Monday, December 28, 2015

“ቱቦ አትሁኑ…ቱቦ አትሁኑ…”


“ልጆቼ ቱቦ አትሁኑ፡፡ ቱቦ ባዶ ነው፡፡ የሚይዘው ነገር የለም፡፡ ማስተላለፍ እንጂ መያዝ አይችልም፡፡ ቱቦ ካልሰጡት በራሱ የሚያመነጨውና የሚያስተላልፈው ነገር የለም፡፡ ቱቦ ሁሌም ጥገኛ ነው፡፡ ልጆቼ ቱቦ አትሁኑ፡፡ቱቦ አትሁኑ፡፡ ልጆቼ መተላለፊያ አትሁኑ፡፡”
ይህ ንግግር በአንድ ወቅት አንድ አባት የተናገሩት ነው፡፡ በወቅቱ ንግግራቸውን ከቁብ አልቆጠርሁትም፡፡ ሌሎቹም እንደዚሁ፡፡ ምክንያቱም ሰው እራሱ ቱቦ ነው፤ በአፉ አስገብቶ በ ‘እንትኑ’ የሚተፋ የምግብና የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦ፡፡ ከዚህ ያለፈ ሰውን ከቱቦ ጋር ሊያመሳስለው የሚችል አንዳች ነገር በጊዜው አልታየኝም፡፡ ይህ ደግሞ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ስለዚህ በጊዜው ሀሳባቸውን ውድቅ አደረግሁት፡፡ መብቴ ነው መቀበልም አለመቀብልም (አንቀፅ---)፡፡

አሁን ላይ ቆም ብዬ ሳስበው ግን እነዚያ አባት ልክ ናቸው (ኧረ ተቀምጨም አስቤዋለሁ)፡፡ የሰው ልጅ ብዙ ቱቦ ያለው ፍጡር ነው፡፡ በጆሮው ሰምቶ ሳያጣራ በአፉ የሚተፋ ቱቦ፤ በዓይኑ ያየውን ነገር ሳያገናዝብ የሚተፋ ቱቦ፣ የሌሎችን አስተምህሮ ጥቅምና ጉዳቱን ሳያመዛዝን ለሌሎች የሚያስተላልፍ ተንቀሳቃሽ ቱቦ፡፡ እውነት ነው፡፡ ሌሎችን እያጠጣ ለእራሱ ምንም የሌለው ሁሌም የቧንቧውን መልካም ፈቃድ የሚጠብቅ ተንቀሳቃሽ ቱቦ፡፡

እነሆ ፍልስፍና፣ ሃይማኖት፣ ፖለቲካ ና ማህበራዊ አስተሳሰብ በመጠንና በአይነት ዓለምን እንደ ክረምት ጎርፍ ማጥለቅለቅ ሲጀምሩ የጎርፉ ማስተላለፊያ ቱቦዎችም መጠን በእጅጉ እየናረ መጣ፡፡ የሃይማኖት ቱቦዎች፣ የፖለቲካ ቱቦዎች፣ የፍልስፍና ቱቦዎች ዓለምን ሞሏት፡፡ የሀሳቡን ትርጉምና ምንጭ፤ ክብደትና ቅለት፣ ጥቅምና ጉዳት ሳያመዛዝኑ የተጫኑትን የሚያስተላልፉ ቱቦዎች በዙ፡፡ ዓለም በቱቦዎች ተሞልታለች፡፡ የተጫኑትን የሚለፈልፉ ነገር ግን ቅንጣት እምነትና እውቀት የሌላቸው ሰባኪዎች፤ የሚናገሩትን የማያውቁ ፖለቲከኞች፤ ሳይገባቸው ሸምድደው ትውልዱን በ መላምት ሳይንስ (Theoretical science) የሚያጠምቁ መምህራን፤ ያልሆነና ያልተፃፈ ታሪክ የሚያነበንቡ ተመራማሪዎች ዓለምን ወረዋታል፡፡ አመንጭ ሳይሆን አስተላላፊ በዛ፡፡ ትውልዱ የትንሽ ሰዎች አስተሳሰብ ማስተላለፊያ ቱቦ ሆኖ ቀረ፡፡ ለምን የሚል ትውልድ እንደምሽት ጀምበር ዝግ በዝግ ወደ አድማሱ ገብቶ ከሰመ፡፡ ሳያመዛዝኑ የሚያስተላልፉት የሀሳብ ጎርፍም ብዙዎችን በማጥለቅለቅ አዕምሮአቸውን አመከነ፡፡ አምክኖም በእልቆቢስ ምክንያት እያሳበበ ብዙ ትውልዶችን ቱቦ አደረጋቸው፡፡

ሰው ከሌላው የምድር ፍጥረታት የሚለየው ማሰብ፣ ማገናዘብ፣ ማመዛዘንና መተንበይ በመቻሉ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጥረታት በምንም አይለይም፡፡ በሬዎች በነዷቸው ማሳ ይነዳሉ፡፡ አህዮች ያሸከሟቸውን ዕቃ ከተባሉት ቦታ ያደርሳሉ፡፡ በጎች ወደተነዱበት ሜዳ ሄደው ይታረዳሉ፡፡ ሰውም የተነገረውን፣ የሰማውን፣ ያየውን፣ የተመለከተውን ሀሳብና ድርጊት የራሱን ግንዛቤና ምልከታ ሳይጨምርበት እንደወረደ ለሌሎች እንደ ቱቦ ካስተላለፈ ከእነዚህ እንስሳት አይለይም፡፡

ትውልድ ቱቦ ከሆነ የራሱ አስተሳስብ፣ የራሱ አመለካከት፣ የዕራሱ ፍልስፍናና የራሱ አስተምህሮ አይኖረውም፡፡ ቆሻሻም ይሁን መልካም ሌሎች የፈጠሩትን ፍልስፍና፣ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምና አስተሳስብ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያስተላልፍ ቱቦ ሁኖ ያልፋል፡፡ በምትኩም አራሙቻ ተከታይ ቱቦችን ይፈጥራል፡፡ ምዕራባውያን የፈጠሩትን የጅብ አስተምህሮ፣ ኢ ሰብዓዊያን የፈጠሩትን የቅራኔ ዓለም አስተሳሰብ፣ ነጋዴዎች ተሰባስበው የፈጠሩትን ሃይማኖት፣ በሞቅታ የተፈጠረን የፖለቲካ አስተሳሰብ፤ በሰከነ መንፈስ ሳያገናዝቡ በቀጥታ ለትውልድ ማስተላለፍ ትውልድን ከማምከንም በላይ የነገ ማንነት ላይ ትልቅ ጠባሳ ጥሎ ያልፋል፡፡ ማንነቱን ረስቶ በሌሎች አስተሳሰብ ጥላ ስር ተንበርክኮ የሚኖር ተቅበዝባዥ ትውልድ ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ ከቧንቧው የተለቀቀለትን ውሃና ፅዳጅ ብቻ ሳይሆን ከእራሱ እውቀት፣ ባህል፣ ሐይማኖት፣ ታሪክ፣ አስተሳሰብና ፍልስፍና ጋር በማገናዘብ ትንሽም ቢሆን ጨምሮ ወይም ቀንሶ ማስተላለፍ ግዘት ነስቶ ለቆመ ሰው ሁሉ ተፈጥሮአዊ ግዴታ ነው፡፡ ያኔ ትውልድ በአመለካከት፣ በአስተሳሰብ፣ በባህል፣ በትምህርት፣ በስልጣኔና በእድገት ከፍተኛ እምርታ ያሳያል፡፡ ቱቦ መሆን ይብቃ! “መቼ? የት? እንዴት? በማን? ለምን?” ብሎ የሚጠይቅ ቱቦ ያልሆነ ትውልድ ፈጣሪ ይስጠን፡፡
              “ልጆቼ ቱቦ አትሁኑ፡፡ቱቦ አትሁኑ፡፡ ልጆቼ መተላለፊያ አትሁኑ፡፡”1 comment: