Wednesday, July 15, 2015

“ አንድ ሰው ለአንድ ወገን! ”

Click here for PDF
       (ወገን አልባ ወገኖች)
ፒያሳ ሐምሌ 82007 . ማለዳ 300 ሰዓት፡፡ ፒያሳ ከፀሐይ በተለቀቁት ጨረሮች ፈካ ለማለት እየሞከረች ነው፡፡ ሰው የማያጣት ፒያሳ በሰው ትርመሰመሳለች፡፡ ወደ አስኮ፣ አውቶብስ ተራ፣ አራት ኪሎ፣ ካዛንቺስ መገናኛ ፣ስድሰት ኪሎ፣ ሽሮሜዳ፣ አዲሱ ገባያ ለመሄድ በሚርመሰመስ ሰው፡፡ መሃል ፒያሳ ከወደ አውቶብስ መያዣ አካባቢ አውቶብስ ጠባቂዎች የሚያርፉበት መቀመጫ እንደድሮው አውቶብስ በሚጠብቁ ሰዎች አልተያዘም፡፡ በምትኩ በቤት አልባ ብላቴናዎች ተጨናንቋል፡፡ ቀኑ ሐሩሩና ረሃቡ፣ ሌሊት ደግሞ ቁሩ የተፈራረቀባቸው ብላቴናዎች በጥዋቷ ፀሐይ ሙቀት እንቅልፍ አሸልቧቸዋል፡፡ አንዲት ቤት አልባ የሆነች ውሻም ከቤት አልባ ብላቴናዎች ጋር ጉርብትናን ፈጥራ አብራ ተኝታለች፡፡ ለብላቴናዎች ሙቀትንና ፍቅርን ትለግሳለች፡፡ እነሱም በአጠፋው ፍቅርንና ሙቀትን ብቻ ሳይሆን ከሚበሉትም ያጋሯታል፡፡ ውሻዋ ለብላቴናዎች ምግብ ማጋራቷን ግን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ውሻና ሰው ተጋርቶ አንድ ላይ ሲበላ ማየት የተለመደ ነው፡፡ በእርግጥ የዚችን ውሻ ያክል ፍቅር እንኳ ማን ሰጣቸው፡፡ ከውሻ የባስን መሆናችንን ሳስበው ዘገነነኝ፡፡


ለደቂቃዎች ቆም ብዬ አካባቢውን ቃኘሁ፡፡ ሰው እነሱን ቆም ብሎ አያየ ከንፈሩን መጦ ያልፋል፡፡ ሌላው ቆረጥ አድርጎ አይቶ አዲስ ነገር አይደለም በሚል አይነት እይታ አይቷቸው ላጥ ብሎ ያልፋል፡፡ አትኩሮቴ አውቶብስ ውስጥ ወዳለች አንዲት ድህነት ያገረጣት እናት ሄደ፡፡ በትካዜና በአትኩሮት ወደ ብላቴናዎቹ በመስኮት ትመለከታለች፡፡ ሴትዮዋ በአርባዎች ዕድሜ ውስጥ ያለች ፊቷ መልካም የእናትነት ፍቅር የሚለግስ ሩህሩህ ትመስላለች፡፡ እይታየ ድርጊቷን እንዳይረብሽ በቆረጣ ማየቴን ቀጠልሁ፡፡ ከመቅፅበት አይኗ በእንባ ተሞላ፡፡ የእናትነትና የርህራሄ እንባ! የሰብአዊነት እንባ! ያስለቀሳት ምን እንደሆነ ግን ደፍሮ የመጠየቅ ወኔ አልነበረኝም፡፡ የእሷ እንባ ሳይጋባብኝ ቶሎ ብየ አካባቢውን ለቀቅሁ፡፡ ህሊናየ ግን አንተስ ምን አደረገህላቸው? ከውሻዋ አንሰህ? ቢያስ ከንፈርህን ምጠጥ? ቢያንስ እንደዚያች ሴትዮ አልቅስ? አለኝ፡፡ ማልቀስ ምን ጥቅም አለው፡፡ ማውራት ምን ጥቅም አለው፡፡ ይኸው ዘመን አለቀስን፣ ዘመን አወራን፡፡ ምላሳችን እና ስራችን ለየቅል ሁኖ ተቸገርን፡፡ ወገን አልባ ወገኖች የበዙባት ሰው አልባ መሬት፡፡ ሰብአዊነት ህንፃ መደርደር የሆነባት ምድር፡፡ አንዱ በብርሃን ፍጥነት ወደ ቱጃርነት ሲለወጥ ሌላኛው በብርሃን ፍጥነት ወደ ባሰ ድህነት (absolute poverty) ይወረወራል፡፡ እንደ ኢኮኖሚስቶች አነጋገር ከሆነ -ፍትሃዊ የሆነ የህብት ክፍፍልና ፍሰት (Improper resource allocation) በአንዲት አገር ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊያመጣ ይችላል፡፡ ጥቂቶች ወደ ሀብት ሰገነትነት ሲወጡ ብዙዎች ወደ ድህነት አረንቋ ይወርዳሉ፡፡ ይህ ደግሞ አንዱ የካፒታሊዝም ስርዓት መገለጫ ነው፡፡ ኢኮኖሚስቶች እንደሚሉት -ፍትሃዊ በሆነ የሀብት ክፍፍልና ፍሰት ስርዓት፣ ሀብታሙ የበለጠ ሀብታም ደሃው የበለጠ ደሃ ይሆናል ይላሉ ("The rich get richer and the poor get poorer"):: ምንም እንኳ ይህ ጉዳይ በአንድ ቀን ሌሊት የአንድ ቀበሌ በጀት በቅንጦት አጥፍተው ከሚያድሩት ቱጃሮች ጀምሮ ከእጅ ወደ አፍ ብቻ የሚኖረውን ወገን ሁሉ የሚመለከት ቢሆንም የአንበሳውን ድርሻ ግን መንግስት ይወስዳል፡፡ መብላት፣ መጠጣት፣ መልብስና መጠለያ መፈለግ የፖለቲካ ጥያቄ አይደለም፡፡ ሰው ሰው በመሆኑ ማግኘት ያለበት ተፈጥሮአና ሰብአዊ መብቶች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው መንግስት የአገሪቱን የኢኮኖሚ ፍሰት ፍትሃዊ በማድረግ መሰረታዊ የሆኑ ፍላጎቶችን ለህዝቦቹ ለማሟላት የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ አለበት የምለው፡፡ ቢያንስ ጊዜአዊ የምግብ እገዛ፣ የልብስና መጠለያ ድጋፍ የሚደረግበት የማገገሚያ ማዕከል (Rehabilitation center) መኖር አለበት፡፡ ይህን የሚያደርጉ የውጭና አገር በቀል ድርጅቶች አንዳሉ እውቃለሁ፡፡ በተለይ የወገን ወዳዱን የቢኒያምን ድርጅት መቄዶንያን ሳልጠቅስ ማለፍ አልችልም፡፡ ሆኖም ግን ካለው የድህነታችን ጥልቀትና በየጊዜው እንደ ዓለም ሙቀት ከሚጨምረው የኑሮ ውድነት (economic inflation) አንፃር እየተደረገ ያለው ነገር አባይን በጭላፋ ብለን ከመተረት ያለፈ አይሆንም፡፡ ከሁሉም በላይ ተምረው ለሀገርና ለወገን ሊጠቅሙ የሚችሉ ብላቴናዎች በመሰረታዊ ፍላጎት እጦት ምክንያት የሀገር ሸክም መሆን የለባቸውም የሚል ፅኑ ቋም አለኝ፡፡

