Saturday, February 25, 2017

መ  ነ  መ  ነ  ች   እ  ው  ነ  ት
ብርሀን ደበዘዘ~ጨለማ ደመቀ
ሰው ከሰው ሲቀርብ~ሰው ከእራሱ ራቀ
ማመን መተማመን~ጥለው ተሰደዱ
ፍርሃት ጥርጣሬ~ ልብ ተዋሃዱ፤
አይንና አፍንጫ~ጉርብትና እረሱ
መተዛዘን ቀርቶ~ይሙት ሆነ ክሱ፤
ቅትሎ…. ስቅሎ
ቅትሎ….ስቅሎ
ይላል ግብረ ቃኤል~ክፋት ጀርባ አዝሎ፤

Thursday, February 23, 2017

"አክሚኝ...፩"

አመመኝ
አልችል ስል ተኛሁኝ
.
.
ተኝቼም ሲብሰኝ~በሽታዬ ሲከር
ሄድሁኝ ወደ ሃኪም~ህመሜን ላማክር
.
.
.
ሆስፒታል ገብቼ~ደሜን መረመሩኝ
ትዝታሽ ነበረ~እኔን ያሳመመኝ

Monday, February 20, 2017

ከ ቢሾፍቱ ሐይቅ አፋፍ ላይ

(ከ ፕሮፌሰሩ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ)

ቢሾፍቱ ነፍስን የሚገዙ ትንንሽ ሀይቆችን በተፈጥሮ የተቸረች ምርጥ ከተማ ናት፡፡ በተደጋጋሚ ጎብኝቻታለሁ፡፡ ግን አልጠግባትም፡፡ ሐይቆቿ ነፍሴን ይገዙታል፡፡ ከ እራሴ ጋር እንዳወራ እድል ይሰጡኛል፡፡ ከ ዓለም ጫጫታ ወጥቼ ከ ማዕበሉ ጉዞ ጋር ነፍሴን አስማምቼ በምናብ እንድመጥቅ፣ ከ ሀሳቤ ህመሜ ለ አፍታም ቢሆን እንድላቀቅ ይረዱኛል፡፡ ሐይቅ እወዳለሁ፡፡ ጣና፣ ደብረዘይት፣ ዝዋይ፣ ሐዋሳ፣ ዘንገና፣ አለማያ……በተጋጋሚ ባያቸውም አልጠግባቸውም፡፡ ሁሌም ከጉያቸው ቁጭ ብዬ የሚተነፍሱትን አየር ወደ ውስጤ መማግ ያረካኛል፡፡ ንፁህ አየራቸውን ስስብ፣ አዲስ ተስፋና አዲስ ህይወት ይታየኛል፡፡ ከ ጀርባዬ ያለ ሸክም የተራገፈ ያክል ነፃነት ይሰማኛል፡፡ ጥሎብኝ ሐይቅ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮን አደንቃለሁ፡፡
ከ ቢሾፍቱ ፈርጦች ውስጥ በ ርዕሰ ከተማዋ ስም የተሰየመችው ቢሾፍቱ ሐይቅ አፋፍ ላይ ቁጭ ብዬ ከማዕበሉ ጋር በመጫወት ላይ ሳለሁ እርዳታዬን ፈልጎ አንድ አሮጌ ፈረንጂ ወደ ተቀመጥሁበት ወንበር መጣ፡፡ (እዚህ ጋ ያዝ ላድርገውና ስለ ቢሾፍቱ ሐይቅ ትንሽ ልበል፡፡)

Wednesday, February 15, 2017

በ እንተ ቫላንታይን_ ፪

(እለትና ማግስት)
ከ ግብረ መልስ ወደ ማረፊያ ክፍሌ ስገባ……..የፈጣሪ ያለህ!  ክፍሉ የ ፋሽን ማሰልጠኛ ወርክሾፕ መስሏል፡፡

“የማይጠቅም መሬት ያበቅላል ደደሆ
የፈራሁት ነገር መጣ ድሆ ድሆ”
……..እንዲሉ……..ሁላችንም ፈረንጂ ካመጣው የባህል ወረራ በምንም መንገድ ማምለጥ እንደማንችል ገባኝ፡

ከሃላፊዎች ቀጭን ትዕዛዝ የተቀበሉ የአልጋ ከፍል ሰራተኞች ያለ የሌለ ጥበባቸውን ተጠቅመው የቫላንታይን ቀን እንዴት ከጥበብ ጋር እንደሚገናኝ አልጋው ላይ በሰሩት ዲኮሬሽን ሊያሳዩን ሞክረዋል፡፡…………..አራት ማዕዘን፣ ልብ ቅርፅ፣ዲያጎናል…..ምን አለፋችሁ የሌለ የለም፡፡….ምን አልባት ከ አገልግሎቱ በተጨማሪ ሆቴሉ የዲይዛይን ትምህርት ይሰጣል መሰለኝ፡፡…………ክፍሉ በፅጌረዳ አበባ መዓዛ ታውዷል፡፡ ከ እብድ መሃከል የተቀመጠ ሰው ጤነኛ ነኝ ቢል ማንም አያምነውም፡፡………..የተረዳሁት ነገር ሁላችንም ታመናል፡፡………ጨዋታው የ 6 እና የ 9 ቁጥር ነው፤ ሰዎች በራሳቸው ዕይታ ያያሉ፣ ያዩትንም ያምናሉ፡፡……. ያመኑትን ግን ሌሎችን ካልተቀበላችሁ ብሎ በግድ መጫን ትክክል አይደለም፤ ይህን ለማድረግ መጀመሪያ በሌሎች ቦታ ሁኖ ማየት ግድ ይላል፡፡……ውድ አድማጮች አስተውሉ፣ እኔ በዓሉን አልነቅፍም……..የበዓሉን አንድምታ እንጅ! ተከተሉኝ!

በ እንተ ቫላንታይን

(ለቀይ አምላኪዎች-ከ ዘይት ተራራ እስከ ቀይ ፓርቲ)


የተዘጋጃችሁ፣ ሩጫ የጀመራችሁ፣ በዝግጅት ላይ ያላችሁ፣ የተደናገራችሁና ግራ የገባችሁ…አንድ ቀኝ መላ ልንገራችሁ፡፡ በቅድሚያ ለቫላንታይን (ቅድመ ቃለ አመጣጥ=አማርኛ፤ ትርጉም=ባለን ታዬን……ዝርዝሩን በሌላ ጊዜ) ዋዜማ እንኳን አደረሳችሁ፡፡ ከ ደም ውጭ ቀይ የሆነ ነገር ለምሸጡ ሁሉ ይሄን ቀን እሺ ያድርግላችሁ፡፡ አሜን በሉ! (ሀሌ ሉያ እንዳትሉ!....ኢየሱስ ደም ሰጠ እንጂ ቀይ ልብስ አልሰጠም፣አልሸጠም)……

የአዲስ አበባ ህዝብ ከሰኞ እስከ አርብ ወጥሮ አዲስ አበባ ውስጥ ይሰራል፡፡ ቅዳሜና እሁድ ደግሞ ደብረ ዘይት ውስጥ ወጥሮ ይሰ’ራል! (ሳቅ)……………………………..(ይህ አረፍተነገር በደምና በወዝ የሚኖሩ ና ከስኳር በሽታ ነፃ የሆኑ የህዝብ አገልጋዮችን አያካትትም፡፡)