Tuesday, November 17, 2015

ለምን አታገቢም? (ክፍል-03)

         

                                       …
ካለፈው የቀጠለ
ምንም እንኳ ስንኞቹን እግር በእግር ባላስታውሳቸውም፤ ከሚከተለው ግጥም ጋር ተመሳሳይ ፍሬ ሃሳብ ያለው ዘፈን ሰምቼ አውቃለሁ፡፡
አግቢ ይሻልሻል ቶሎ ተሞሸሪ
እህትሽ ስትዳር ቁመሽ እንዳትቀሪ
ሴቶች ለምን ቶሎ አያገቡም? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የግድ ሴት መሆን አያሻም፡፡ ካየነው፣ ከሰማነው፣ ከታዘብነው፣ ከተማርነውና ካነበብነው በማንኪያ እየጨለፍን ዘርፈ-ትንሽ የሆኑ ምክንያቶችን ከመጥቀስ ማን ይከለክለናል? ሴቶቹ ስለእኛ ለመፃፍ የኛ ፍቃድ ያስፈልግሃል ካላችሁ፤ በፌደራል ፖሊሳዊ ሰላምታ እጂ ነስቻለሁ (ፌደራል ሲነሳ እንዳትበረግጉ)፡፡ ተፈቅዷል….እሺ ልቀጥል!
ከጎኖችህ አጥንት ሔዋን ሳትፈጠር
አዳም ሆይ ህይወትህ ምን ይመስል ነበር?”

