Wednesday, July 22, 2015

ይድረስ ለባራክ ኦባማ

         Click for PDF
            
ይድረስ፡ ለ ባራክ ሁሴን ኦባማ ንጉሰ ነገስት ዘ አሜሪካ
            ተላከ፡ ከ ወጣት እርቅይሁን በላቸው ዘብሔረ ኢትዮጵያ
ኦቡየ እንዴት ነህ፡፡ አማረኛ ታነባለህ አይደል፡፡ መቼም በየጊዜው “ኋይት ሀውስ” የሚመጡት አበሾች አስጠንተውሃል ብለውኝ ነው፡፡ ሰማሁ ኦቡየ፣ ወሬ አይደበቅም፡፡ በእኛ ሀገር “ወሬን ተራራ አይጋርደውም” ተብሎ ይተረታል፡፡ በእናንተስ ኦቡየ ወሬን ፎቅ ምናምነ አይጋርደውም ትላላችሁ፡፡ እንዴው ለነገሩ እንጂ እናንተን ምንም አይጋርዳችሁ፡፡ እድሜ ለእነ….ይቀር ተወው፡፡ የራሳችንን ጉዳይ እንኳ እናንተ አላምጣችሁ ከተፋችሁት በኋላ ነው እኛ የምንሰማው፡፡ ኧረ ላንሰማም እንችላለን፡፡ ማለቴ ቴሌና መብራት ትንሽ አመም አድርጓቸው ከዋለ ካደረ ማለቴ ነው፡፡ ለመሆኑ ኢንተርኔት፣ ቴሌ፣ መብራት አሜሪካ እንዴት ነው? ማለቴ…. ይቅርታ ኦቡየ ገና በመግቢያ በነገር አደከምኩህ፡፡ አንተ ግን እንዴት ነህ፡፡ አቦ እናትህም አባትህም እንኳን ወለዱህ፡፡ ይህን 7 ቢሊዮን የዓለም ህዝብ ስምህን አስጠራኸው እኮ፣ ማለቴ ህፃናትም ሲያድጉ አንተን መጥራታቸው አይቀርም ብዬ ነው፡፡ በተለይ አፍሪካ! የአንተ መምጣት እኮ አንደ ምፃት ቀን፣ እንደ መሲህ ምናምን ነው እየታየ ያለው፡፡ አቦ ናልን አሜሪካዊው የዓለም መሲህ! እንኳን ወደዚች ታሪካዊ፣ የተቀደሰችና እንግዳ ተቀባይ ወደ ሆነች አገራችን በሰላም መጣህ፡፡ 


