Sunday, December 13, 2015

እያነቡ እስክስታ....

       “የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ
        ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትም አልወጣ”
………ጥርስ ከምላስ፣ እጅ ከእግር፣ አይን ከጆሮ፣ ህሊና ከእውነት የከረረ ጥላቻና ጦርነት ውስጥ የገቡበት እኩይ ዘመን ላይ ደርሶ “የገደለው ባልሽ……” ብሎ መተረት ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡ ምን አልባት እንዲህ ብለን ብንተርት የተሻለ ይመስለኛል::
     “የገደለው ግራሽ የሞተው ቀኝ አጅሽ
      ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከራስሽ አልወጣ”
ከታሪክ ማኅደር
የቅርብ ታሪካችንን በጨረፍታ የኋሊት ስንመለከት በተለይ በደርግና በሻቢያ መካከል ናቅፋ ተራራ ላይ በተደረገው አስቀያሚ ጦርነት ብዙ ጀግና የኢትዮጵያ ልጆች ባሩድ እያሸተቱ ላይመለሱ የጥይት ራት ሁነዋል፡፡ በዚህ ጦርነት ከተከሰቱትና ታሪክ ከማይረሳቸው ሁነቶች መካከል በስጋ የአንድ እናት ልጆች በተቃራኒ ተሰልፈው የተረፈረፉበት ጦርነት መሆኑ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በወታደራዊው መንግስትና ጎን ለጎን በተፈለፈሉት የነፃነት ታጋዮች መካከል በተፈጠሩ የርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች ምክንያት ኢትዮጵያን አንድ እርምጃ ወደፊት ሊያራምዱ የሚችሉ ትውልዶች
      “ፋኖ ተሰማራ ፋኖ ተሰማራ
       አንደ ሆቺ ሚኒ አንደ ቼ ጉቬራ”፣ 
እያሉ እርስ በርስ እየተጠላለፉ እሳት ውስጥ ገብተው ላይመለሱ አሸልበዋል፡፡
በጠራራ ፀሐይ ከእናቱ ጓሮ ገሎ ለገደለበት ጥይት ዋጋ ተቀብሎ “የፍየል ወጠጤ……….”ን እያዘፈነ ከህዝብ ህሊና በላይ የሆነው ወታደራዊው መንግስትም በህዝብ ብሶት እንደ በጋ ደመና በአንድ ቀን ተገፎ ከምድረ አቢሲኒያ ጠፍቷል፡፡ በግብራቸው ተደስተው በሰዓቱ እስክስታ የወረዱት ሁሉ ጊዜው ሲያልፍ የቁጭት እንባ ማንባታቸውን ታሪክ በትዝብት ከትቦት ያለፈው ሃቅ ነው፡፡ ይሄ ነው እንግዲህ እያነቡ እስክስታ-የመከራ ደስታ፡፡ ከዚህ ሁሉ የታሪክ ውጥንቅጥ ግን ሀገሪቱ ያጣችው እንጂ ለመጪው ትውልድ ያተረፈችው ሚዛን የሚደፋ የተስፋ ዳቦ እንኳ አንደሌለ ለማወቅ ምስክር አያሻም፡፡
ከትናንት ታሪክ ለነገ
ታሪክ መጥፎም ይሁን ጥሩ ከፍ ብሎና ጎልቶ መታየት ያለበት አስተማሪነቱ ነው፡፡ መልካሙን ታሪክ ነገ እንዴት እናሳድገው፣ መጥፎውን ታሪክ እንዳይደገም እንዴት እናሻሽለው ብለን ከትናንት ታሪክ ካልተማርን….ታዋቂው የማህበረሰብ ፈላስፋ ካርል ማርክስ ታሪክ ራሱን ደገመ፣ መጀመሪያ አሳዛኝ ቀጥሎ ቧልት በሚመስል መንገድ” ብሎ እንደተናገረው የኛም ታሪክ እራሱን ከመድገም ወደኋላ አይልም፡፡ ታሪክን ከስሜታዊነት፣ ከግብዝነት ና ከበቀል ነፃ በሆነና በሰከነ አዕምሮ መገንዘብና መተንተን ያሰፈልጋል፡፡ ታሪክን ከትምህርትነት ባለፈ ለበቀልነት ቢጠቀሙበት ኑሮ በአይሁዶችና በጀርመኖች፣ በአሜሪካኖችና በጃፓኖች መካከል የማያባራ ጦርነት ዛሬ ላይ በኖረ ነበር፡፡ ታሪክን አንደመሳሪያ በመጠቀም ድክመትን ለመሸፈን መሞከር ደግሞ በአንፃሩ ትውልድን ከማክሰምና መፃኢ ተስፋን ከማጨለም ያለፈ የረባ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ አመንም አላመንም የዛሬው ትውልድ ዛሬ ለሰራው ስራ እንጂ ትናንት አያቶቹና ቅድመ አያቶቹ ላጠፉት ጥፋት ተጠያቂ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ ነገር ግን የሰሩትን ጥፋት የማከምና መልካም ስራቸውን አጉልቶ የመዘከር ኋላፊነት አለበት፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን በየቦታው እየሄዱ ፈሰስ መቅደድ ፍሜው መሬቱን በጎርፍ ማስበላት ነው፡፡

ተማርን በሚል አጉል መኮፈስ አንድ እርምጃ እንኳ ወደፊት ተራምዶ ማሰብ የማይችል ጭንቅላት ተሸክመን ከእኛ በተሻለ ሁለት ሶስት እርምጃ ወደፊትና ወደኋላ ተራምዶ ማሰብ የሚችለውን የኢትዮጵያን ገበሬ አብረን እሳት ውስጥ እየገመድነው ነው፡፡ እነሆ እንደ ዋዛ የተረተው “የተማረ ይግደለኝ…..” የሚለው ተረት እውን እየሆነለት ነው፡፡ ይህ ህዝብ የዕርስ በርስ ሽኩቻውን ወደ ጎን ትቶ ለዘመናት ለሃገር ሉዓላዊነት በተባበረ ክንድ ደሙን ሲያፈስ አጥንቱን ሲከሰክስ የኖረ ህዝብ ነው፡፡ ይህ ህዝብ ምንም እንኳ በዘመናዊ ትምህርትና ስልጣኔ እዚህ ግባ የሚባል እርምጃ ባይራመድም ከአባቶቹ የተረከበውን ጥንታዊ ስልጣኔና ያልተበረዘ አኩሪ ባህል ከነሙሉ ታሪኩ እዚህ አድርሷል፡፡ ታዲያ ይህ ህዝብ በተደጋጋሚ የሚታወቅበት አንድ ባህሪ አለው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ካመረረ፣ በግ ከበረረ መመለሻ የለውም፡፡ ይህን ሃቅ መታገል ደግሞ እዳው ገብስ ነው፡፡ ስለዚህ መንግስትም፣ ወጣቱም፣ ተቃዋሚዎችም፣ ማዶ ሁነው እሳት የሚለኩሱና የሚያራግቡ ዲያስፖራዎችም ቆም ብለው በሰከነ አእምሮ መጪውን የህዝብና የነገ ትውልድ ዕጣ ፈንታ ማገናዘብ አለባቸው፡፡ የአንድ ትውልድ አርቆ አሳቢነትና አስተዋይነት የሚለካው ቢያንስ አንድ ትውልድ ወደፊት ሄዶ ማሰብ ሲችል ነው፡፡ አንድ የሚያደርጉንን ነገሮች ጨፍልቀን የሚለያዩንን እያጎላን ከሄድን ስለነገው ትውልድ አይደለም ስለራሳችን ማሰብ እንደ ብረት አሎሎ የከበድ ሸክም ይሆናል፡፡

ውሃ በቀጠን የሚፈጠሩት የእርስ በእርስ አምባጓሮዎች የትውልዱን ህልም ከማጨለም ያለፈ የረባ ታሪክ አይኖራቸውም፡፡ ያለነው በ21 ኛው መቶ ክ/ዘመን እንደመሆኑ መጠን ከእጃችን ይልቅ ሃሳባችንና ንግግራችን እንዲቀድም ማድረግ የአንድ የሰለጠነና ሰብዓዊ የሆነ ማህበረሰብ መገለጫ መሆኑንም መዘንጋት የለብንም፡፡ ግራ እጃችን ቀኝ እጃችንን ሲቆርጠው ትናንትም ነገም የሚመነምነው አካላችን እንደሆነ ሁሉም የሚያምነው ሃቅ ነው፡፡ ከራስ ጥቅም አልፎ ስለመጪው ዘመን ማሰብ በታሪክና በመጪው ትውልድ ዘንድ በመልካም የመነሳት እድልን ይጨምራል፡፡ ከዚህ ያለፈ በዚህ ምድር የሚቀር ነገር የለም፡፡ የበላም ያልበላም፣ የጠጣም ያልጠጣም፣ መሪም ተመሪም፣ ገዥም ተገዥም፣ ደሃም ሃብታምም፣ አለቃም ጭፍራም ሁሉም ያልፋሉ፡፡ ይህ አነጋገሬ የዋህነት የተሞላበት ቢመስልም በንፁህ ህሊናና በሰብዓዊነት መነፅር ላየው ደረቅ ሃቅ ነው፡፡ ሁላችንም እናልፋለን-ከነግብራችን፡፡ በዚህ ምድር የሚቀረው ግን ስማችንና ስራችን ነው፡፡ ስለዚህ ቢያንስ በዚህ ሰዓት ሁላችንም ቆም ብለን ነገን በማሰብ ከወረስነው ቂም ላይ የራሳችንን ቂም ቀላቅለን በጥጓ ከመጋት ይልቅ ንፁህ ፍቅርን ለመጪው ትውልድ ለማውረስ እንዘጋጅ፡፡ ማንም ምንም ቢሆን ሰው ነው፡፡
ክብር ለሰብዓዊነት!
ሁሉም ያልፋል ፍቅር ያሸንፋል!


1 comment:

  1. ክብር ለሰብዓዊነት!
    ሁሉም ያልፋል ፍቅር ያሸንፋል!

    ReplyDelete