Monday, March 16, 2015

ጀግናው አርበኛ በላይ ዘለቀ (አባ ኮስትር) ክፍል -2


  በላይ ዘለቀና ምቀኞቹ  
መጋቢት 1933 .. ከበደ ተሰማ (ደጃዝማች )ወዳገራቸው ለመመለስ መንገድ ላይ ከነበሩት ንጉስ ተልከው መጡ ::ከሳቸው ጋር የነበረው ጀኔራል ሳንፎርድ በላይ ዘለቀን ለመጨበጥ እጁን ሲዘረጋ በላይ ዘለቀ "ለፈረንጅ እጄን አልሰጥም "ብለው ሳንፎርድን አግባቡት :: በሁዋላ ልጅ መርድ መንገሻና እንግሊዞች ወደ ደጀን መቱ ::ወደበላይ ዘለቀ ላኩባቸው ::ሄዱ ::"የደጀንን ምሽግ ለመስበር ተባበሩን "ተባለ :: "መድፍ ይዛችሁዋል ?ኤሮቢላ ይዛችሁዋል ?"አላቸው በላይ ዘለቀ :: "አልያዝንም ግን መክበብ ይበቃል "አሉት :: "አይበቃም "አላቸው ::"ከዚህ በፊት ወር ካስራ አምስት ቀን ሙሉ ሞክረን ብዙ ወንድሞቼ አልቀዋል ::መድፍና ኤሮብላ አምጡና ምቱት ሌላውን ለኛ ተዉልን ::አለዚያ ግን እኔ ወንድሞቼን በከንቱ አላስፈጅም ::" ሳይስማሙ ተለያዩ ::

ንጉሱ ደብረ ማርቆስ ሲገቡ አርባ አራት ሺህ የበላይ ዘለቀ ሰራዊት በፊታቸው በሰልፍ አለፈ ::ያውም ባንድ ቀን ጥሪ የደረሰው ነው እንጂ ሰራዊቱ በሙሉ አይደለም :: በላይ ዘለቀ እንግዲህ በሰላም አርሼ እበላለሁ ብሎ ንጉሱን "አገሩንም ሰራዊቱን ይረከቡኝ "አላቸው :: "የሰላም ጊዜ ስራ አለ ::አገርን ማስተዳደር አለ "አሉት :: "እኔ ተራ ሰው ነኝ ::ሀረግ የሚቆጥሩት ሰዎች አያሰሩኝም ::ከርስዎ ጋር ያጣሉኛል "አላቸው :: "እኛ የማንንም ወሬ አልሰማም ::እንደአባትህ ቁጠረን ::እነዚህ ልጆቻችንም ወንድሞች ናቸው ::..."
ንጉስ ሹም ሽር አደረጉ ::በላይ ዘለቀ ከወንድሞቹ ጋር ሆኖ በሁዋላም ከአገሬው ጋር ሆኖ ጠላትን ተዋግቶ ነጻ ያወጣው ጠቅላይ ግዛት ለራስ ሀይሉ ተሰጠ :: በላይ ዘለቀ ወዳዲሳባ ተጠርቶ ደጃዝማች ተብሎ የቢቸና አውራጃ ገዥ ሆኖ ተሾመ :: የቢቸና አውራዣ ገዥ ሆኖም ሊሰራ አልቻለም ::ከደብረ ማርቆስ ትእዛዝ እየመጣ ወረዳዎቹ ሁሉ ቀድሞ ባንዳ የነበሩ ሰዎች ተሾሙባቸው ::ብስጭት በዛበት በላይ ዘለቀ :: "ሊወጋን ነው ....እምቢ አለ ..."እያሉ ማስወራት ጀመሩ :: በቂ ካስወሩ በሁዋላ ከራያና አዘቦ ጦር አስዘመቱበት :: (ጎጃመማ በላይ ዘለቀን ወይ ይወደዋል ወይ ይፈራዋል :: ) በላይ ዘለቀና ወንድሞቹ ከጥቂት ታማኝ ተከታዮቹ ጋር ሆነው ወደ ሳማ አምባ ሸሹ ::በላይ ዘለቀ ሸፈተ ተባለ :: ሳማ አምባ ያለ ሁለት በር የላትም ሁለቱንም በር ይዘው ሀያ አምስት ቀን ሌትና ቀን ተዋጉ :: "ምረነዋል ልቀቁት ይምጣ "የሚል መልእክት ከንጉሱ መጣ :: ከሳማ አምባ ከወረዱ በሁዋላ ተከበቡና መሳሪያቸውን ተነጥቀው እንደ እስረኞች ወደ አዲስ አበባ ተወሰዱ :: በላይ ዘለቀ ሞት ተፈረደበት ::ንጉሱ "ምህረት " አደረጉለትና ቅጣቱ ወደ እስራት ተለወጠለት ::

