(ሳይቃጠል በቅጠል፤ በዘላለም ጥላሁን) Must read!
እስኪ ልጻፍ፡፡ ዛሬ ካልጻፍሁ መቼ ልፅፍ ነው፡፡ እናቴ ጓዳውን፣ አባቴ ጋጣውን ተከፋፍለው እስኪለያዩ መጠበቅ የለብኝም፡፡ ምን ማለት እንደፈለግሁ አዊ ዞን የሚኖሩ ወጣቶች ይረዱኛል፡፡ ወደ ዋናው ነጥብ ከመግባቴ በፊት አንዴ ጠብቁኝ ‹‹የዘር ፖለቲካን ሰፈር ድረስ የዘራውን ሰው ሁሉ ልራገም››….‹‹ልጅ አይውጣላችሁ!›› ጨርሻለሁ!.....
እኔ ግን ይች ሀገር ታሳዝነኛለች፡፡ እንደ ዶሮ ብልት ተከፋፍላ ተከፋፍላ ማለቋ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ዛሬ ማንሳት የፈለግሁት ‹‹ጉዳዩ እየገፋ ስለመጣና የእዚህ ጉዳይ አራማጆች ዛሬ አዲስ አበባ ‹‹ራስ አምባ ሆቴል ›› ሲመክሩ ስለዋሉ ነው››
አሁን ‹‹አገው ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት›› የሚሆነው በየት በኩል ነው?……..ይህን ስል የአገውን ማህበረሰብ ማንነት ማሳነሴ አይደለም፡፡ ራሴን ማሳነስ ስለሚሆን፡፡ ሃቁ የአገው ህዝብ የራሱ ቋንቋ አለው፡፡ አብሮት ከሚኖረው አገውኛ ከማይናገረው ህዝብ የተለዬ ባህል እና ትውፊት ግን የለውም፡፡ ለጊዜው ትኩረቴን ‹‹የአዊ ዞን ህዝብ›› ላይ ላደርግ፡፡ ተከተሉኝ፡፡ ወደ ጉዳዩ ለመንደርደሪያ እንዲሆን እና ምሁራን ጉዳዩን በትኩረት እንዲያዩት ፍንጭ ለመስጠት ያህል እንዳንድ አሃዛዊ መረጃዎችን ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡
እንደ ማዕከላዊ ስታቲስቲክ መረጃ፣ አዊ ዞን ውስጥ ከሚኖረው ማህበረሰብ ውስጥ፣ 53.38 ፐርሰንቱ አፉን በአማርኛ ቋንቋ የፈታ ሲሆን፣ 45.04 ፐርሰንቱ አፉን በአገውኛ ቋንቋ የፈታ ነው፡፡ የተቀሩት 1.58 ፐርሰንት ሰዎች ደግሞ በሌሎች ቋንቋዎች የፈቱ ናቸው (Central Statistics Agency, 2007):: በ1997 ዓ.ም በድርቅ ምክንያት ከዋግ ህምራ ብዙ አባዎራዎች ከእነቤተሰቦቻቸው አዊ ዞን ውስጥ መጠው ከመስፈራቸው በፊት፣ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ባደረገው የቤት ቆጠራ፣ 49.97% ለሚሆኑት ብሔር የሚለው ቦታ ላይ ‹‹አገው›› ተብሎ የተሞላ ሲሆን፣ 48.6% ለሚሆኑት ደግሞ ‹‹አማራ›› ተብሎ ሲሞላ ለቀሪዎቹ ‹‹ጉሙዝ›› እና መሰል ስሞች ተሞልተዋል፡፡
እኔ እራሴ 2006 ዓ.ም ላይ በዞኑ ባደረግሁት 6000 አካባቢ ሰዎችን ባካተተ የዳሰሳ ጥናት 99.1 ፐርሰንት የሚሆኑት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ሲሆኑ፣ 40% አካባቢ በት/ት ገበታ ላይ ያሉ ህጻናት እና ወጣቶችን፣ እንዲሁም 39.6% ማንበብና መፃፍ የማይችሉ ሰዎችን የያዘ ዞን ነው (URL: https://doi.org/10.1186/s12886-018-0868-1)፡፡
ስለ ዞኑ አሃዛዊ ስብጥር ይህን ያህል ካልኩ፣ ወደ አንድ ቃላዊ ማስረጃ፣ እንዲሁም አንዳንድ መፅሃፍት ላይ ስለ ተፃፈ ታሪካዊ ነገር ልውሰዳችሁ፡፡ አሁን አዊ ዞን ውስጥ የሚጠሩ ሰባት ወረዳዎች ስያሜያቸው፣ ከዋግ-ህምራ ፈልሶ በመጣ አንድ አባት ልጆች ስም እንደተሰየመ ይነገራል፡፡ ይህን አፈታሪክ (oral literature) አብዛኛው ሰው ይቀበለዋል፡፡ እኔም እቀበለዋለሁ፡፡ ነገር ግን ከዚያ በፊት በዚህ ቦታ ስለነበሩት ሰዎች ምንም መረጃ የለም፡፡ አለቃ ተክለእየሱስ ዋቅጅራ ከላሊበላ ጋር አገናኝተው የሚያነሱት አንድ ታሪክ ቢኖርም ከዚህ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡
ከላይ ካነሳነው የአሃዝ መረጃ ተነስተን ግን አንድ ነገር መገመት ይቻላል፡፡ የአገዎች አባት ከሰቆጣ ተነስተው ወደ ጎጃም ሲመጡ በተለመደው እንግዳን የመቀበል ባህሉ ተቀብሎ እንዳስተናገዳቸውና መኖር ሲፈልጉም ፈቅዶ አቅፎ እንዳኖራቸው፡፡ በሂደትም ዘራቸው እየበዛ ሲሄድ ከሌላው ጋር ተጋብተውና ተዋህደው እንደኖሩ፡፡ በዚህ ሁሉ የማህበረሰብ ሂደት ውስጥ ግን ቋንቋቸውን ጠብቀው፣ የሌሎችንም አውቀው እንደኖሩ፡፡ ባህላቸውን ጠብቀውም፣ ከሌሎች ጋር አዳቅለውም በህብረት እንደኖሩ እንገነዘባለን፡፡ የጎጃም ህዝብ አቃፊ እንደሆነ ደግሞ ብዙ ማሰረጃዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡
1ኛ) የዳሞት (የጋፋት ህዝብ)፡ በ15ኛው መቶ ክ/ዘመን በግራኝ ጦርነት እና በኦሮሞ ህዝብ መስፋፋት ምክንያት ከአሁኗ ‹‹አዲስ አበባ›› እና በስተደቡብ ይኖሩ የነበሩት የዳሞት ህዝቦች ወደ ጎጃም ፈልሰው፣ ከጎጃም ጋር ተዋህደው፣ ቋንቋቸው በሂደት ቢጠፋም ‹‹ዳሞት›› የሚለውን ስም አትመው ‹‹ጎጃሜ›› የሆኑ ህዝቦች ናቸው፡፡
2ኛ) የኦሮሞ ህዝብ፡ እነ ባሶ ሊበን፣ ማንኩሳ፣ አዴት፣ ይልማና እና ዴንሳ፣ ሜጫ የመሳሰሉ ስሞች በጎጃሞች አቃፊነት የ‹‹ኦሮሞ ህዝብ ስያሜዎችን›› የያዙ ቦታዎች ናቸው፡፡ አስገራሚው ነገር ደግሞ አዊ ዞን ውስጥ ከአገው ማህበረሰብ ጋር አብረው ተዋልደው በጋራ የሚኖሩ ፣ ዘራቸውን ከወዲያ የሚጠቅሱ ነገር ግን አገው ሆነው የሚኖሩ የኦሮሞ ማህበረሰቦች መኖራቸው ነው፡፡
#ማጠቃለያ
ስለዚህ የአገው ምድር ህዝብ ቋንቋን መሰረት አድርጌ ክልል መሆን እፈልጋለሁ ቢል አይችልም፡፡ ለምን?
1ኛ) ‹‹አገው ነኝ›› ብሎ የሚያስበው እና ቋንቋውን አቀላጥፎ የሚናገረው ሰው፣ ከመጀመሪያዎቹ ሰዎች ጋር የተቀላቀለ እና የተዋለደ ስለሆነ
2ኛ) መሰረቱ ‹‹ቋንቋ›› ቢሆን እንኳን ከግማሽ በላዩ አፉን የሚፈታው በአማርኛ ስለሆነ እና ዘሬ ከአገው ቅልቅል ነው የሚል፣ ነገር ግን ቋንቋውን የማይችል ብዙ ሰው ስላለ
3ኛ) የአገው ምድር ህዝብ የሚኖርባት ምድር የራሱ ብቻ ስላልሆነች
ከላይ ያነሳሁት ትንተና የቅማንትን እና የዋግ-ህምራን ጉዳይ እንደማይጨምር ቀድሜ ጠቅሻለሁ፡፡ ስለዚህ ማህበረሰብ ብዙ እውቀት ስሌለኝ የማላውቀውን መቀባጠር አልፈልግም፡፡ ነገር ግን የቅማንት ጉዳይ ከላይ ካነሳሁት ሀቅ የተለዬ ይሆናል የሚል ግምት ባይኖረኝም፣ የዋግ ህምራ ጉዳይ ግን ትንሽ ትንሽ ይሸታል፡፡ ዋግም ቢሆን ግን ከወሎ ህዝብ ጋር ያለውን ቁርኝት ትንሽም ቢሆን በነበረኝ ጉብኝት ተረድቻለሁ፡፡
#መፍትሔው፡
የ‹‹አገው ምድር ህዝብ›› በራሱ ክልል ለመሆን የሚያበቃው ወይም ‹‹ከሌሎች ጋር ተደምሮ ክልል ለመሆን የሚያስችለው›› መስፈርት የለም፡፡ አገውን ከጎጃም አማራ፣ ኦሮሞ እና ጉሙዝ ለመለዬት ‹‹በጣም የመጠቁ የዲኤኔ (DNA) ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ››፡፡ የሚሻለው ‹‹እኔ አገው ነኝ››፣ ‹‹እኔ ጎጃሜ ነኝ››፡፡ ከፍ ካለ ደግሞ ‹‹ እኔ አማራ ነኝ፣ ‹‹እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ›› ብሎ በጋራ መኖሩ ነው፡፡
ስለዚህ ‹‹ጊዜ ያለፈበትን የቁማር ካርታ እየመዘዛችሁ፣ ተፋቅሮና ተዋልዶ በጋራ ተከባብሮ በሚኖረው ማህበረሰብ ላይ ለግል ጥቅማችሁ ብላችሁ ሌት ከቀን ሴራ የምትጎነጉኑ ሰዎች እጃችሁን ሰብስቡ››፡፡ ለአዊ ዞን (አገው ምድር) ህዝብ ካሰባችሁ፣ ት/ቤት ስሩ፡፡ ጤና ጣቢያ ስሩ፡፡ ገበሬዎችን ምርታማ እንዲሆኑ በእውቀት አግዙ፡፡ ባህሉ እንዲያድግ ‹‹የባህል ማዕከል ስሩ››፡፡ ያኔ እኔም፣ መሰል ጓዶቼም የአቅማችንን እንፍጨረጨራለን፡፡ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲም የእራሱን የቤት ስራ ወስዶ ጥናት ማጥናት ያለበት ይመስለኛል፡፡
አመሰግናለሁ!
ዘላለም ጥላሁን
ደነዝ በ1997 ዓ.ም በድርቅ ምክንያት ከዋግ ህምራ ብዙ አባዎራዎች ከእነቤተሰቦቻቸው አዊ ዞን ውስጥ መጠው ከመስፈራቸው በፊት how?
ReplyDelete