Thursday, December 31, 2015

“ትርጉሙን የማላውቀው ህይወት በ___ብር”

የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በዓል ማግስት ምሽት የባቡሩን መንገድ ተከትዬ ከሜክሲኮ ወደ ቡናና ሻይ እያዘገምሁ ነው፡፡ በአካባቢው የመኪና፣ የሰውና የባቡር ድምፅ ነግሷል፡፡ ቡናና ሻይ አካባቢ ስደርስ አንድ ተባራሪ መፅሐፍ ነጋዴ….

“ትርጉሙን የማላውቀው መፅሃፍ በ 20 ብር….”
“ትርጉሙን የማላውቀው መፅሃፍ በ 20 ብር…..”

እያለ አልፎ ሂያጁን ይጣራል፡፡ ወደ ቦሌና ወደ አራ ኪሎ የሚሄድ ታክሲ ፈላጊ ልጁን ገረፍ አድርጎት ፈገግ ብሎ ያልፋል፡፡

እኔ ትንሽ ቆም ብዬ መፅሀፎችን ገረፍኋቸው፡፡ ነገር ግን ከፅሁፋቸው መብዛት የተነሳ ርዕሳቸውን በደንብ ማስታወስ አልቻልኩም፡፡ የተፃፉት ግን በእንግሊዝኛ ነው፡፡ የማንበብም የመግዛትም ሙድ ውስጥ ስላልነበርሁ እኔም ገረፍ አድርጌው ሄድሁ፡፡

Monday, December 28, 2015

“ቱቦ አትሁኑ…ቱቦ አትሁኑ…”


“ልጆቼ ቱቦ አትሁኑ፡፡ ቱቦ ባዶ ነው፡፡ የሚይዘው ነገር የለም፡፡ ማስተላለፍ እንጂ መያዝ አይችልም፡፡ ቱቦ ካልሰጡት በራሱ የሚያመነጨውና የሚያስተላልፈው ነገር የለም፡፡ ቱቦ ሁሌም ጥገኛ ነው፡፡ ልጆቼ ቱቦ አትሁኑ፡፡ቱቦ አትሁኑ፡፡ ልጆቼ መተላለፊያ አትሁኑ፡፡”
ይህ ንግግር በአንድ ወቅት አንድ አባት የተናገሩት ነው፡፡ በወቅቱ ንግግራቸውን ከቁብ አልቆጠርሁትም፡፡ ሌሎቹም እንደዚሁ፡፡ ምክንያቱም ሰው እራሱ ቱቦ ነው፤ በአፉ አስገብቶ በ ‘እንትኑ’ የሚተፋ የምግብና የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦ፡፡ ከዚህ ያለፈ ሰውን ከቱቦ ጋር ሊያመሳስለው የሚችል አንዳች ነገር በጊዜው አልታየኝም፡፡ ይህ ደግሞ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ስለዚህ በጊዜው ሀሳባቸውን ውድቅ አደረግሁት፡፡ መብቴ ነው መቀበልም አለመቀብልም (አንቀፅ---)፡፡

Thursday, December 17, 2015

እኔ ምለው……

 ያልበላሽን አከሽ ባመጣሽው ጣጣ
የታከከው ሳይሽር ያልታከከው ወጣ”.....
የምትል የኩርፊያ ግጥም ለዚያች እከክ አካኪ ልፅፍላት ፈልጌ ነበር፡፡ ማከኩን ላታቆም ምን አስለፈለፈኝ ብዬ ከራሴ ጋር ስሟገት ያበደ ነፋስ ሃሳቤን በተነው፡፡ ይገርማል ነፋስ የሚበትነው ሃሳብ ተሸክሜ የምጓዝ ከንቱ ፍጡር መሆኔን አላውቅም ነበር፡፡ በነፋስ የሚመራ የነፋስ ትውልድ አካል! ኧረ መፈላሰፍ! የሰው ልጅ ከነፋስ አይደል እንዴ የተሰራው፡፡ ነፋስነቴን ልክድ ነው እንዴ! ቢሆንም ቢሆንም……ነፋስነታችንና መሬትነታችን ሚዛን ደፋ ወዳጄ! እሳትና ውሃ የት ሄዱ?

Sunday, December 13, 2015

እያነቡ እስክስታ....

       “የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ
        ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትም አልወጣ”
………ጥርስ ከምላስ፣ እጅ ከእግር፣ አይን ከጆሮ፣ ህሊና ከእውነት የከረረ ጥላቻና ጦርነት ውስጥ የገቡበት እኩይ ዘመን ላይ ደርሶ “የገደለው ባልሽ……” ብሎ መተረት ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡ ምን አልባት እንዲህ ብለን ብንተርት የተሻለ ይመስለኛል::
     “የገደለው ግራሽ የሞተው ቀኝ አጅሽ
      ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከራስሽ አልወጣ”
ከታሪክ ማኅደር
የቅርብ ታሪካችንን በጨረፍታ የኋሊት ስንመለከት በተለይ በደርግና በሻቢያ መካከል ናቅፋ ተራራ ላይ በተደረገው አስቀያሚ ጦርነት ብዙ ጀግና የኢትዮጵያ ልጆች ባሩድ እያሸተቱ ላይመለሱ የጥይት ራት ሁነዋል፡፡ በዚህ ጦርነት ከተከሰቱትና ታሪክ ከማይረሳቸው ሁነቶች መካከል በስጋ የአንድ እናት ልጆች በተቃራኒ ተሰልፈው የተረፈረፉበት ጦርነት መሆኑ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በወታደራዊው መንግስትና ጎን ለጎን በተፈለፈሉት የነፃነት ታጋዮች መካከል በተፈጠሩ የርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች ምክንያት ኢትዮጵያን አንድ እርምጃ ወደፊት ሊያራምዱ የሚችሉ ትውልዶች
      “ፋኖ ተሰማራ ፋኖ ተሰማራ
       አንደ ሆቺ ሚኒ አንደ ቼ ጉቬራ”፣ 
እያሉ እርስ በርስ እየተጠላለፉ እሳት ውስጥ ገብተው ላይመለሱ አሸልበዋል፡፡

Friday, November 20, 2015

UNDERSTANDING RISK & FINANCE

Let me greet you first with this Poem:
<<Risk @ Crazy Tomorrow>>
We are in the hands of disaster 
Tomorrow is crazy as ever
We are creating millions of sin
Full of problems up and down
Whatever comes whatever gone
                                                Drink the waste of life as you gain
                                                you can't go back once you are born!
                                                Thus go and forecast the risk
                                                To have a light in the dark
                         [Zelalem T; AU, Addis Ababa, Ethiopia; Nov 19, 2015]
The International conference on "Building financial resilience of African nations and communities to climate and disaster risks" started on Nov 17, 2015 and end up on Nov 20, 2015 at the AU headquarters.

Tuesday, November 17, 2015

ለምን አታገቢም? (ክፍል-03)

         

                                       …
ካለፈው የቀጠለ
ምንም እንኳ ስንኞቹን እግር በእግር ባላስታውሳቸውም፤ ከሚከተለው ግጥም ጋር ተመሳሳይ ፍሬ ሃሳብ ያለው ዘፈን ሰምቼ አውቃለሁ፡፡
አግቢ ይሻልሻል ቶሎ ተሞሸሪ
እህትሽ ስትዳር ቁመሽ እንዳትቀሪ
ሴቶች ለምን ቶሎ አያገቡም? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የግድ ሴት መሆን አያሻም፡፡ ካየነው፣ ከሰማነው፣ ከታዘብነው፣ ከተማርነውና ካነበብነው በማንኪያ እየጨለፍን ዘርፈ-ትንሽ የሆኑ ምክንያቶችን ከመጥቀስ ማን ይከለክለናል? ሴቶቹ ስለእኛ ለመፃፍ የኛ ፍቃድ ያስፈልግሃል ካላችሁ፤ በፌደራል ፖሊሳዊ ሰላምታ እጂ ነስቻለሁ (ፌደራል ሲነሳ እንዳትበረግጉ)፡፡ ተፈቅዷል….እሺ ልቀጥል!
ከጎኖችህ አጥንት ሔዋን ሳትፈጠር
አዳም ሆይ ህይወትህ ምን ይመስል ነበር?”

Thursday, November 5, 2015

ለምን አታገባም? (ክፍል-02)

እንደምን አላችሁ፡ እስኪ ወጋችንን እንጠርቅ፡፡ ወጋችንን ያቆምነው 45 ዓመቱ ጓደኛዬ ላይ ነው፡፡                                            ልቀጥል……

ምነው ጋሸ ነገር እምቢ አለህ እንዴ?
ኧረ!…..አንተ!……እሱማ…………ጥዋት ጥዋት የአባቴን ጎራዴ እየመሰለ እያስቸገረኝ ነውአለ ደስ በሚል ፈገግታ፡፡ ደሃ ፈገግ ሲል እንዴት ደስ ይላል መሰላችሁ፡፡
ቀላል አልሳቅሁም፡፡ ምንም እንኳጥዋት ጥዋትየሚሉት ቃላት ባይዋጡልኝም፤ ሌላ ጊዜስ ብዬ ለመጠየቅ ግን ድፍረቱን አጣሁ፡፡
ያም ሆነ ይህ ጎራዴ መምሰሉ የስሜት ይሁን የሽንት ባይታወቅም፤ የጓደኛዬ መልስ ወንዶቹ እስከ 45 ዓመት ድረስ ጥሩ ተስፋ እንዳላቸው የሚያበስር ነው፡፡
ታዲያ ለምን አታገባም፣ እንዴት ለአንተ የምትሆን ሴት ታጣለህ?
ኧረ እሱስ አላጣሁም፡ እኔ ምመጥናት ሴት አትገኝም ነው እንጂ?”
ምን ማለት ነው እሰኪ አብራራልኝ?

Saturday, October 24, 2015

“የእኔና የአንቺ ዓለም”

ለአንዱ ማግኘት ጣጣ 
ከውስኪ ሰገነት ስካር ላይ ሲወጣ
ለአንዱ ማጣት ዕዳ
ኑሮና ህይወቱ የቆሻሻ ገንዳ፤
አንዱ ጉልበተኛ የተጣላ ከእግዜር
ሰውን እንደ ሽንኩርት በስለት ሚመትር
ሌላው እረሃብተኛ
አገጩን ጭኑ ላይ ደግፎ የተኛ፤
አንዳንዱ ቄንጠኛ
በልዑል ሰገነት ልጁን የሚያስተኛ
ሌላው ዕድለቢስ
ከመላጣ እስፋልት ላይ በውርጭ የሚጠበስ፤
እዚያ ዲሞክራሲ 
ነፃነት በኬሻ ሁሉም ሰው ሃያሲ
እዚ አውቶክራሲ
ትንሽ ሰው ደራሲ፣ እራሱ ሃያሲ፤
ማዶ ቀዝቃዛ ብርድ 
የበረዶ ክምር ሰውነት የሚያርድ
ወዲህ የእሳት ምድር 
ጠብታ አልባ መሬት የሚያቃጥል ሐሩር፤
ይች ናት እንግዲህ…………
እግዜሩ ሲፈጥር መከራ ያየባት
በነጭ ወረቀት ላይ እርሳስ የነደፋት፤
ከእሱ ተቀብሎ ምድራዊው ፈላስፋ
የብዕሩን ቀለም ምራቅ እየተፋ፤
አጥፍቶ የሳላት በዥንጉርጉር ቀለም
ይች ናት እንግዲህ የእኔና የአንቺ ዓለም
!
          [ዘላለምየእናቱ ልጅ]

          ጥቅምት 11፣ 2007 ዓ.ም

Wednesday, October 21, 2015

'የሰንደቅዓላማ ቀን'ን…በበርጫ

(ከ'አጠቃ'ዎች አንደበት)

ከሆነ ሰፈር ወደ ፒያሳ እየሄድሁ ነው፡፡ አቤት እነዚህ እረዳቶች ደግሞ….ሳንቲም ጨምር….ጠጋ በልየዕቃ ይህን ያክል ትከፍላለህ….ከዚይ ላይ አይቆምም! አሁን አሁን ታክሲ ውስጥ ያለው ጭቅጭቅ ስለመመረረኝ፤ ቅርብ ከሆነ በሁለት አግሬ ማቅጠን ጀምሬአለሁ፡፡ ራቅ ካለብኝ ደግሞ ጆሮዬ ውስጥ የምጨምረው ጥጥ ይዞ መግባት ጀመርሁ፡፡ ታዲያ ዛሬም እንደተለመደው እርዳቱ እንደ ሐምሌ መብረቅ ተሳፋሪ ላይ መጮህ ሲጀምር ቶሎ ብዬ መከላከያ ጋሻዬን ጆሮዬ ውሰጥ ሰካሁ፡፡ ምን ላድርግ ጆሮዬ ገና ብዙ ክፉ ደግ መስማት አለባት-ቢጠቅማትም ባይጠቅማትም፡፡ ታዲያ በዚህ መሃል ፀጉሩን እንደ ደረቀ ተክል ቅርንጫፍ ያንጨበረረ አንድ ወጣት ከጎኔ መጦ ቁጭ አለ፡፡ በአካል ጠጋ አልሁለት-ሶስተኛ መሆኑ ነው፡፡ በሃሳብ መጠጋጋት ግን በአካል እንደ መጠጋጋት ቀላል አይደልም፡፡ አይገርምም! በአካል እንደምንጠጋጋው በሃሳብም ብንጠጋጋ ምን አይነት ኢትዮጵያ ትፈጠር ነበር? ተውት በቃ፡፡ ይቅርታ ወደ ልጁ ልመለስ፡፡ ታክሲው በአንዴ ከህዝባዊ ሽታ ወደ ጫትና ሲጋራ ማዓዛ ተለወጠ፡፡ ደግሞ ጫትና ሲጋራ ሲቀላቀሉ እንዴት ነው የሚሸቱት!