Monday, October 12, 2015

[ይድረስ ለአፍሪካ]


እንዴት ነሽ ሀገሬ እንዴት ነሽ አፍሪካ
የምስኪኖች ቋጥኝ የክፉች ዋርካ”
የምትል ግጥም ፅፌ ልልክልሽ አስቤ ነበር፡፡ ነገር ግን አንዱ አድርባይ አጎብዳጅ ስም አጠፋህ ብሎ ጆካ እንዳይለይ ብዬ ስለፈራሁ ለስለስ ባለ አማርዚኛ የሰላምታ ደብዳቤየን ልልክልሽ አሰብሁ፡፡ አኔ ምለው አፍሪካ እንዴት ነሽ ባያሌው? ኑሮ፣ ጤና እንዴት ነው?…ይሄ ፈረንጆቹ “undefined word” የሚሉትን ቃል እንዳትጠቀሚ፡፡ ማለቴ “ምንም አይል”፣ “cool” ምናምን እንዳትይኝ፡፡ እናቴ እኛም “ምንም አይል!” እያልን ነው ኑሮ ምናምንቴ አድርጎን የሄደው፡፡ አሁንማ “ኑሮ” የሚለውን ቃል ሲሰማ ሁሉ የሚበረግግ ምስኪን አፈር ነው፡፡ ብዙ ነው ማለቴ ነው፡፡ እባክሽ ደግሞ ተረት እንዳታወሪ፡፡ ይሄ ምንድነው እሱ…… “ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል” ….ምናምን እንዳትይ፡፡
መቃብር ሞቆም በርዶም አያውቅም…ሬሳ እንዴት መሞቅንና መብረድን ይለያል፡፡ ነው እኛን እንደ ሬሳ ቆጥረሽ ልትናገሪ ነው፡፡ በህግ አምላክ! ነገሩ ልክ ነሽ ሲያንሰን ነው፡፡ እውነት ሲያንሰን ነው! ከሬሳ የምንለየው ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀሳችን ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ እንደ ሬሳ በገነዙን ገመድ እንገነዛለን፡፡ሲያርዱን እንታረዳለን-ልክ እንደ አብርሃም በግ፡፡ በቆፈሩልን መቃብር እንቀበራለን፡፡ ይለቀስልናል፡፡ ምን ቀረን…ልጭምርልሽ….እንደ ሬሳ ካለምግብ መኖርም እየተለማመድን ነው…..አይበቃም፡፡

ደሞ እነዚህ ምዕራባውያን! ኤጭ! አናቴ አንቺን አልሰለጠነችም አሉሽ እንጂ የነሱ ነገር መሰልጠን ይሁን መሰይጠን አልተለየም፡፡ ስሚኝማ ይኸውልሽ….አሁን ባለፈው ወንድ ከወንድ፣ ሴት ከሴት ጋር ይጋባ አሉ፡፡ እንዴት ሆኖ አልናቸው…ይቻላል አሉን….. እሺ አልናቸው፡፡ አሁን ደግሞ ቅንዝርናቸው ቅጥ አጣና፤ የመቃብር ቤታቸው ውስጥ ሶፋ፣ ሻወር፣ ቴሌቭዥን፣ አልጋ….ኧረ ምኑ ቅጡ……ገባላቸው፡፡ አሁን ከአንድ የናጠጠ የአፍሪካ ሃብታም ቤት፣ የአንድ ምዕራባዊ መቃብር ቤት ያምራል፡፡ ስቀልድ መሰለሽ…እውነቴን ነው፡፡ ካላመንሽኝ ጉግል አድርጊ…..ማለቴ ኢንተርኔት ካለ….ሶሪ መብራት ሄደ እንዴ….እኔ ምለው አፍሪካ…ሚስት አወቅሽ ሲሏት……….የሚለው ተረት መሰረቱ ከነጮች ነው እንዴ?…እስኪ ምን ይሉታል አሁን የመቃብር ጌጥ…ኧረ ግፍ ነው፡፡ የአንቺ ልጆች መላጣ አስፋልት ላይ በእራፊ ጨርቅ ተጠቅልለው ተኝተው ቀን ፀሐዩ፣ ሌሊት ብርዱ በዚያ ላይ እራቡ እያሰቃያቸው ለሬሳ ይህን የመሰለ ቤት መስራት አውነትም የግፍ ግፍ ነው፡፡ ፈረንጅ ግን ግፍ ያውቃል?….እኔ እንጃ!….ነገሩ ፈረንጅ አይደለም ያንች ጥቁሮችም የግፍ ዘመንን አልፈው ግፍ መስራት ጀምረዋል፡፡ ያውም ለከት የሌለው ግፍ! እዚ እኛ ሰፈር ሀበሾችን ብታይ ብሰዋል፡፡ የፕላስቲክ ጎጆ በተወደደበት ሰፈር፣ መቃብራቸውን በጡብና የሚገነቡ ግፈኞች በዝተዋል፡፡ ይቅርታ ስለመቃብር ብዙ አወራሁ መሰለኝ….ደግሞ ደንግጠሸ ሞትኩ እንዳትይ….ለነገሩ ያው እንደ….ተይው በቃ ተውኩት፡፡ ለመሆኑ ጤንነትሽ እንዴት ነው፡፡ ትናንት ቅኝ ግዛት፣ ከዚያም ርሃብና እርዛት፣ ስደት፣ ዘረኝነት፣ አሁን ደግሞ የልጆችሽ የስልጣን ጥመኝነት ብዙ እንደጎዳሽ አውቃለሁ፡፡ ማለቴ ትንሽ ትንሽ አውቃለሁ፡፡ “ከ ባለቤቱ ያወቀ ……….” ይባል የለ…..ይባላል ነው፡፡ ለነገሩ ምዕራባውያን ገመናሽን በአደባባይ ሲዘከዝኩት፣ ያንቺ አፈቀላጤዎች ደግሞ ተሎ ብለው ድንኳን ያለብሱሻል፡፡ በምትኩ ምርጥ ዜና ይፈበርኩልሻል፡፡ ምን ዋጋ አለው ታዲያ …. “አለባብሰው ቢያርሱ …….” ነውና አበባሉ ውሎ አድሮ አውነቱ መውጣቱ አይቀርም፡፡ ይኸውልሽ እናት አህጉራችን….እኛ ተረት ስንቀምር ሌላው ፎቅ ይደረድራል……እኛ ጭንቅላታችንን ወሬ ስናስሞላ፣ ሌላው የባንክ ቡኩን በወፍራም ረብጣ ያስሞላል፡፡ ግን አፍሪካዬ፡
               “በው’ሸት ከምቆልል ሃብት እንደ ተራራ
                ድህነት ይሻላል ከህሊና ጋራ” 
ያለው ማን ነበር? ዋው ምርጥ አባባል፡፡ እኔ ነኝ ባክሽ፡፡ እራሴን አካበድሁ አይደል? ምን ላርግ ለምዶብኝ ነው፡፡ አንዷን ነገር በመቶ አባዝቶ ማውራት በሀገሬ ተለመደ፤ ታዲያ እኔ ምን ላርግ እናቴ…ሰው ከጎረቤት ነው የሚማረው፡፡

ይኸውለሽ አፍሪካ ዛሬ ደብዳቤውን የፃፍሁልሽ ዋናው ምክንያት ሰሞኑን አንድ ወሬ ሰምቼ ነው፡፡ አፍሪካ ዲቪ ልትሞላ ነው አሉኝ፡፡ እውነት ነው ግን አፍሪካ?…. ዲቪ ለመሙላት ወሰንሽ? ሼም ኦን ዩ! ሼም! ሼም!!!   ሼም!!!!............ነው አፍሪካ! ምን አሉኝ መሰለሽ መረጃ ምንጮቼ፡ ልጆቼ ዲቪ ዲቪ እያሉ ተሰቃይተው ከሚሞቱ ለምን እኔ ቀድሜ አልሄድም ብለሽ ነው አሉ ዲቪ ለመሙላት የወሰንሽው፡፡ የኛ አዝማሪዎች ነገሩ ቀድመው እንዲህ ብለው ተንብየውልሽ ነበር፡፡
“ችግሩ ስቃዩ ቢበዛ መከራው
ጥሎን ተሰደደ መሬቱም እንደ ሰው”
ይሄን አልሰማሽም ነበር? የኛ አዛኝቷ አፍሪካ! አሺ ባክሽ! እውነቱን ልንገርሽ ቀድሞውንም አንቺም ልጆችሽም በአካል አንጂ እዚህ ያላችሁት በመንፈስ እኮ ከሄዳችሁ ቆያችሁ፡፡ ነገሩ ሄድሽም ቀረሽም የነሱ ነሽ-የነጮች፡፡ ማለቴ ያው ታውቂዋለሽ፡፡ አይይ…አይይ ….አፍሪካ! ይህ አርቲፍሻል ትውልድ አንቺንም አኮ አርቲፍሻል አረገሽ፡፡ ለነገሩ እኛ ሸጠን ከምንጨርስሽ፣ ተሰደደች ቢባል ያምራል፡፡ እባክሽ አፍሪካ ባይሆን ስምሽን እንዳትቀይሪ፡፡ የምንሊክ፣ የኃ/ስላሴ፣ የንኩርማህ፣ የጀሞ ኬንያታ፣ የማንዴላ አጥንት ይወጋሻል፡፡ እኒ ጀግኖች ታግለው ነፃነትሽን እንዳላስመለሱልሽ በራስሽ ጊዜ ዘው ብለሽ ቅኝ ግዛት ውስጥ ገባሽ፡፡ ለነገሩ ቀድሞውንም ነጮች ወደዚህ መስመር አስገብተውሽ ነው የወጡት፡፡
ይህን ዘመን አይቼ እኔም ልጅሽ እንዲህ ብዬ ለትውልድሽ ተቀኘሁ፡፡
“ከሰው ዘር መገኛ ከአፍሪካውያን ምድር
ከሰሜን ኢትዮጵያ ከታራሮቿ ስር
ለጥቁር ነፃነት እሳት ነዶ ነበር!
ግን ግን………………….
በጀግኖቹ እራስ ያን ዘመን ተሻግረን
የነፃነት ትርጉም ጥቅሙ ስላልገባን
የእሳቱን ፀዳል ብርሃኑን አጥፍተን
ይኸው ከጨለማው ገባን ተመልሰን”
አፍሪካዬ እስከመቼ ነው በጨለማ የምትኖሪው፣ አስከመቼ ነው በድህነት የምትማቅቂው፣ እስከመቼ ነው እንቅልፋም የምትሆኝው?……እንዴ ነቃ በይ እንጂ!…..አኔ ምለው እኒህ ነጮች የድህነት ብቻ ሳይሆን የእንቅልፍ መርፌም ሰጠውሻል እንዴ?…..በይ ልተኛ ነው ሌላውን በሚቀጥለው እፅፍልሻለሁ፡፡

                            (((((((((((((((ይቀጥላል!!!)))))))))))))))))

2 comments:

  1. ምዕራባውያን ገመናሽን በአደባባይ ሲዘከዝኩት፣ ያንቺ አፈቀላጤዎች ደግሞ ተሎ ብለው ድንኳን ያለብሱሻል፡፡

    ReplyDelete