እኛስ እንደ ወገን ምን እናድርግ? ከንፈር እየመጠጥን እንለፍ! ደጉ ሳምራዊ በመፅሀፍ ውስጥ እንጂ በተግባር ከእኛ ልብ ወጥቷል፡፡ በእርግጥ -ሰብአዊነትን ለምደነዋል፤ በየመንገዱ፣ በየገደሉ፣ በየቆሻሻ ገንዳው፣ በየስርቻው ወደቀው የሚያቃስቱ ሰዎችን እያየን ማለፍ ብርቅ አይደልም፡፡ ከዚያም አልፎ የብዙቻችን ህንፃ በድሆች ደምና አጥንት የተገነባ መሆኑን ለአፍታ እንኳ ማስታወስ አንፈልግም፡፡ ብናምንም ባናምንም የእያንዳንዱ ድሃ ሀብት እኛ እጅ ላይ አለ፡፡ ሀብቱን ያገኘንበት መንገድ ፍትሃዊም ይሁን -ፍትሃዊ፤ ሃብት ከአንዱ ወደ አንዱ በመዛወሩ ምክንያት እኛ ሀብታም ስንሆን ሌሎች ድህነት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሰዎች መርዳት የሰብአዊነት ግዴታ ብቻ ሳይሆን የህሊናም ግዴታ አለብን፡፡ የግል የሆነ ሀገር፣ የግል የሆነ ሀብት፣ የግል የሆነ ገንዘብ የለም፡፡ እኛ ሀብታም የሆነው የነዚን ህዝቦች መሬት፣ ውሃ፣ መብራት፣ መንገድ፣ ጉልበት፣ ገንዘብ፣ ጊዜና እውቀት ተጠቅመን ነው፡፡
                       ስለዚህ ምን እናድርግ?
እኔ አንድ ሃሳብ አለኝ፡፡ ለአንድ ወገን አንድ ብርአልላችሁም-ሚዛን የሚደፋ ለውጥ ሊያመጣልን ስላልቻለ፡፡ እያንዳንዱ ሰው ቢያንስ አንድ ችግረኛን ማገዝ ከቻለ፣ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ባንቀርፈውም ካለበት አስከፊ ሁኔታ ፈቀቅ ማድረግ ይቻላል ብየ አምናለሁ፡፡  እስኪ ሁላችንምአንድ ሰው ለአንድ ወገን ብለን እንነሳ፡፡ እኔ ለእናንተ ቃል ገባሁ! እናንተስ?

                                                         አንድ ሰው ለአንድ ወገን!

No comments:

Post a Comment