Wednesday, October 21, 2015

'የሰንደቅዓላማ ቀን'ን…በበርጫ

(ከ'አጠቃ'ዎች አንደበት)

ከሆነ ሰፈር ወደ ፒያሳ እየሄድሁ ነው፡፡ አቤት እነዚህ እረዳቶች ደግሞ….ሳንቲም ጨምር….ጠጋ በልየዕቃ ይህን ያክል ትከፍላለህ….ከዚይ ላይ አይቆምም! አሁን አሁን ታክሲ ውስጥ ያለው ጭቅጭቅ ስለመመረረኝ፤ ቅርብ ከሆነ በሁለት አግሬ ማቅጠን ጀምሬአለሁ፡፡ ራቅ ካለብኝ ደግሞ ጆሮዬ ውስጥ የምጨምረው ጥጥ ይዞ መግባት ጀመርሁ፡፡ ታዲያ ዛሬም እንደተለመደው እርዳቱ እንደ ሐምሌ መብረቅ ተሳፋሪ ላይ መጮህ ሲጀምር ቶሎ ብዬ መከላከያ ጋሻዬን ጆሮዬ ውሰጥ ሰካሁ፡፡ ምን ላድርግ ጆሮዬ ገና ብዙ ክፉ ደግ መስማት አለባት-ቢጠቅማትም ባይጠቅማትም፡፡ ታዲያ በዚህ መሃል ፀጉሩን እንደ ደረቀ ተክል ቅርንጫፍ ያንጨበረረ አንድ ወጣት ከጎኔ መጦ ቁጭ አለ፡፡ በአካል ጠጋ አልሁለት-ሶስተኛ መሆኑ ነው፡፡ በሃሳብ መጠጋጋት ግን በአካል እንደ መጠጋጋት ቀላል አይደልም፡፡ አይገርምም! በአካል እንደምንጠጋጋው በሃሳብም ብንጠጋጋ ምን አይነት ኢትዮጵያ ትፈጠር ነበር? ተውት በቃ፡፡ ይቅርታ ወደ ልጁ ልመለስ፡፡ ታክሲው በአንዴ ከህዝባዊ ሽታ ወደ ጫትና ሲጋራ ማዓዛ ተለወጠ፡፡ ደግሞ ጫትና ሲጋራ ሲቀላቀሉ እንዴት ነው የሚሸቱት!
አስቡት ማቀዝቀዣውን ቢጨምር ኖሮ ምን ምን እንደሚሸት እንጃ! አልወርድ ነገር ሒሳብ ከፍዬ፤ እንደ ጆሮዬ አፌንና አፍንጫዬን አላፍን ነገር ይሉኝታ ቢጤ ሸነቆጠኝ-አይ የሀበሻ ይሉኝታ! እንግዲህ ያው አንዴየጫት እንፋሎትና  የሃብታም ግሳትእየማግን እንድንኖር ተፈርዶብናልና ቻልኩት፡፡ የእነንትና እንትንስ ቢሆን….ተውኩት፡፡ በአራዳ ቋንቋአጠቃ ወጣት ወደ እኔ ዞር አለና……“ፍሬንድ ትናንት በዓል እንዴት ነበርአለኝ፡፡
የምን በዓል ነው አልኩት ኮስተር ብዬ….
እንዴ ፍሬንድ….ልጠብሪብኝ ነው……..የሰንደቅዓላማ ቀን ነዋአላከበርሽም እንዴ?” እየሳቀ፡፡
ይችና ናትና ነገር ፍለጋ! አልሁኝና በውስጤ……ይቅርታ ለምን ጠየቅኸኝአልኩት ኮስተር ብዬ
አይ ለጨዋታ ነው?”
አላከበርኩምማለቴ ሜዳ ወጥቼ አልዘመርሁም እንጂ ለአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ዘወትር በልቤ እዘምራለሁ፡፡ አየህማንነት በቀንና በቃል ብቻ የሚገለፅ ሳይሆን ከደምና ከስጋ ጋር ተዋህዶ የሚኖር እስትንፋስ ነውአልኩት እንደመፈላሰፍ ብዬ፡፡ኧረ ፍሬንድ አመረርሽ እንዴ?”….አለኝ እየሳቀ፡፡
ቢመረኝስ….. ስኳር ትጨምርልኛለህ?
ምን ችግር አለው….ከቀበሌ ከሰጡኝ
ከጫት የተረፈ የለህም እንዴ?
እህህህህ….(ሳቅአሁን ተመቸሽኝጭንቅ አልችልም ቀለል አድርግልኝ
እሺ አንተ በዓሉን አከበርህ?
አዎ…..ያውም ከጓደኞቼ ጋር…”
የትና እንዴት አከበራችሁ?
ሰፈራችን አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን-በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ አከበርን
አልገባኝምሰንደቅዓላማ ሰፈራችሁ ላይ ሰቅላችሁወይስ….
አይደለም ባክህ!“
እንዴት ነው ታዲያ…. ፈሊጥ አደረግኸው እኮ!
ይኸውልህበመጀመሪያ በዓሉን በማስመልከት ከሁለት ጓደኞቼ ጋር 400 ብር በርጫ ጨቅ አድርገን ቃምንበዚሁ የአገራችንን ባንዲራ አረንጓዴ ቀለም- በአረንጓዴ ወርቅ አከበርን ማለት አይደለም? ከዚያስ አትልም…”
እሺ ከዚያስ?
ከዚያማ ፍሬንዴ….በአረንጓዴው የጀመርነውን ምርቃና ለመስበር….እኛ ሰፈር ያለ ጃንቦ ሐውስ ገብተን በቢጫ የዋልያ ድራፍት አቀለጥነው….ተጠጣ ባክሽ ሞት ላይቀር!….ስምንት ስምንት ጃንቦ ጠጣንኧረ ከዚያም ይበልጣልየቆጠርሁትን ነው የነገርሁህ፡፡ አየሽ ፍሬንድ ቢጫውን ቀለም-በብሩህ ተስፋ አከበርን ማለት አይደለም!….መጠጣት እንዴት ደስ ይላል…. ወደን መሰለህ የምንጠጣው….ካልጠጣን እኮ ነገን በተስፋ አንኖርም
እሺ ከዚያስ? (ቀይዩን ለመስማት በጣም ስለጓጓሁ ስለደሰኮረው ፍልስፍና ለመጠየቅ አልፈለግሁም….ደሞ ፌርማታዬ ላይ ልደርስ ነው)…..እሺ ቀጥል! …አልኩት….ፍጠን ቶሎ በሚል አይነት እይታ
ከዚያማ ሞቅ ብሎን ነበርና ከሰው ጋር ተጣላን፡፡
ከማን ጋር?
ከዚያው ከሚጠጡ ሰዎች ጋር…. አንዱ ምላሰ ረጅም ጓደኛችንእናትህን……” ብሎ አንዱን ሰደበውና ቅውጥ ያለ ጠብ ተፈጠረ፡፡
ከዚያስ?
ከዚያማ ሁለቱ ጓደኞቼ ከጠላት በተላከ የጃንቦ ጠርሙስ ሚሳየል በደም ተላወሱ፡፡ እኔም ይኸው በእሱ ጦስ እጄን ትንሽ ተጎድቻለሁአለና የብርጭቆ ስባሪ የጋሸረውን እጁን ሰሚዙን ወደላይ ሰብስቦ አሳየኝ፡፡
እሺ ከዚያስ ምን ሆነ?
ከዚያማ ይኸውልህ የባንዲራችንን ቀዩን ቀለም በደማችን አክብረን…..ጭንቅላታቸውን አሰፍተን ወደ ቤታችን ገባን፡፡ አየህ ሰው በምላሱ ሲያከብር እኛ በተግባርአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩንአከበርንአለኝ እየሳቀ…,
                   ከዚህ ላይ ሴቶች በአንድ ወቅት የገጠሙት ግጥም ትዝ አለኝ፡፡ እንዲህ ይላል፡
እኛ ሴቶች ለእናት ሀገራችን
28 ቀን ይፈሳል ደማችን
ይህንን ወደ እኛ ቀይሬ ልቀኘው ብዬ አሰብሁና እንዲህ የሚል ግጥም ገጠምሁ (ሰሙን ብቻ አዳምጡ)
እኛ ወጣቶች ለእናት ሀገራችን
በስካር ጦርነት ይፈሳል ደማችን
ከጎኔ የተቀመጠውን ልጅ ምንም ማለት አልፈለግሁም……ትንሽ የግርምት ሳቅ ሳቅሁና …..ከፌርማታዬ ስለደረስሁ በል ቻው ወንድሜ ብዬው ወረድሁ፡፡
ፒስ ፍሬንድ ይመችሽብሎኝ ከእነጫቱ ሽታ ታክሲው ውስጥ ቀረ፡፡
የትውልድ ማንነት……ከየት ወደየት….” የሚል መፅሐፍ ፀሐፊ ናፈቀኝ!!!.........ማን ያውቃል አንድ ቀን ወይ እኔ እሞክረው ይሆናል……….እስከዛው ግን………
             “ዘላለማዊ ክብር ለማንነት አርማችን



No comments:

Post a Comment