መስከረም 1936 . በላይ ዘለቀና ወንድሞቹ በያገሩ ተበትነው ታሰሩ :: በላይ ዘለቀና ወንድሙ እጅጉ ዘለቀ ወሊሶ በበቀለ ወያ ጠባቂነት ታሰሩ :: የበላይ ዘለቀ ምቀኖች አሁንም አላረፉለትም ::በላይ ዘለቀ ከዳ ;አመለጠ ጠፋ እየተባለ ይወራ ጀመር ::በቀለ ወያ ተያዘና "ምን ቢሰጥህ ነው የለቀከው ?"ተባለ ::"እረ እኔ አልለቀኩትም አለ :::: በላይ ዘለቀና እጅጉ ዘለቀን ወደ አዲስ አበባ አመጡዋቸውና ከአንድ ሌላ ሰው ጋር አሰሩዋቸው :. ሰው እናምልጥ እያለ እነ በላይ ዘለቀን ይጎተጉታቸው ጀመር :: አንድ ቀን "ጠባቂዎቻችንን የኛ ወዳጆች ገዝተዋቸዋልና እናምልጥ ::በንዲህ ያለ ስፍራ እነ እገሌ መኪና ይዘው እየጠበቁን ናቸው ::"አል :: "ወንድሞቸ በየቦታው ተበታትነው ታስረው እኔ ማምለጥ ምን ያረግልኛል ?" አለ በላይ ዘለቀ :: "ፈራህ እንዴ በላይ ዘለቀ ?"አለው :: "እኔ የዘለቀ ልጅ !" በላይ ዘለቀ ወንድሙን ላከው መኪናው እተባለበት ስፍራ መኖሩን ለማረጋገጥ ::ወንድምየው በተባለበት ስፍራ መኪና አየ ::እስረኞቹና ጠባቂዎቻቸው አብረው አመለጡ ::እመኪናው ቦታ ሲደርሱ መኪናው የለም ::እንግሊዝም የለም :: ጠባቂዎቻቸው ከዚያ ሮጠው አጠገባቸው ከነበረው ጫካ ገቡና ደጋግመው ተኮሱ ::ምልክት ነው :: በላይ ዘለቀ እጠላቶቹ ወጥመድ ውስጥ መግባቱን አወቀ :: በላይ ዘለቀና እጅጉ ዘለቀ ከዚያ እሮጠው አመለጡ :: ሰላሌ ደርሰው በቅሎ ለመከራየት ሲነጋገሩ ተከበቡ :: በላይ ዘለቀ በጦር ፍርድ ቤት ሞት ተፈረደበት ::ንጉሱ ፍርዱን አጸደቁት :: ጥር 1937:.በላይ ዘለቀ በስቅላት ሞተ ::እድሜው ሰላሳ አምስት አመት ነበር ::

ጥልያንን በመድፍ በመትረየስ በአውሮፕላን ሊገድለው ያልቻለውን ጀግና በቅናት የተነሳሱ መቀኞች የሸረቡት ገመድ ገደለው ::ፊታውራሪ ተሻለ አለሙ ሰላሳ አምስት አመት ታስረው በለውጡ ተፈቱ :: በላይ ዘለቀ ፎቶ ተነስቶ አያውቅም ::መልኩን ፊታውራሪ ተሻለ አለሙ እንዲህ ብለው ይገልሱታል :: "አፍንጫው ሰተት ብሎ ወርዶ ቅጠሉ ነፋ ነፋ ይላል ::ከንፈሩ ከበድ ይላል ::ጠጉሩ ክርክም ጎፈሬ ጺሙ ሙሉ ለስላሳ ረጅም ጣቱ መልካም ወተት የተነከረ ነው የሚመስለው ጣቱ ::እግረ ቀጭን ::"