አይዞህ አቡየ ድሆችን ስታይ እንዳደነግጥ፡፡ አንደናንተ የህንፃና የገንዘብ ሀብታም ባንሆንም፤ የህሊና ደሃ ግን አይደለንም፡፡ እናንተ የህሊና ደሃ ናችሁ አላልሁም፡፡ ቅኔ ስለማችል ቅኔ አልዘርፍብህም፣ አማርኛ ከቻልህ ይበቃሃል፡፡ ስላንተ የተዘረፈውን ቅኔ አስፈትቼ ሌላ ጊዜ እልክልሃለሁ፡፡ ኦቡየ አድናቂህ ነኝ፡፡ የመጀመሪያው ጥቁር የአሜሪካ ንጉሰ ነገስት፤ ይቻላል ብለህ ተነስተህ የዘረኝነትን ቀንበር በመስበር ጥቁር መሪ መሆን ስለቻልህ አድናቂህ ነኝ፡፡ ነገር ግን “ይቻላል” የምትለዋን ቃል ከየት አመጣሃት፡፡ ከእኛው ከ ሻለቃ ሃይሌ ከሆነ የወሰድሃት በ “ፓተንት ራይት” ህግ መሰረት ተቀጠህ በሻለቃ ጦር ተከበህ ቅሊንጦ መውረድህ አይቀርም፡፡ በዚያውም እነንተና እነንተና… እያሉ ሚዲያዎች ያሰለቹህን ሰዎች የእግዜር ሰላምታ ሰጥተሃቸው ትመለሳለህ፡፡ ዶላር ካልያዝህ የአሜሪካ መንግስት መጦ እስኪያስፈታህ ድረስ አንተም እዚያው የእጅ ስራ እየሰራህ ትቆያለህ፡፡ ፈራህ እንዴ ኦቡየ፡፡ አይዞህ! እናንተን ለጊዜው ካለ እግዜሩ የሚያሰጋችሁ ነገር የለም፡፡ እሱንም እኮ ተፈታተናችሁት! ማን ልቡ ያበጠ ተናግሯችሁ፡፡ ሌላው ዓለም ይቅበዝበዝ እንጂ! አውነቴን ነው፡፡ የእናንተ አባቶች በጊዜው ተቅበዝብዘው፤ እናንተን አቅበዝባዥ አድርገዋችኋል፡፡ የእኛ አባቶች እንኳ አልተቅበዘበዙም፡፡ ከፈለግህ ስለ አክሱም፣ ስለ አድዋ፣ ስለ “ክሎዝ ዶር ፖሊሲ”፣ ስለ ጋፋት ምናምን እተርክልሃለሁ፡፡ ምን ዋጋ አለው አባቶቻችን እኛን የመሰለ ተቅበዝባዥ ትውልድ ፈጠሩ፡፡ ፈረንጅን ከአገር እንዳላባረሩ፣ ዛሬ የነጭ ጫማ ዝቅ ብሎ የሚልስ ትውልድ ፈጠሩ፡፡ ትናንት እነሱ አፈራችንን አራግፋችሁ ውጡ እንዳልተባሉ፤ ዛሬ የእነሱ አሜካላ ማራገፊያ ሆንን፡፡ ወይ ነዶ አለ…ማን ነበር? ኦቡየ የተሁትን ነገር ነካክተህ አናደድከኝ፡፡ ኧረ ጨጓራም ተነሳብኝ፡፡ ምን ላድርግ ብለህ ነው፣ ሆድ ብሶኝ እኮ ነው ኦቡየ፡፡

ለመሆኑ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ምን አነሳሳህ ኦቡየ፡፡ በህልምህ ምን አየህ? አስፈታኸው? ምን አለህ ህልም ፈችው? ኢትዮጵያ አንተ ከጎበኘሃት ታድጋለች አለህ? ንገረኝ በሞቴ! ተወው አትንገረኝ፣ አውቀዋለሁ፡፡ እሺ መጠህ ምንድነው የምታደርገው ንገረኝ? ነው “የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ በድህነቷ የምትታወቀውን ምስራቅ አፍሪካዊቷን አገር ኢትዮጵያን ጎበኙ” በሚል አርዕስተ ዜና የዓለም መሳለቂያ ልታደርገን ነው፡፡ ነው ወይስ የተለመደውን “የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ስለ ዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር ተወያዩ” የሚለውን እንጨት እንጨት የሚል ዜና ልታሰማን ነው፡፡ እኔ ምለው ኦቡየ፣ መጎብኘት ብርቅ ነው እንዴ! የእኛ ንጉስ እኮ የአንተን አገር አሜሪካን ሲጎበኙ ኬነዲ እንደ አመት በዓል ስራ አዘግተው፤ ህዝቡን ጎዳና እንዲወጣ አድርገው ነው የተቀበሏቸው፡፡ አውነቴን ነው ሚስተር ፕሬዘዳንት! ካላመንከኝ የሚከተለውን ቪዲዮ ተመልከት፡ https://www.youtube.com/watch?v=xDI12q-TtHw
አየኸው ኦቡየ? እንዴት ነው? ለጠቅላላ እውቀት ይሆንሃል ብየ ነው፡፡ በኋላ ከዚህ መጠህ እራስህን እንዳታካብድ፡፡ የጃማይካውንም ከፈለግህ እየው፡https://www.youtube.com/watch?v=9Ao-EwzX0jY፡ ለማንኛውም ተስፋ ቁረጥ እኛ ስራም አናቆምም፣ ጎዳናም አንወጣም፡፡ አንውጣ ብንልም…..፣ ተውኩት! መብቴ ነው! የመናገር መብት እንዳለኝ ሁሉ ያለመናገር መብትም ያለኝ መሰለኝ፡፡ ማለቴ አንተ መጠህ እ እ እ፣ አሁንም ተውኩት!

