Thursday, December 31, 2015

“ትርጉሙን የማላውቀው ህይወት በ___ብር”

የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በዓል ማግስት ምሽት የባቡሩን መንገድ ተከትዬ ከሜክሲኮ ወደ ቡናና ሻይ እያዘገምሁ ነው፡፡ በአካባቢው የመኪና፣ የሰውና የባቡር ድምፅ ነግሷል፡፡ ቡናና ሻይ አካባቢ ስደርስ አንድ ተባራሪ መፅሐፍ ነጋዴ….

“ትርጉሙን የማላውቀው መፅሃፍ በ 20 ብር….”
“ትርጉሙን የማላውቀው መፅሃፍ በ 20 ብር…..”

እያለ አልፎ ሂያጁን ይጣራል፡፡ ወደ ቦሌና ወደ አራ ኪሎ የሚሄድ ታክሲ ፈላጊ ልጁን ገረፍ አድርጎት ፈገግ ብሎ ያልፋል፡፡

እኔ ትንሽ ቆም ብዬ መፅሀፎችን ገረፍኋቸው፡፡ ነገር ግን ከፅሁፋቸው መብዛት የተነሳ ርዕሳቸውን በደንብ ማስታወስ አልቻልኩም፡፡ የተፃፉት ግን በእንግሊዝኛ ነው፡፡ የማንበብም የመግዛትም ሙድ ውስጥ ስላልነበርሁ እኔም ገረፍ አድርጌው ሄድሁ፡፡

“ትርጉሙን የማላውቀው መፅሃፍ በ 20 ብር….”
“ትርጉሙን የማላውቀው መፅሃፍ በ 20 ብር…..”
ተባራሪ ነጋዴው በአራቱም አቅጣጫ ጥቁር የለበሱ ፖሊሶችን እየተመለከተ፣ አልፎ አልፎም ሙሉ ጥቁር የለበሰ ሰው ሲመለከት ብትት ብትት እያል ቶሎ ቶሎ መጥራቱን ቀጥሏል (ኑሮ በመከራ)፡፡ እየራቅሁ ስሄድ የድምፁ መጠን ቢቀንስም እየተሰማኝ ነው፡፡ የዚህ ልጅ ጥሪ ግን መፅሐፉን ሳይሆን የ “ኑሯችንን ትርጉም አልባነት” የሚጣራ መልክተኛ አድርጎ ውስጤ ተቀበለው፡፡ በምላሹም ትርጉም የሌለው ኑሮ እየኖርኩ መሆኑ ትዝ አለኝ፡፡ እስኪ ንገሩኝ፤ የመኖር ትርጉሙ ምንድነው?
 “መብላት፣ መጠጣት፣ መስራት፣ መዳራት፣ መዝረፍ፣ መግዛት፣ መገዛት፣……?????”
ነው ወይስ፡ “ሃብት መሰብሰብ፣ ቤት መስራት፣ ስልጣን መያዝ……….?????”

የኑሮ ትርጉም ጠፍቶብኝ በፍለጋ ስዳክር…….ከሆነ አቅጣጫ የመጣ የአንጎል መልክት “ አትልፋ፣ እኛ ማለት የብዙ ነገሮችን ትርጉም ሳናውቅ አምነንና ተቀብለን የምኖር ፍጡሮች ነን” ብሎ ለውስጤ ሹክ ሲለው ከፍለጋዬ ወጣሁ፡፡ አይገርምም ሳይገባን ተቀብለን መኖር ብቻ አይደለም ሳይገባን ገልብጠን የራሳችን ያረግናቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉም ትዝ አለኝ፡፡ ትርጉማቸው ሳይገባን ገልብጠን በምላሹ እየተገለበጥን መሆናችንን ሳስበው ደግሞ አልቅስ አልቅስ አለኝ (ኧረ አላለቅስም ለማን ደስ ይበለው ብዬ)፡፡ ምን ያልገለበጥነው ነገር አለ፡፡

ለምሳሌ፡ የአውሮፓን ባህል ሳይገባን ገልብጠን፤ ሱሪ ዝቅ አደረግን፣ ጡት ገልጠን ለበስን፣ ሎቲ አንጠለጠልን፣ ፀጉራችንን አንጨበረርን፣ ግብረ ምናምን ውሰጥ ተዘፈቅን፣…..ወዘተረፈ…..
ምን ይሄ ብቻ፡ ህጋችን፣ ፖሊሲያችን፣ ደንባችን፣ መመሪያችን ከየት ነው የመጣው፡፡ መገልበጡ ሃጢያት ወይም ወንጀል አይደለም ግን የገለበጥነው ነገር ገብቶናል ወይ ነው ጥያቄው????
የአንድ አገር ባህል፣ ፖሊሲና መመሪያ ሲገለበጥስ ወደ ሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ሳይገናዘብና ሳይሸሻል በቀጥታ መገልበጥ አለበት ወይ???

“በቀጥታ” የሚለውን ቃል ሳነሳ ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ፣ በአንድ ወቅት ነፍሳቸውን ይማረውና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር (የቀድሞው ለማለት በእርግጥ ይከብዳል) ስለ አሸባሪነት አዋጁ ሲናገሩ ፤ “ይህን ህግ በዓለም ላይ የተሻለ ከሚባለው ከአሜሪካ የአሸባሪነት ህግ ላይ በቀጥታ ነው የገለበጥነው” ብለው ነበር፡፡

እነሆ መገልበጥ ባህላችን ሆነና ተማሪው ፈተና መስራት ቢያቅተው የጓደኛውን ስም ገልብጦ ይሰጣል፣ ግማሹ መንግስት ለመገልበጥ ያሴራል፣ ግማሹ የአለቃውን ንዴት ለመወጣት ማታ ገብቶ ሚስቱን ይገለብጣል፣ ሌላው ራሱን ከፎቅ ገልብጦ ይጥላል፣ አንድ ሐሙስ የቀረው ደግሞ ልብሱን ገልብጦ ይለብሳል፣ መሬትና ቤት ሻጭ በሳምንቱ ይገለብጣል፣ መገልበጥ …..መገልበጥ….መገልበጥ……፡፡
እኔ ምለው……… ኑሮ ማለት ትርጉሙ መገለባበጥ ነው እንዴ?????.....እከከከከከከ.. “ያልተገላበጠ ያራል” የምንለው ለዚህ ነው እንዴ???

ግን ግን……..ከመገልበጣችንና ከመገልበጣችን (ይጠብቃል) በፊት ለምን አንደምንገለብጥ ማሰብና ትርጉሙን ተንትኖ ማወቅ መቅደም ያለበት አይመስላችሁም??????? ነው እንደ መፅሐፍ ሻጩ “ትርፍ እናግኝበት እንጂ ትርጉሙን ባናውቀው ምን አገባን” ማለት ይሻላል፡፡ ገዢውስ??? የነገስ ትውልድ????
እኔ ምለው…………….በእውነት የእኛ ኑሮስ ትርጉሙ ምንድነው? ነው ወይስ እንደ መፅሐፍ ሻጩ ትርጉሙን አናውቀውም?????
          ትርጉሙን የማላውቀው ህይወት በ___________ብር እንዳትሉ አደራ!!!

                                    ሰናይ ጊዜ!

1 comment:

  1. “ አትልፋ፣ እኛ ማለት የብዙ ነገሮችን ትርጉም ሳናውቅ አምነንና ተቀብለን የምኖር ፍጡሮች ነን”

    ReplyDelete