በላይ ዘለቀ ደጃዝማች ተብሎ ካዲስ አበባ ወደ ደብረ ማርቆስ እንደተመለሰ ከባለስልጣኖች ጋር ለመገናኘት ወደ "ጠቅላይ ግዛቱ " ጽህፈት ቤት ሄደ ::ዘበኞቹም አጋፋሪውም ሲያዩት ጊዜ ሽሽታቸውን ለቀቁ ::ስምና ግርማው ያን ያህል ያስፈራ ነበር :: ከጽህፈት ቤቱ ወጥቶ ወደ ሚያርፍበት ቤት ሲገባ ወሬው ከተማውን ከመቼው እንዳደረሰው አይታወቅም ::ማርቆስ ያለ ሰው ሁሉ እንጀራውን ወጡን ጠላውን ጠጁን አረቄውን እየያዘ መጣ ::በላይ ዘለቀን ህዝቡ ሲወደው ያን ያህል ነበር ::ምግብና መጠጡ ከመብዛቱ የተነሳ ሰዎች ወደውጭ ተላኩና አላፊ አግዳሚውን "የራበኽ ስንቅ የለለኽ ብላ !በበላይ አምላክ ግባ "እያሉ ጋበዙት :: በበላይ ዘለቀ ሰራዊት ውስጥ መሪና ተከታይ አለቃና ጭፍራ ያለው በውጊያ ሰአት ነው እንጂ በምግብ ሰአት ሁሉም እኩል ነው ::ለሰራዊቱ የሚበቃ ምግብ ከሌለ ያለው ተቆራርሶ ለሁሉም እኩል ይደርሰዋል :: በላይ ዘለቀ መሶብ ሲቀርብለት "ሁሉም በልቷል " ይላል :: "አይ ዛሬ እጥረት አለ "ካሉት "እንግዲህ መልሱ ::እኔ አልበላም "ይልና ጦሙን ያድራል :: (አንዳንድ ጊዜ ሁሉም ባይበላም ውሸታቸውን ሁሉም በልቷል ይሉና ያበሉታል :: ) "አንድ ጊዜ ሁለት ቀን ጦም አድረን በላይ ዘለቀ ዛሬ ሶስት ድርብ (ሁለት ቁና ) ሽምብራ ላመጣልኝ ጠመንጃ እሰጠዋለሁ አለ ::አንድ ገበሬ ሽምብራውን አመጣ ;ጠመንጃውን ወሰደ ::ሽምብራውን በልተን አደርን " በላይ ዘለቀ የገንዘብ ፍቅር የለበትም ::እንዲያውም ብር በእጁ አያድርም :: "ራስ ጌታ አታርጉብኝ ...ይጠቀጥቀኛል "ይላል :: ያቃዠኛል ማለቱ ነው በጎጃምኛ ::
ንጉሱ ደብረማርቆስ የመጡ ጊዜ አስራ ሁለት ሺህ ብር ሰጥተውት ሄዱ ::በላይ ዘለቀ ከማርቆስ ወደ ቢቸና ሲጉዋዝ አንዱ መጥቶ "ቤቴ ተቃጠለ "ገንዘብ ሲሰጠው ;ሌላው መጥቶ "ከብቴ ተዘረፈ " ሲል ገንዘብ ሲሰጠው እንዲህ ሲል ገና ቢቸና ሳይገባ አስራ ሁለት ብሩ አለቀ :: "ጊዮርጊስ ያውቃል "ይላል በላይ ዘለቀ ::በጊዮርጊስ በጣም ያምናል ::ፍልሰታ ሲሆን ሁል ጊዜ ሱባኤ ይገባል ::"እኔ የዘለቀ ልጅ !"ይላል ሲቆጣ :: "በምድር በሰማይ የሚያስጉዘው !በላይ የወንዶች ቁና "ይላል ሲፎክር :: በላይ ዘለቀ ተኩሶ አይስትም ::ፍጥነቱ ደሞ ሲደግንና ሲተኩስ እኩል ነው ::ውጊያ ሊጀምር ሲል "እኔ ሳልተኩስ እንዳትተኩሱ " ብሎ ያዛል ::አንዳንድ ጊዜ በውጊያ ሰአት "እርስዎ እዚህ ይቆዩን " ሲሉት "ምን ?" ይላል ቁጣ እየጀመረው ::"እርስዎ ከወደቁ መሪ የለንም " ሲሉት "ወይድ ! እኔ አሮጌ ነፍጠኛ ነኝ ::"ይልና ግንባር ይጋፈጣል :: በላይ ዘለቀ እራሱ ሲዋጋ "ገምባው " ይተበባለው ጥሩንባው ይነፋል ::"ገምባው "ባንዳን ያስበረግጋል ::ጥልያንን ያብረከርካል ::