እሺ ምንድነው የምታደርገው ንገረኝ? ባይሆን እህ ብለህ ስማኝና ምን ማድረግ እንዳለብህ እኔ ልንገርህ፡፡ ለአገሬ ሰው መድህኒቱ እህ ብሎ መስማት ነው፡፡ ኦቡየ! እህ ባትለኝም እቀጥላለሁ፡፡ እስኪ ከተለመደው የጉብኝት ስልት ውጣና ህዝብን ጎብኝ፡፡ መጀመሪያ እስኪ ወደ ገጠር ውጣና ህዝቡን ጎብኝ፡፡ ሐረር፣ ጋምቤላ፣ መቀሌ፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ጎጃም፣ ወለጋ፣ ባሌ ምናምን አልልህም፤ ከዚው ከአዲስ አባባ ትንሽ ወጣ ብለህ ህዝባችን እየው፡፡ ህዝባችንም ይይህ፡፡ በዚያውም እሸት ከደረሰ ወይም ጠቦት ካለ “አይ ስዎየር” የእኛ ገበሬዎች አይጨክኑም፡፡ ሌላው ቢቀር፣ ማር፣ ወተት፣ ቡና፣ ቆሎ ምናምን አይጠፋም፡፡ ከዚያ ስትመለስ ለተወሰኑ የመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞችና ነጋዴዎች ፊትህን አሳያቸው፡፡ ቀጥሎ ቦሌን ብቻ ሳይሆን አነ ጨርቆስን፣ እነ ጉለሌን፣ አነ መርካቶን ዞር ዞር ብልህ ጎብኝ፡፡ በዚያውም መሰረተ ልማታችንንም ኑሯችንንም አይተህ ፍርድህን ትሰጣለህ፡፡ ቢሮ ቁጭ ብሎ የተሰራ ቁጥር እየተቀበሉ አገሬን ማወደስና ማኮሰስ እጅ እጅ ብሎኛል፡፡ ምንድነው እጅ እጅ እንዳትለኝ፡፡ በነገራችን ላይ ሚስተር ፕሬዘዳንት የናይሮቢን ዩኒቨርሲቲ ጎበኘኸው፡፡ ተማሪዎች ካልጎበኘኸን አትክልቱ ላይ ሽንታችንን እንሸናለን ብለው አንገራገሩ አሉ፡፡ ወይኔ! አሳፍረው የነጭ መሳለቂያ አረጉህ፡፡ ይሄ ሼም ነው ፕሬዘዳንት! ለነገሩ አትዘን አፍሪካ በአትክልት ብቻ ሳይሆን በትውልድ ላይ የሚሸኑ ብዙ ወፈፌዎችን የያዘች አህጉር ናት፡፡ ታዲያ በነካ እጅህ ይሄን የኛውን አዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲንም አየት ብታደርገው ቅር ይልሃል? አይዞህ ከእኛ አገር ያሉ ተማሪዎች እንኳ አትክልት ላይ እንሽና ብለው አያንገራግሩም፡፡ ምክንያቱም ቀድመው ሸንተውበታል! ኧረ ይሄ ብቻ አይደልም አትክሉትን መከታ አርገው ያልሰሩት ምን አለ? ተወው ባክህ፣ ጉዳችንን በሆዳችን አለ ያገሬ ሰው፡፡ እኛው ጋ ተከድኖ ይብሰል! ከዚያ መልስ አፍሪካ ህብረት ህንፃ አረፍ በልና እስኪ እነዚህ ተቃዋሚ ነን ባዮችን ስማቸው፣ ማለቴ አውራቸው፡፡ ቻይና በሰራችው ቤት አልገባም ካልህ፣ የህንፃ ችግር የለብንም አታስብ፡፡ ከሻይ ቡናው በኋላ እስኪ ጋዜጠኞች ትንሽ ተቧጨቅ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ኦቡየ የመንግስት ባለስልጣናትንና የአፍሪካን መሪዎች ማግኘት፡፡ አሁን ተግባባን ኦቡየ፡፡ ገና ስታስበው ደከመህ ኦቡየ፡፡ ምን ላድርግ ብለህ ነው፤ ከእናንተ አገር የመሸገው መስከረም በቀለ ሳይቀር በአንተ ላይ ቀልዶ ሲያበቃ ሁሉንም ነገር ቸክድ ኢን ቸክድ አውትአድርገህ ብሎህ አል ነበር፡፡ ቀልዱ አልደረሰህም? በሞትኩት ይኸው ተመልከት፡ https://www.youtube.com/watch?v=gUxQjnT3jqo ለማንኛውም ቀልዱን አይተህ በጣም እንዳትስቅ፤ ፕሬዘዳንት ሲሳቀቅ እንጂ ሲስቅ አያምርበትም፡፡ ማታ ዘና ማለት ካስፈለገህ ደግሞ ወደ አንዱ አዝማሪ ቤት ጎራ በል፡፡ ለምሳሌ አንዱ ወፈፌ አዝማሪ እንዲህ ብሎ ሊገጥምልህ ይችላል፡
 የእኔ ሆድ ኦባማ…….ኦቡየ….እዝዝዝዝዘ  ኦቡነት…….እዝዝዝዝዝ…….አቧችን……..እዝዝዝዝ
የእኔ ሆድ ኦባማ የአማሪካው ንጉስ
ልጅህን ዳርልኝ ድል ባለ ድግስ፤
ብሎ የዱብዳ ጥያቄ እንደ ኬኒያው ገበሬ ሊያቀርብልህ ይችላል፡፡ ሌላኛው ተቀብሎ እንዲ ሊልህ ይችላል፡፡
የእኔ ሆድ ኦባማ…….ኦቡየ….እዝዝዝዝዘ  ኦቡነት…….እዝዝዝዝዝ…….አቧችን……..እዝዝዝዝ
አንተ የጥቁር ነጭ ጠይም ሸሞንሟና 
ዶላሩን ላክልን ሌላውን ተውና፤

