው ጠየቋት፡፡ እሷምልነግርሽ አልችልም፡፡ ልነግርሽ አልችልም፣ ምክንያቱም ልጄ ያውቀዋል፡፡አለቻቸው፡፡እናትየው ወደ አማቻቸው ዞር ብለውአንተስ ምን ሆነሃል?” ብለው ጠየቁት፡፡እሱምእኔም ልነግሮዎት አልችልም፡፡ ምክንያቱን የሚያውቀው ልጄ ብቻ ነው፡፡አላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ልጁ ይደርስናችግር የለውም፤ ወደቤታችን እንመለስና ችግሩን እኔ እፈታዋለሁ፡፡አላቸው፡፡ ከቤት እንደደረሱም ልጁ ሁለቱን ለየብቻ እየጠራ በማነጋገር አባትየውንከዚህ በኋላ ድርጊትህን የምታቆም ከሆነ እናቴ ልትምርህ ፈቃደኛ ነች፡፡አለው፡፡ ከዚያም ወደ እናትየው ሄዶከዚህ በኋላ ድርጊትሽን የምታቆሚ ከሆነ አባቴ ሊምርሽ ፈቃደኛ ነው፡፡አላት፡፡ በዚህ ሁኔታ ሁለቱም አንዱ የሌላውን ያለመታመን ምስጢር ሳያውቅ በደስታ መኖር ጀመሩ፡፡ ይህ ታሪክ ብልህ ልጅ የቤተሰቡ ኩራት መሆን እንደሚችል ያሳያል፡፡
ተረቴን መልሱ አፌን በዳቦ አብሱ፡፡

No comments:

Post a Comment