Thursday, October 8, 2015

[“የእንቅልፍ ዘመን”]

ድሃ እንዳትሆን እንቅልፍህን አትውደድ” 
       መፅሐፈ ምሳሌ 20፡13ጠቢቡ ሰለሞን በዚህ ዘመን ቢኖር ኖሮ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ የድሃ ድሃ እንዳትሆኑ እንቅልፋችሁን አትውደዱ” ብሎ ይናገር ነበር፡፡ እነሆ ይች ዓለም የበረዶ ዘመን፣ የነሃስ ዘመን፣የብረት ዘመን፣ የጨለማው ዘመን፣ የአብዮት ዘመን፣ የጦርነት ዘመን ፣ የሳይንስ ዘመን እያለች ብዙ አያሌ ዘመኖችን አሳልፋለች፡፡ እነሆ የእንቅልፍ ዘመን ደረሰ! እናት አህጉር አፍሪካ የ 50 ዓመት መፃኢ ራዕይዋን የምታሳካበት የስራ ዘመን ሳይሆን በድጋሜ ተኝተን ቅኝ የምንገዛበት የ "እንቅልፍ ዘመን" ውስጥ የገባች ይመስላል፡፡ ድህነት፣ ረሃብ፣ በሽታ፣ ጦርነት፣ ብጥብጥና ጥላቻ አፍሪካን ቅኝ የሚገዙበት የእንቅልፍ ዘመን!

መሪና ተመሪ የተኛበት፣ ተማሪና መምህር የተኛበት፣አሠሪና ሠራተኛ የተኛበት የእንቅልፍ ዘመን! እንቅልፍ ተፈጥሮአዊና የጤነኛ ሰው የስርዓተ ሕይወት አካል ነው፡፡ አንድ ጤነኛ ሰው በቀን በአማካኝ ከ6-8 ሰዓት ሊተኛ ይችላል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከዚህ በላይ እንቅልፍ ሊተኛም ይችላል፡፡ አልፎ አልፎም በቀን እንቅልፍ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን አንድ የሃገር መሪ ወይም የሚሊዮኖችን ድምፅ ወክሎ ፓርላማ የተሰየመ ሰው በጠራራ ፀሐይ ሀገራዊና አህጉራዊ ፖሊሲዎችና ህጎች በሚፀድቁበትና በሚሻሩበት መድረክ ላይ ደህና አደሩ ሳያል በእንቅለፍ ጭልጥ ማለት አሳዛኝም አስገራሚም ነው፡፡

አኔ ምለው፤ ፕሮፌሰሩ አላዩም እንዴ? ምን አልባት ወደፊት “መክሸፍ እንደ አፍሪካ ህብረት መሪዎች” ወይም “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ፓርላማ አባላት” ብለው ሊፅፉ ይችላሉ፡፡ ላይፅፉም ይችላሉ፡፡ ባይፅፉም ግን እየከሸፍን አይመስላችሁም? በዚህ ከቀጠለ ወደፊት “ዛሬ ኃላፊው እንቅልፍ ላይ ስለሆኑ እስኪነቁ ጠብቁ ወይም ነገ ተመለሱ” የምትል ፀሐፊ ሊገጥመን ይችላል፡፡ ካዘነችላችሁ ደግሞ “ኃላፊው እስኪነቁ ሻይ ቡና” ብላ ከፈገግታ ጋር ልትጋብዛችሁ ትችላለች፡፡ ምን ይሄ ብቻ ችግሩ እየባሰ ከመጣ ደግሞ “ይቅርታ ዶ/ር ተኝተዋል እስኪነቁ ጠብቁ” የምትል ነርስ ትገጥማችሁ ይሆናል፡፡ ዕድሜ ከሰጠን “እንቅልፍ የማያስቸግረው” የሚል ሀረግ ከቅጥር ማስታወቂያ ወይም ከምርጫ ውድድር ማስታወቂያ እንደ አንድ መስፈርት ሆኖ እንመለከት ይሆናል፡፡ ይህ በሽታ ነው፡፡ ያውም ተላላፊ፡፡ ለዚህ እኮ ነው ከሹፌሩ ጎን እንቅልፋም ሰው መቀመጥ የለበትም የምንለው፤ በሽታው ወደ ሹፌሩ እንዳይተላለፍ፡፡ ምን ዋጋ አለው የሰሞኑ የእንቅልፍ በሽታ ከቁጥጥር ውጭ ሁኖ በማህበራዊ ድህረ ገፅ ተዛመተ፡፡ እኔ እራሱ ሰሞኑን እንዴት አይነት እንቅልፍ ተኛሁ መሰላችሁ፡፡ ህመሙ ከጠነከረ  አንብቡ እንጂ ስንላቸው “የፓርላማ አባላቱም ተኝተዋል እንኳን እኛ ተጨንቀን ምን ልናመጣ፣ ለእራሳችን እናንሳለን እንዴ፤ ደግሞስ የተማረና ያነበበ የት ደረሰ? መተኛት ነው የሚሻለን” የሚሉ ልጆችን ማየታችን አይቀርም …..ለሽሽሽ ነው አለ እከ…..ለሽሽሽሸ………..ለሽሽሽሽ ያለ ትውልድ!

