Saturday, October 24, 2015

“የእኔና የአንቺ ዓለም”

ለአንዱ ማግኘት ጣጣ 
ከውስኪ ሰገነት ስካር ላይ ሲወጣ
ለአንዱ ማጣት ዕዳ
ኑሮና ህይወቱ የቆሻሻ ገንዳ፤
አንዱ ጉልበተኛ የተጣላ ከእግዜር
ሰውን እንደ ሽንኩርት በስለት ሚመትር
ሌላው እረሃብተኛ
አገጩን ጭኑ ላይ ደግፎ የተኛ፤
አንዳንዱ ቄንጠኛ
በልዑል ሰገነት ልጁን የሚያስተኛ
ሌላው ዕድለቢስ
ከመላጣ እስፋልት ላይ በውርጭ የሚጠበስ፤
እዚያ ዲሞክራሲ 
ነፃነት በኬሻ ሁሉም ሰው ሃያሲ
እዚ አውቶክራሲ
ትንሽ ሰው ደራሲ፣ እራሱ ሃያሲ፤
ማዶ ቀዝቃዛ ብርድ 
የበረዶ ክምር ሰውነት የሚያርድ
ወዲህ የእሳት ምድር 
ጠብታ አልባ መሬት የሚያቃጥል ሐሩር፤
ይች ናት እንግዲህ…………
እግዜሩ ሲፈጥር መከራ ያየባት
በነጭ ወረቀት ላይ እርሳስ የነደፋት፤
ከእሱ ተቀብሎ ምድራዊው ፈላስፋ
የብዕሩን ቀለም ምራቅ እየተፋ፤
አጥፍቶ የሳላት በዥንጉርጉር ቀለም
ይች ናት እንግዲህ የእኔና የአንቺ ዓለም
!
          [ዘላለምየእናቱ ልጅ]

          ጥቅምት 11፣ 2007 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment