Wednesday, June 15, 2016

‹‹‹‹አዎ መምህር ነኝ!….›››

የትውልዱን ነገ ያዘልሁኝ በ ጀርባ
መጪውን እያሰብሁ በ ህልም የምባባ
አዎ መምህር ነኝ የእውቀት ደብተራ
ከ ፈጣሪ በታች ሰውን የምሰራ

የ ጠመኔ ብናኝ በላጠው መዳፌ
በ መለፍልፍ ብዛት በ ደረቀ አፌ
ሰው ሃብታም የማደርግ ድህነት ታቅፌ
አዎ መምህር ነኝ
የእውቀት ደብተር እንጂ የባንክ ቡክ የሌለኝ

እንደ ደረሰች ሴት እውቀትን እያማጥሁ
ጠመኔ ታቅፌ ከ ትውልድ ፊት የቆምሁ
ነገን እንዲሸከም ጮሄ የምሞግት
ደሞዝ ቀን የራቀኝ እንደ ዳግም ምፃት
አዎ መምህር ነኝ!
የመቶ ብር ምስል የሚያስደነግጠኝ

የቱጃር ቀበጦች የዋሌት ግልምጫ
ገንዘብ የሚያጋብስ የ ነጋዴ ሩጫ
ያላስበረገገኝ
ያላስደነበረኝ
ቁርሴን ተራምጄ ተማሪ ፊት ምገኝ
አዎ መምህር ነኝ!
እስትንፋስ ምዘራ ትንፋሽ እያጠረኝ

የ ለበስኩት ጃኬት ቢያልቅም ከጫንቃዬ
ሁለተኛ እግሬ ብታልቅም ጫማዬ
ምንም ቢቸግረኝ ከፊትህ ማልጠፋ
የ እውቀት አባትህ ነኝ ለነገህ ምለፋ

በል እንግዲህ ልጄ አስተውለህ ስማ
እኔ መምህር ነኝ በችግር ማልደማ
“ካለው ወስዶ መስጠት
በ እጅ ይዞ ንፍገት”
እንደዚህ ቢሆንም~የ አለሙ አባዜ
ትርፌ አንተ ነህ ልጄ~አይደለም ደሞዜ
        ከ ዘላለም፡ 2008 ዓ.ም
___________________________

(አበርክቶ፡ በትጋት ዳግም ለወለዱን መምህራን ሁሉ) 

No comments:

Post a Comment