Wednesday, June 22, 2016

የብሔራዊ ቴአትር አዲሱ ስያሜ…..

አንዳንዴ ይገርመኛል፡፡ የዳበረ ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ እንደሌለው ሀገር ለምን ወደ ፈረንጅ ቋንቋ እንደምንሮጥ አይገባኝም፡፡ እነ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን የመሳሰሉ የቋንቋ ሊቃውንት በፈለቁበት ሃገር ለአፍርጅኛ ቃላት ትርጉም ከመፈለግ ይልቅ አዳቅሎ መጠቀምን እንደ ባህል ከለመድነው ሰነባበትን፡፡

………ይህ ድርጊት ከግለሰብ አልፎ፣ የሀገሪቱ ትልልቅ ተቋማት ሳይቀር የበሽታው ሰለባ ከመሆን አልተረፉም፡፡  ለምሳሌ፡ ‘ሚሊኔም’፣ የእድገትና የ ‘ትራንስፎርሜሽን’ እቅድ፣ የኢትዮጵያ ‘ፕሮድካስቲንግ ኮርፖሬት’፣ ‘ፐፕሊክ ሰርቪስ’ ና የመሳሰሉት ደጋግመን የምንሰማቸው የእንግሊዘኛ ቃላት ድቅሎች ሲሆኑ የተፃፉት ግን በ አማርኛ ነው፡፡

አንዳንዴ ሳስበው… ከብዙ ጊዜ በኋላ ብዙ ስሞቻችን ተቀይረው በ እንግሊዝ ቅኝ ግዛት ተይዘው ከነበሩ አገሮች ጎራ መመደባችን የሚቀር አይመስለኝም፡፡
ለዛሬ ትዕዝብቴን ያጫረው ግን የአገሪቱን ጥበብና ባህል ለማሳደግ ከ 60 ዓመት በላይ ደፋ ቀና ያለው ብሔራዊ ቴአትር ይህንን ስህተት ሲደግመው ነው፡፡ ከ ስዕሉ አንደምታዩት አዲሱ የብሔራዊ ቴአትር ኪነ ህንፃ ንድፍ ላይ “New National Professional Theater” ለሚለው የእንግሊዘኛ ስም…. “አዲሱ ብሔራዊ ፕሮፌሽናል ቴአትር”…….የሚል የአማርኛ ቅያሬ ስም ተቀምጦለታል፡፡

…………….ፕሮፌሽናል ለሚለው ቃል እንዴት ትርጉም ይጠፋል፡፡ እስኪ እኔ ልሞክረው፡ ፕሮፌሽን ማለት ሙያ ሲሆን፣ ፕሮፌሽናል ማለት ደግሞ ባለሙያ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሲተረጎም “አዲሱ ብሔራዊ የባለሙያ ቴአትር” ይሆናል፡፡ ምን አልባት …የባለሙያ የሚለው ቃል አላስደሰታቸው ይሆናል፡፡ ………ግን ማንነት ነው፡፡ ማንነትን እየረገጡ ማንነትን ማስተዋወቅና ማሳደግ አይቻልም፡፡…….ማንነት በፈለግህ ሰዓት አውልቀህ የምትጥለው ስትፈልግ ደግሞ የምትለብሰው አይደለም---አብሮህ የሚኖር እንጂ፡፡ 

………..ከዚሁ ጋር ተያይዞ “አዲሱ ቴአትር ቤት የድሮው ፈርሶ ነው የሚሰራው” የሚል ወሬ ይናፈስ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ስለ እውነትነቱ ግን በቂ ማስረጃ የለኝም፡፡ ተጨማሪ ይሁን የዋናው አካልም በቂ ማስረጃ የለኝም፡፡ በሂደት የምናየው ይሆናል፡፡ እውነት ከሆነ ግን ለእኔ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ …………..በ አንድ ወቅት ፕሮፌሰር ሽፈራው የጥንት ህንፃዎችን በአዲስ መተካት ያለውን ታሪካዊና እሴታዊ ክስረት በተመለከተ ያቀረቡት ጥናት ትዝ ይለኛል፡፡ ቢያንስ 50 ዓመት ያለፋቸው ህንፃዎች መፍረስ እንኳን ካለባቸው ጥልቅ ጥናት ሊደረግባቸው ይገባል፡፡

………ይህን የምለው ፀረ ልማት ስለሆንሁ አይደለም፡፡ ማንም ማደግን፣ መበልፀገንና መሻሻልን አይጠላም፡፡……ግን ማስተዋል ያለብን የሀገር እድገት በህንፃዎች ጥርቅም ብቻ አይመጣም፡፡ …………..የበለፀገ ታሪክ፣ እሴትና ባህል ለማህበረሰብ እድገትና ትስስር ያለውን ፋይዳ ማንም አሌ የማይለው ሀቅ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ አንዴ የፃፍሁት ግጥም ትዝ አለኝ፡

“ትውልድ የሚያገናኝ~የማንነት ድልድይ~እስካልሰራን ድረስ
ነግ ትውልድ ይመጣል~የቆመ የሚንድ~የተሰራ ሚያፈርስ”

…….በ ነገራችን ላይ ብሄራዊ ቴአትር ውስጥ ያለው ህንፃ ብቻ አይደለም፤ በታዛው ስር የተከናወኑ እልፍ ሁነቶች አሉ፡፡ እነዚህ ሁነቶች ከማይጨበጡ የሀገሪቱ ሃብቶች  (Intangible country treasures) ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡ ይህ ሃሳብ በልማትና በማደስ ሰበብ የሚፈርሱ ታሪካዊ ዳራ ያላቸው ህንፃዎችን፣ አብያተክርስቲያኖችንና መስጊዶችንም ያካትታል፡፡
……ስለዚህ ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነውና ብሔራዊ ቴአትሮች እባካችሁ እናንተ እንኳ ስሙን ሀገረኛ አድርጉት፡፡ ሌሎችም ልብ ይስጣችሁ፡፡


No comments:

Post a Comment