ዌል እንግዲህ…..አዳም ከሰማኝና ከመለሰልኝ እኔም መልሱን በሌላ ጊዜ ጀባ እላችኋለሁ፡፡ ለጊዜው ያነሳነውን ወፍራም ርዕሰ ጉዳይ እንቀጥል፡፡ ሔዋን በዘመኗ የነበራት አማራጭ አዳም ብቻ ነበር-አዳምም እንደዚሁ፡፡ አይዟችሁ አትሰላቹከአዳም ጀመርሁ እንጂ ወደ እነ አብርሃምሳራ….ይስሐቅ እያልሁ መንገዱን አላገምደውምቀጥታ ወደ እናንተ እመጣለሁ፡፡ እናም ይኸውላችሁወፈረም ቀጠነም፣ አጠረም ረዘመም፣ አማረም አስጠላም፣ ከበረም ደኸየም ሔዋንዬ ከአዳም ሌላ አማራጭ አልነበራትም (አማረርኋችሁ መሰለኝ-ሔዋንና አዳም አይሰሙ……ወደ እኛ ጉዳይ ቶሎ ግባ አለች አንደኛዋ)፡፡ አሺ ወደ እናንተ ልምጣ፡፡ ችኩል ትውልዶችም አይደለን! ታሪክን ከስሩ ሳይሆን ከቅርንጫፉ ጀምረን የምንቆጥር፤ ያዝነው ስንል ቅርንጫፉ እየደረቀ የተቸገርን፡፡ ሲደርቅብን ተመልሰን ወደ ስሩ የምንሮጥ ቅብዝብዞች፤የጅብ ችኩል……” ተብሎ የተተረተብን እኛ ነን መሰለኝ፡፡ ይቅርታ ወቀሳ ቢጤ ሆነ መሰለኝ፡፡ ለማንኛውም ወደ ገደለው ልግባ፡፡ ሴቶች ለምን ቶሎ አያገቡም?
ምክንያተ-አሀዱ የእኛ ዘመን ሴቶች ቶሎ ላለማግባታቸው አንደኛው ምክንያት ከላይ ያነሳሁት ጉዳይ ተቃራኒ ነው-የአማራጭ መብዛት፡፡ ከገንዘብ፣ ከትምህርት፣ ከመልክ፣ ከዘር፣ ከሃይማኖት፣ ከቋንቋና ከስነ ባህሪ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች የምርጫ መስፈርታችንን ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ መስፈርት የበለጠ እንዲሆን ምክንያት ሁነዋል፡፡ በዚህም ምክንያት፤ ደሃ ሲመጣ ሀብታም ሲፈልጉ፣ ዲግሪ ሲመጣ ማስተርስ ሲሉ፣ የእንትና ብሔር ሲጠይቅ የእንትና ካልሆነ ሲሉ……...ሲሉ……...ሲሉ…….ሲግደረደሩ….. ሲግደረደሩ……ሲግደረደሩ…… መከረኛው 30 ይመጣና የትናንት ጠያቂያቸውን ዙረው ራሳቸው መገረብ ይጀምራሉ፡፡ሁለት ያባረረ አንድ አይዝም……ተግደርዳሪ ጦም አዳሪእየተባለ በሚተረትብት ሀገር ተረቱን አልሰማ ብለው ሃምሳ ሲያባርሩ በመጨረሻም ከሁለት (ከብዙ) ያጣ ጎመን ሆነው ወደ አርባዎች ይሸበለላሉ፡፡ ከዚያም ክፍል-02 ላይ ያነሳሁት 45 ዓመቱ ጓደኛዬ ታሪክ ወደ እነሱ ቤት ዘው ብሎ ይገባል፡፡
ምክንያተ-ክሌቱ፡ ሁለተኛው ምክንያት ከባህልና ከሐይማኖት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምንም እንኳ አሁን አሁን በምዕራባዊያን የባህል ተፅዕኖ የወደዱትን ሸበላ የሚጠይቁ ሴቶች እየተበራከቱ ቢመጡም፤ አገራችን ውስጥ ካለው ጥብቅ የባህልና የሐይማኖት አስተምህሮ የተነሳ ሴት ልጅ ፍቅሯን በገደምዳሜም ቢሆን ከአፏ አውጥታ ለመናገር ይከብዳታል (መሽኮርመሙና መቅለስለሱ እንደተጠበቀ ሁኖ)፡፡ ምን እንኳ በፍቅሩ ብትቃጠልም ባህሏንና ሐይማኖቷን በማክበር ደፍራ የፍቅር ወይም የጋብቻ ጥያቄ ማቅረብ ይከብዳታል፡፡ በዚህ ውዝግብ መሃል የወደደችውን ጎረምሳ አንዷ ትሞጨልፍባትና የተስፋ መቁረጥ እምባ ወደ ውስጥ እያነባች እጆቿን አጣጥፋ ትቀመጣለች፡፡ ከዚያም ገጣሚው፡
                               “ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድሞ
                                ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቁሞ”……...እንዳለው እድሜ ቁሞ አይጠብቅምና እንደ ምፅዓት የምትፈራው 30 ቁጥር ከች ይላል፡፡ 40ባው በፈረስ ይደርሳል፡፡
ምክንያተ-ሰለስቱ፡ ሶስተኛው የሴቶች የጋብቻ መሰናክል የአቅመ ልዕልና አለመጠጣም ወይም በእንግሊዝኛው “superiority complex” የምንለው ነው፡፡ ሴቶቹ ከወንዶቹ በትምህርት፣ በገንዘብ፣ በስልጣንና በመሳሰሉት ጉዳዮች የሚበልጡ ከሆነ ወንዶቹ ሳይሰናበቷቸው የውሃ ሽታ ይሆናሉ (ይህ ሹገር ማሚወችን አይጨምርም)፡፡ ይህ ሴትን ልጅ የበታች አድርጎ የማሰብ አባዜ ከባህላችን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው፡፡ ወንዶችም ካለባቸው የባላይነት መንፈስ የተነሳ ከእነሱ የምታንስ ሴት ላይ ጆፌአቸውን ይጥላሉ፡፡ ሴቶችም ባላቸው ደረጃ ሲኩራሩ የመጀመሪያውን ምዕራፍ አልፈው ሁለተኛውን ከማገባደዳቸው በፊት ከፊታቸው ያገኙትን ሞጭልፈው ወደቤታቸው ያስገባሉ፡፡ /-ዘበኛ፣ ምሁሯ የጉልበት ሰራተኛ፣ ሚሊየነሯ ደግሞ የቀን ሰራተኛ ሊያገቡ ይችላሉ-እስካሁን ያገቡትም ብዙ ናቸው፡፡ ደከማችሁእሺ አንድ ሙዚቃ ልጋብዛችሁ! የሳልሳዊ ቴዎድሮስንወደ አገር ቤት”………
“…..በሰማዬ ጋሪ የሄድሁት በርሬ
ቢያልፍልኝ ብዬ ነው ስወጣ ካገሬ
በስለት ወጥቼ ለምኘ ታቦት
ምን ይዤ ልመለስ ወደ እናቴ ቤት
ባህር አቋርጨ ተጉዤ…………………”
ቀሪውን እናንተ ጨርሱት (ማልቀስ ወይም መተከዝ አይፈቀድም)፡፡ ወደየት ልወስዳችሁ እንደፈለግሁ ገብቷችኋል ብዬ አስባለሁ፡፡
ምክንያተ-አርባዕቱ፡ ስደት!!! በየትኛውም ምክንያት ይሁን ሰው የተወለደበትንና ቦርቆ ያደገበትን ቀዬና ሀገር ጥሎ ድንበር ሲሻገር ለእኔስደትነው፡፡ የስደትን ህመም የተሰደዱት ያውቁታል፡፡ ምንም እንኳ ችግሩ በራሱ ሰፊና ዘርፈ ብዙ ቢሆንም ለጊዜው ከትዳር ጋር ያለውን መስተጋብር እንመልከት፡፡ ለስራ፣ ለኑሮ፣ ለትምህርትና ለመሳሰሉት ጉዳዮች ባህር ማዶ የተሻገሩ እህቶቻችን (ወንዶችንም ይጨምራል) ሁሉም ነገር እንዳሰቡትና እንዳቀዱት ሳይሆንላቸው ሲቀር በቶሎ ወደ ሃገራቸው መመለስ አይችሉም፡፡ ለእራሳቸው እና ለቤተሰባቸው ሚሆን ጥሪት ለመሰብሰብ ደፋ ቀና ሲሉ አመታት ያልፋሉ፡፡ በለስ ቀንቷቸው ወደ ሃገር ቤት ሲመለሱም ሲሄዱ የነበረችው ኢትዮጵያ ቆማ አጠብቃቸውም፡፡ ሁሉም ነገር እሳት ሆኖ ያገኙታል፡፡ ያመጧት ሳንቲምም ላሰቡት ዓላማ ቀርቶ ለመዝናኛ ሳትሆናቸው ትቀርና ብዙዎቹም ለዳግም ስደት ይዳረጋሉ፡፡ እንዲህ እንዲህ….. እያለ ዓመታት እንደ ገና ጀምበር ይሮጣሉ፡፡ ለሴት ልጅ ሲሆን ደግሞ በእጥፍ ይሮጣሉ፡፡ በዚህ ሂደት አንዳንዶች በባዕድ ሀገር ከሀገራቸው ልጅ ወይም ከመሰል ስደተኛ ጋር ተጣምረው ጎጆ ይቀልሳሉ፡፡ አይ ስደት! ………..ችግር ባይኖር ማን ይሰደዳል?
        “ካላጡ ካልተቸገሩ--መኖር ማን ይጠላል ባገሩነፍስሽን ይማረው ማንአልቦሽ፡፡
 ምክንያተ-አምስቱ፡ አምስተኛው ምክንያት ከአራተኛው ርዕሰ ጉዳይ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ እህቶቻችን ወደ አረብና ሌሎች ሃገራት ለስራ ሲሰደዱ ቦሌ ድረስ ሄዶ፤እወድሻለሁ፣ እስከትመለሽ በቃሌ ፀንቼ እጠብቅሻለሁየሚለውን ቃል ከባንክ ደብተር ቁጥሩና ከወፍራም እምባ ጋር ሰጦና ሸኝቶ የሚመለስ ብዙ ወንድ አለ፡፡  ይህን ማድረጉ ክፋት የለውም፡፡ ቸግሩ የሚመጣው ግን በኋላ ነው፡፡ እነዚህ የዋህ ሴቶች ቃል ለገባላቸው ጎረምሳ ልባቸውን ብቻ ሳይሆን  የሸቀሏትን ሳንቲምም በየጊዜው ገረምሳው አካውንት ውስጥ ይወሽቃሉ፡፡ አጅሬው ፍቅረኛው መከራ አይታ በላከችለት ገንዘብ አይኑ ያያትን ኮረዳ ሲያማግጥ ይቆይናአገር አማንብላ ስትመለስ አይንሽን ለአፈር ብሏት እብስ ይላል፡፡ እሷም እድሏን እየረገመች፡
                  “ተው እምባዬ ውረድ-ደረቴን ግመሰው
                   ብሎ ለመቅረት-ይገናኛል ወይ ሰው”…………..የሚለውን የተስፋዬ ካሳን ዜማ በእምባ እያዜመች ለዳግም ስደት ትዳረጋለች፡፡ በተቃራኒው በቃላቸውና በፍቅራቸው ታምነው ሰባራ ሳንቲም ሳያጎድሉ የሚጠብቁ ምስጉን ወንዶችም እንዳሉ መዘንጋት የለብንም፡፡ሴቶች ያለህን ቀፍለው እብስ ይላሉያላችሁኝ ወንዶች እዚህ ላይ ምን ትላላችሁ? የትኛው ቅፈላ ሚዛን ይደፋል? የወንዱ ነው የሴቱ? መልሱን ህሊናችሁ ይመልሰው፡፡ ይህ እንግዲህ ከህሊናችንና ከማንነታችን ጋር ምን ያክል የግብ ግብ ጥላቻ ውስጥ እንደገባን አንድ ማሳያ ነው፡፡ ለመሆኑኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን፣ ነብር ዥንጉርጉርነቱን አይለውጥምየተባለው ትንቢት እኛን ያካትታል? እኔ እንጃ! ከፈለጋችሁ ነብዩን ጠይቁት፡፡
ምክንያተ-ስድስቱ፡ የሴቶች የጀርባ ታሪክ፡፡ ከወንዶች የበለጠ የሴት ልጅ የጀርባ ታሪክ ከጋብቻ በፊት ይጠናል፡፡ ወንዱ ከክብረ ንፅህናዋ እስከ ዘር ማንዝሯ ብሎም ከዚህ በፊት አንሶላ ስለተጋፈፈቻቸው ወንዶች ሙልጭ አድርጎ ያጠናል፡፡ የወንዱ ክብረ ንፅህና በተግባር ሳይሆን በሚሰጠው ቃል ይረጋገጣል፡፡ እዚህ ላይ ተፈጥሮ ሴቶችን እንዳይዋሹ ጎድቷቸዋል ማለትም አለማለትም ትችላላችሁ፡፡ሴት ሳይንቲስቶች ሆይ የወንድ ልጅ ክብረ ንፅህና መመርመሪያ መሳሪያ እባካችሁ ስሩልንብለን ብንፀልይስ? ያም ሆነ ይህ ግን ሴት ልጅ ከማንነቷና ከባህርይዋ ጋር የተየያዙ መጥፎ ታሪኮች ከጀርባዋ ካሉ ሊያገባት ሲንሰፈሰፍ የነበረ ወንድ እንደ መስከረም ዝናብ ጥሏት እብስ ይላል፡፡
ምክንያተ-ሰባቱ፡ በብዙ ወንዶች ሲነሳ የምሰማው ሰባተኛው ምክንያት ከሴቶች ድብቅነት ጋር የተየያዘ ነው (ወንዶችንም ይጨምራል)፡፡ ሴቶቹ ያለፈ ማንነታቸውን ለወንዱ በግልፅ ከመናገር ወደ ኋላ ይላሉ፡፡ አንዳንዴም የውሸት መልስ ይሰጣሉ፡፡እውነትን ተናግሮ ከመሸበት ማደርየሚለው አባባል ትዳር ላይ የሚሰራ አይመስላቸውም፡፡ የተደበቀው ማንነት አንድ ቀን ሲታወቅ ዝቅ ካለ በነገር ከፍ ካለ ደግሞ በጥፊ ተላልሰው እህል ውሃቸው ያበቃል፡፡ ይህ ፊልሞቻችንም በየቀኑ የሚያሳዩን እውነታ ነው፡፡
ምክንያተ-ስምንቱ፡ ከሐይማኖትና ከባህል ማፈንገጥ፡፡ ለምዕራባውያን የባህል ወረራ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች የበለጠ የተጋለጡ መሆኑ አሌ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ በመሆኑም ከአገራችን ባህልና ሐይማኖት አስተምህሮ ውጭ የሆኑ የአለባበስ፣ የአነጋገር፣ የአመጋገብና የስነ ባህሪ ለውጦች ወደ ትዳር ለመግባት ትልቅ መሰናክሎች ናቸው፡፡ አውሮፓውያን ባህላቸውን ላኩልን እንጂ እነሱ አልመጡም፡፡ ስለዚህ ወንዶቹ የአውሮፓን ባህል ተከታዮችን ለጊዜአዊ ጓደኝነት፣ የኢትዮጵያን ባህል ተከታዮችን ደግሞ ለጋብቻ ሲመርጡ የምዕራባውያን ባህል ተከታዮች ሲቃብዙ ይኖራሉ፡፡ ዕድለኛ የሆኑት ቤተሰብ ፈቀዳ የመጣ ዲያስፖራ ወይም ለጉብኝት የመጣ አሮጌ ፈረንጂ ጠብሰው ወደ ውጭ ይኮበልላሉ ወይም ለተመላላሾቹ ቅምጥ ሆነው ይኖራሉ፡፡
በአጠቃላይ ለሴት ልጅ ከወንዱ የበለጠ ብዙ የጋብቻ መሰናክሎች በዙሪያዋ እንዳሉ ይሰማኛል፡፡ ሰው እንዳቅሙ ይናገራል፣ ይፅፋል፡፡ እኔም ምክንያቶችን በስምንት ገደብኋቸው፡፡ የቻለ ይቀጥል! ከዚያም ወደ መፍትሔው እንሸጋገር፡፡ ስለመፍትሔው ለማውራት ትንሽ ጥናት ቢጤ ያስፈልጋል፡፡ ከጥናቱ መልስ እስካሁን ላየናቸው ችግሮች መፍትሔ የሚሆኑ ሐሳቦችን ይዤ እቀርባለሁ፡፡

                   ((((((ክፍል (((((((ይቀጥላል!!!)))))04))))))

No comments:

Post a Comment