አባቶቻችንን ጠላት አላሸነፋቸውም፤ አባቶቻችንን ድህነት አላሸነፋቸውም፤ አባቶቻችንን ጥላቻ አላሸነፋቸውም፡፡ ፍቅር ብቻ ነበር ያሸነፋቸው፡፡ የሀገር፣ የፈጣሪ፣ የወገን፣ የቤተሰብና የታሪክ ፍቅር! እኛን ምን ያላሸነፈን ነገር አለ? ድህነት፣ ረሃብ ፣ በሽታ፣ ስደት፣ ሱስ፣ ስግብግብነት፣ አሁን ደግሞ እንቅልፍ አሸነፈን፡፡ ኧረ እባካችሁ ነቃ በሉ! ለስንቱ የእንቅልፍ መድሃኒት ሰጠን እንችላለን፡፡ ወጣቱ ምሽቱን ጫት ሲያመነዥክና ጃቦውን ሲገለብጥ አድሮ፤ በነጋታው ቢሮ ሰራተኛው ዴስኩን የጉልበት ሰራተኛው ግድግዳውን ተደግፎ ሲያንቀላፋ ይውላል፡፡ ሹፌሩስ ቢሆን መሪ ላይ እየተኛ የስንቱን ሰው ህልም ነው ጎዳና ላይ ያስቀረው? ተማሪውስ ብትሉ ዴስክ ተድግፎ እያንቀላፋ የተማረበትን ሙያ ስም እንኳ በትክክል መፃፍ ሳይችል ወፍራም ዲግሪ ተሸክሞ ይወጣል፡፡ 

ከዚህ ይባስ ብሎ መምህሩ ቦርድ ስር ከተኛ፣ ኃላፊው ቢሮ ውስጥ ከተኛ፣ እነ እሜቴ ፓርላማ ውስጥ ለሽ ካሉ፣ ጤና ባለሙያው ዋርድ ውስጥ ከተኛ ተያይዘን ማለቃችን አይደለም? እኔ ምለው ግን የህዝብ ብሶት እንደዚህ ያስተኛል እንዴ? እውነቴን ነው፤ አይደለም ሺዎችን ወክሎ የአገሪቱን መፃኢ ዕድል ለመወሰን አናት ላይ ቁጭ ያለ ሰው ቀርቶ አንድ ቤተሰብ አስተዳዳሪ እንኳን እንዴት በጠራራ ፀሐይ ይተኛል? የምንመኛትን ኢትዮጵያ ለማየት በቀን አይደለም ገና በማታም መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ምንም እንኳ በመንፈስ ከተኛን ብዙ ዘመን ቢቆጠርም ቢያንስ በአካል ባለማንቀላፋት በሽታውን ከወዲሁ መከላከል ይኖርብናል፡፡ ወይ መከራችን!.... ወደፊት እንደ ፖሊዮ የእንቅልፍም ክትባት ሊያስፈልግን ነው? ምን አገባን ፈረንጆች ምን ሰርተው ይብሉ? ትውልድ ነቃ በል እንጂ! አሊያ አባቶቻችን በንቃት ጠብቀው ያስረከቡንን ሃገር አሁን ካለችበት የእጂ አዙር ቅኝ ግዛት ወደ ቀጥተኛ ቅኝ ግዛት አስረክበን የትውልድም የታሪክም ተጠያቂ መሆናችን አይቀርም፡፡ ፈረንጆቹ ድሮ በጦርነት ያጧትን ሀገር እኛ ስንተኛ ከመረከብ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ለነገሩ ቻይናዎች ቀድመው በር በሩን እየያዙት ነው፡፡ አይ ቻይና!

በመጨረሻም ጠቢቡ እንዲህ ይለናል፡
አንተ ታካች እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሳለህ?” ………..እንግዲህ ድህነትህ እንደ ወንበዴ ችጋርህም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል” ……………ዓይንህን ግለጥ እንጀራም ትጠግባለህ” ይላል (ምሳሌ 6፡9-11፣ ምሳሌ 20-13)፡፡

  እንግዲህ ምህረቱንና መድሃኒቱን ይላክልን ነው እንጂ ሌላ ምን ይባላል!
                       መልካም የመንቃት ዘመን!

No comments:

Post a Comment