ብሎህ እርፍ ሊል ይችላል፡፡ ለማንኛውም የሚሉህን መስማት ከፈለግህ ገብተህ መስማት ነው፡፡
እኔ ምለው ኦቡየ ከአንተ አገር ያሉ ምቀነኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ አትሂድ እያሉ ነው አሉ፡፡ ምናለበት የአንተን በረከት ብናገኝ ኦቡየ፡፡ ወይ ምቀነኛ አርፎ አይተኛ፡፡ ለማንኛውም አንተ አትስማቸው! ታድያ ኦቡየ አንድ ነገር ላስጠንቅቅህ፤ ጎብኝተህ እንደጨረስክ ከአገር ሳትወጣ ክፉ ነገር እንዳትናገር! ምክንያቱ ገብቶሃል አይደል? በቃኝ ጨረስኩ፡፡ ይቅርታ ኦቡየ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ስለ ግብረ ምናምን ትንፍሽ ካልክ፣ አንተን አያርገኝ ኦቡየ፡፡ ዝም ብለህ አምልጥ፡፡ ግብረ ሶዶም ምናምን፣ እሱን ጉዳይ ለእኛ ተወው እዛው እናንተ ተጨማለቁበት፡፡ ስልጣኔአችሁ ይህ ከሆነ ስልጣኔ በአፍንጫችን ይውጣ፡፡ ለማንኛውም ኦቡየ እህ ብለህ ስላዳመጥኸኝ እህ ብሎ የሚያዳምጥ ልጅ ይስጠህ፡፡ በል እንደለመድከው “ጋድ ፕሌስ ኢትዮጵያ” ብለህ ሂድ፡፡ ባትለንም አገራችን የተባረከች ናት፡፡ እናንተ ይሄ ምነው እሱ ዲያስፖራ፣ ላሜቦራ… ምናምን እየላካችሁ እያረከሳችሁን ነው እንጂ፡፡ ይቅርታ ዲያስፖራ ብራችሁ እንኳ ጠቅሞናል፣ እንትናችሁ ነው እንጂ፡፡ እኔም እልሃለሁ “ጋድ ሲ ዘ ሲን ኦፍ አሜሪካ ”፡፡  ቻው ኦቡየ በሰላም አያገናኘን፣ ማለቴ በዚያው በአንተው አውሮፕላን “ኤር ፎርስ ዋን” ይሻላል ብየ ነው፡፡

3 comments:

  1. ጥሩ እይታ!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!

    ReplyDelete
  2. ግብረ ሶዶም ምናምን፣ እሱን ጉዳይ ለእኛ ተወው እዛው እናንተ ተጨማለቁበት፡፡ ስልጣኔአችሁ ይህ ከሆነ ስልጣኔ በአፍንጫችን ይውጣ፡

    ReplyDelete