በላይ ዘለቀ የዘ ,መኑን አስተሳሰብ በማወቁ ህዝቡን ለማስተባበር "ትልቅ ሰው " ማስፈለጉን በመገንዘቡ እሱ እራሱ ግን ተራ ሰው በመሆኑ የንጉስ ተክለሀይማኖት ሀረግ ለሆኑት ለልጅ ሀይሉ በለው ደብዳቤ ጻፈላቸው :: የደብዳቤው ሀሳብ ባጭሩ "ህዝቡን ለማስተባበር እርስዎ የበላይ ሆነው እነን የጎበዝ አለቃ ይሹሙኝና ጠላትን እንቋቋመው ::እኔም እዋጋለሁ ::እርስዎ ወደጦር ግንባር መድረስ አይኖርብዎትም ::" የሚል ነበር ::ደጋግሞ ደብዳቤ ጻፈላቸው ::ገጸበረከትም ላከላቸው ::...ጠመንጃ ሽጉጥ ዝናር ከነጥይቱ ሶስት መቶ ብርና ካባ ::

ልጅ ሀይሉ በለው ለደብዳቤዎቹ አንድም መልስ ሳይሰቱ አንድ ቀን አንድ የትእዛዝ ደብዳቤ ላኩበት ::"ደብረወርቅ ገበያችንን ያለአግባብ ቀረጡብን ብለዋልና ከንግዲህ ቆቅ የሰገረ ወፍ የበረረ እንዳይደርስባቸው ::የተወሰደባቸውም ቀረጥ እንዲመለስላቸው ::"
በላይ ዘለቀ ተናደደ ::አብረውት የነበሩትን "ጎበዝ እግዚአብሄር የወለደው ሰው አለ ?" ሲል ጠየቀ :: "እግዚአብሄር ይፈጥራል እንጂ አይወልድም " አሉት :: "ንጉስስ ?" "ንጉስም እግዚአብሄር ይቀባዋል እንጂ አይወልድም ::ይፈጥረዋል እንደሌላሰው " "እኔንም ፈጥሮኛል ::ሊቀባኝ አይችልም ?" "የሱ ሀይል ካደረብዎ የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ ::" "እንግዲህ ከዛሬ ጀምሮ ለማንም አልታጠቅም ::" ተመስገን ፈንታ የበላይ ዘለቀ የቅርብ ጉዋደኛው ነበር ::አንድ ቀን ከጠላት በፊት ተመስገን ፈንታ በላይ ዘለቀን "ሸዋ ሄደን ለትልቅ ሰው እንደር ::እንሾማለን ;እንሸለማለን "አለው :: "እኔ ሰው ሆኜ ለሰው አላድርም "አለ በላይ ዘለቀ :: "ባንተ ተኩስ ;ባንተ ወኔ ;ባንዳፍታ ትሾማለኽ :: "ጀግንነት እደጃችን ድረስ ይመጣ እንደሆነ ማን ያውቃል ?" አለው በላይ ዘለቀ ::አመታት አለፉ ::
ሞረድ እጀ ጠባብ ካስመራ እሚመጣ አፈ ሾሌ ሱሪና ተመሳሳይ ኮኮት ጥንግ ድርብ ጥበብ ኩታ በቅሎ እንደተጫነች ጠመንጃ ከነሙሉ ዝናር ጥይት ...በላይ ዘለቀ ይህንን ሁሉ አዘጋጀና ተመስገን ፈንታን ጠርቶ ; " የጌታ አዳር ሄደን እንሸለማለን ያልከው ይኸውና "ብሎ ሸለመው ::በአርበኝነት ዘመን ጉዋደኛሞቹ አልተለያዩም :: በላይ ዘለቀ መጀመርያ "ራስ " ብሎ የሾመው ተመስገን ፈንታን ነበር :: "እኔንስ ራስ አልከኝ ::አንተ ማን ልትባል ነው ?" አለው ተመስገን ፈንታ :: "እኔንማ እናቴ አንደዜ በላይ ብላኛለች " አለ በላይ ዘለቀ ::

1 comment: