(ሳይቃጠል በቅጠል፤ በዘላለም ጥላሁን) Must read!
እስኪ ልጻፍ፡፡ ዛሬ ካልጻፍሁ መቼ ልፅፍ ነው፡፡ እናቴ ጓዳውን፣ አባቴ ጋጣውን ተከፋፍለው እስኪለያዩ መጠበቅ የለብኝም፡፡ ምን ማለት እንደፈለግሁ አዊ ዞን የሚኖሩ ወጣቶች ይረዱኛል፡፡ ወደ ዋናው ነጥብ ከመግባቴ በፊት አንዴ ጠብቁኝ ‹‹የዘር ፖለቲካን ሰፈር ድረስ የዘራውን ሰው ሁሉ ልራገም››….‹‹ልጅ አይውጣላችሁ!›› ጨርሻለሁ!.....
እኔ ግን ይች ሀገር ታሳዝነኛለች፡፡ እንደ ዶሮ ብልት ተከፋፍላ ተከፋፍላ ማለቋ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ዛሬ ማንሳት የፈለግሁት ‹‹ጉዳዩ እየገፋ ስለመጣና የእዚህ ጉዳይ አራማጆች ዛሬ አዲስ አበባ ‹‹ራስ አምባ ሆቴል ›› ሲመክሩ ስለዋሉ ነው››
አሁን ‹‹አገው ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት›› የሚሆነው በየት በኩል ነው?……..ይህን ስል የአገውን ማህበረሰብ ማንነት ማሳነሴ አይደለም፡፡ ራሴን ማሳነስ ስለሚሆን፡፡ ሃቁ የአገው ህዝብ የራሱ ቋንቋ አለው፡፡ አብሮት ከሚኖረው አገውኛ ከማይናገረው ህዝብ የተለዬ ባህል እና ትውፊት ግን የለውም፡፡ ለጊዜው ትኩረቴን ‹‹የአዊ ዞን ህዝብ›› ላይ ላደርግ፡፡ ተከተሉኝ፡፡ ወደ ጉዳዩ ለመንደርደሪያ እንዲሆን እና ምሁራን ጉዳዩን በትኩረት እንዲያዩት ፍንጭ ለመስጠት ያህል እንዳንድ አሃዛዊ መረጃዎችን ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