Thursday, August 16, 2018

የአዊ (አገው ምድር) የፈረስ ጉግስ ባህል

70 ዓመታት በላይ የሆነው ‹‹አዊ የፈረስ ማህበር›› ባህሉን ጠብቆ በማቆየቱ ‹‹ቅርስና ባህል ዘርፍ›› ለዘንድሮው በጎ ሰው ሽልማትከተመረጡ ሶስት ዕጩዎች አንዱ ሁኗል፡፡ የፈረስ ጉግስ ባህሉ ዝም ብሎ ለመዝናኛ የሚሆን ብቻ አይደለም፡፡ የማህበራዊ ስነ-ሰብ አጥኝዎች በአግባቡ ባያጠኑትም ቅሉ፣ የራሱ ታሪካዊ አመጣጥ አለው፡፡ ከታሪካዊ እውነታዎች እና አሁን የፈረስ ጉግስ ከሚዘወተርባቸው ሁነቶች ተነስቶ ሶስት መላምቶችን መገመት ይቻላል፡፡
1) አንደኛው ከመከረኛው ጦርነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡
መኪና፣ አውሮፕላን እና ዘመናዊ የጦር መሳሪያ በሌለበት ዘመን አብዛኛው የእርስ በርስም ሆነ ከውጭ ጠላት ጋር ይደረጉ የነበሩ ውጊያዎች የሚከወኑት በጦር እና ጎራዴ በሚደረግ የጨበጣ ውጊያ ነው፡፡ የጨበጣ ውጊያን በድል ለማጠናቀቅ ደግሞ ፈረስ ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ የአድዋ ጦርነት በፈረስ አጋዥነት ለድል እንደበቃ ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ ‹‹ባንዳ እርግማን›› አፋችን የሾለውን ያህል ‹‹ፈረሶችን›› አመስግነናቸው አናውቅም፡፡ ለኢትዮጵያ ነፃነት ‹‹ባንዳዎች›› እና ‹‹ከፈሪዎች›› ይልቅ ፈረስ የነበረው አስተዋፅኦ ታላቅ ነው፡፡ ፈረስ ለቀደሙ ነገስታት ባለውለታ፣ የህይወታቸው አለኝታ ነበር፡፡ ለዚህም ይመስላል ብዙ ነገስታት አባታቸው ይልቅ የፈረሳቸው ስም ጎልቶ የሚወጣው፡፡ ለምሳሌ የአፄ ቴወድሮስን ብናነሳ፡
‹‹ታጠቅ ብሎ ፈረስ፣ ካሳ ብሎ ስም
አርብ አርብ ይሸበራል፣ ኢየሩሳሌም››……ተብሎ ተገጥሞላቸዋል፡፡

/መንግስቱ ሐይለማሪያም ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ ያለውን እና ለኦጋዴን ጦርነት በአንድ ቀን 300 ሰራዊት ያሰለጠኑበትን የጦር ሰፈር በጀግናው በአፄ ቴወድሮስ ፈረስ ስም ‹‹ታጠቅ›› ብለው መሰየማቸው በድንገት የሆነ አይደለም፡፡ ብዙ ትችት የደረሰበት ቴወድሮስ ካሳሁን ጥቁር ሰውአልበሙ ውስጥ /አዝማች ባልቻ ሳፎን ‹‹ባልቻ አባቱ ነፍሶ›› ብሎ ማቀንቀኑ በስህተት ወይም ዜማ ለማሳመር ሳይሆን ይህን ሃቅ በመረዳት ይመስለኛል፡፡
2) ከቤተክርስቲያን ክብረ በዓል ጋር በተያያዘ
የፈረስ ጉግስ ከሚዘወተርባቸው በዓላት መካከል ‹‹ጥምቀት በዓል›› እና ‹‹ዓመታዊ የንግስ በዓላት›› ቀዳሚዎች ናቸው፡፡ እግር ጥሎት የጥምቀት በዓልን አገው ምድር ያከበረ፣ ከታቦቱ በረከት ባለፈ በፈረስ ጉግሱ ተዝናንቶ ይመለሳል፡፡ ትንሽ የሚሞክር ከሆነም የአንዱን ፈረስ ተቀብሎ ‹‹አይሞሎ›› ማለትን ማንም አይከለክለውም፡፡ ከንግስ በዓላት ጋር ተያይዞ የሚደረገው ጉግስ ‹‹ቅዱስ ታቦቱ›› ክብር የሚደረግ ነው፡፡ ባለፈረሶች የራሳቸውን ዜማ እየዘመሩ ታቦቱን ዙሪያውን አጅበውት ይዞራሉ፡፡ ታቦቱ በሰላም ወደ መንበሩ ከመለሱ በኋላ ወደ ሜዳ ሄደው ፈረስ ጉግስ ይጫወታሉ፡፡
3) ከለቅሶ ጋር በተያያዘ
ዘመናዊ የትራንፖርት አገልግሎት ባልነበረበት ዘመን፣ የሩቅ ዘመድ ወዳጅ ሲሞት ፈጥኖ ለመድረስ፣ ወዳጅ ዘንድ ሄዶአይንን ለማበስትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው/ አሁንም አለው፡፡ በተለይ ሟች የጦር ዘማች ከሆነ በባህሉ መሰረት ‹‹ትልቅ የፈረስ ሰልፍ›› ይደረግለታል፡፡ ለሌሎች በእግር ሰልፍ የሚደረገው ሙሾ፣ ቀረርቶ እና ፉከራና ለዘማች ግን ‹‹በፈረስ ሰልፍ››ይደረግለታል፡፡ ለቅሶ ላይ ጉግስ ባይኖርም ‹‹ ስጋር›› ግን የተለመደ ነው፡፡ ይህ መጀመሪያ ላይ ካነሳነው ‹‹የጦርነት አውድ›› ጋረ በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አንድ ነገር ያሳያል፡፡ አገው ምድር ውስጥም ሆነ በአጎራባች የጎጃም ግዛቶች ፈረስን እንደመሳሪያ ተጠቅመው ለነፃነት ይታገሉ የነበሩ ጀግኖች እንዳሉ ያሳያል፡፡ በዘመን ሂደት ስማቸው የተዘነጋ አንዳድ ሰዎችን ልጥቀስ፡ ‹‹ራስ ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ፣ ራስ ቢተወደድ መንገሻ አቲከም፣ ፊታውራሪ ባይህ፣ ቀኝ አዝማች ስሜነህ (ለደርግ አልገዛም ብሎ ከደርግ ጋር እየተዋጋ ወደ ሱዳን የሸሸ) ግራ አዝማች አበጋዝ፣ ፊታውራሪ ሙላት (የደራሲና ፀሀፌ ተውኔት አያልነህ ሙላት አባት) የመሳሰሉት በከፊል ይጠቀሳሉ፡፡
ሲጠቃለል
የዘንድሮውን  ሽልማት ‹‹አዊ ፈረስ ማህበር›› ማበርከት ባህሉን ጠብቀው ላቆዩት ማበረታቻ፣ በፈረስ ጫንቃ ሁነው ሲዋጉ ለተሰው ጀግኖች መታሰቢያ፣ ደመ ነፍስ ባይኖራቸውም በዱር በገደሉ ለኢትዮጵያ ነፃነት ለተዋደቁ ፈረሶች ምስጋና ይሆናል፡፡

No comments:

Post a Comment