Monday, September 10, 2018

‹‹በደሃ እናቶች እምባና በወጣቶች ደም-የስልጣን ቁማር መጫወት ይብቃ!››

(የአዲስ ዓመት መልዕክት)
 
የፕ/ ብርሃኑ እናት ልጃቸውን ቦሌ ተቀብለው ለመሳም ታደሉ፣ የሌሎችም እንዲሁ፡፡ ያም ሆኖ ግን ስስታቸውን ምስሉ ይገልፀዋል፡፡ እናት ምንም ቢሆን እናት ናት፡፡ ለሴኮንድም የልጇን መከራ መስማት አትፈልግም፡፡ ከጀርባ ግን ታላቅ የእምባ ጎርፍ ይታየኛል፡፡ ልጆቻቸውን በአደባባይ በአገዛዙ በግፍ የተነጠቁ እናቶች፣ መሰል ምስሎችን ሲያዩ የሚያነቡት እምባ!  ከአንጀት ተንሰቅስቆ የሚወርድ ትኩስ አምባ! በበቃሽ የማይቆም እምባ!



ሰላባ የሆኑ ወጣቶች ደግሞ በአብዛኛው ዝቅተኛ የሆነ የኑሮ ደረጃ ካለው ቤተሰብ ውስጥ የወጡ፣ ከፍ ሲልም የቀን ስራ ሰርተው ወላጆቻቸውን የሚጦሩ ናቸው፡፡ ወላጆች በሁለት ነገር ያነባሉ! የመጀመሪያው ልጆቻቸውን በግፍ በማጣታቸው፣ ሁለተኛ- ጧሪ ቀባሪ በማጣታቸው፡፡
እዚህ ላይ በጣም የምወደውን  አባባል ልጠቀም ‹‹ The Poor people are always Victims of History” ይላል፡፡ ‹‹ድሆች ሁልጊዜም ቢሆን የታሪክ ሰለባዎች ናቸው›› እንደማለት ነው፡፡ ከ 1960ዎች ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የርዕዮተ ዓለም ትግል እነማን ዋጋ እንደከፈሉ፣ በኋላ ወደ ድል ሲደረስ ደግሞ እነማን ወደ ስልጣን እንደወጡ ስናየው፣ ስንሰማው፣ ስናነበው የኖርነው ሃቅ ነው፡፡ ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት የኢትዮጵያ መንበረ መንግስት የቆመው፣ በእልፍ ወጣቶች ደምና እጥንት፣ እንዲሁም በእናቶች የእምባ መሰረትነት ነው፡፡ የእነዚህ ሁሉ የታሪክ ሰለባ ወጣቶች ዶሴ ቢጎረጎር፣ አብዛኞች ከደሃው ጓዳ ወጠው የደሃውን ህይወት ለማሻሻል ሲታገሉ የተሰው ናቸው፡፡
ጳጉሜ ሊሽረው ሰዓታት የቀሩት የትናንቱን ታሪክ እንኳን ስናይ ከላይ ያነሳሁት ሃቅ ጎልቶ ይወጣል፡፡ ከወላጆቻቸው ተነጥለው በረሃ ለበረሃ ለትግል ሲንከራተቱ የነበሩ ብዙ ወጣቶች አሸልበዋል፡፡ አንዳንዶች አሁንም በእስር ሰቆቃ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ገለልተኛ ባልሆነው የመከላከያ ሰራዊት እና የፖሊስ መዋቅር ውስጥ ያሉ የድሃ ልጆች ስርዓቱ ባደረገባቸው ጫና መሰረት በወገናቸው ላይ ሲተኩሱ በምላሹ ሰለባ ሁነዋል፡፡ የበረሃ እሳት የለበለባቸው ታጋዮች በጋሪ እየተገፉ ወደ ሀገራቸው ገብተው ወደ ደሃው ማህበረሰብ ተቀላቅለዋል፡፡  አታጋዮች እና አፈ ቀላጤዎች በአውሮፕላን ገብተዋል፡፡ ቀኝ ዮፍታሔ ንጉሴ የባንዳዎችን የስልጣን ስስት አይቶ፡
‹‹የጌሾ ወቀጣው፣ ማንም ሰው አልመጣ
የመጠጡ ጊዜ፣ ከየጎሬው ወጣ››……..እንዳለው አይነት መሆኑ ነው፡፡
በግፍ የታሰሩት እንደታሰሩ፣ የተገደሉት የወላጆቻቸውን ልብ እንደሰበሩ፣ አዲስ ዓመት መጣ! በመጨረሻም ታማኝ በየነ አንድ ታላቅ ነገር ተናግሮ ነበር…..‹‹ የምንራመድበት መሬት ሁሉ ደም ብቻ ነው›› ብሏል፡፡ ‹‹አብዛኛው ደም ደግሞ የደሃ ልጆች ደም ነው›› የሚል ቢጨምርበት መልካም ነበር፡፡
ይህን ያነሳሁት ወደ ማንም ጣቴን ለመቀሰር አይደለም፡፡ ሁሉም ባመነበት መንገድ ተጉዟል፡፡ ነገር ግን ወደ ነገ መሻገሪያውን በጥንቃቄ ማስተዋልና ማሰናሰል ያስፈለጋል ባይ ነኝ፡፡ እንደ በግ ወደ ነዱን መነዳት፣ እስካሁን ብዙዎችን አክስሮ፣ ትንሾችን አትራፊ አድርጓል፡፡
በአዲሱ ዘመን መባቻ፣ ከታቻለም የበዓል ቀን ልጆቻቸውን ያጡ ወላጅ ጎረቤቶቻችንን በመጠየቅ፣ በመደገፍ ብናሳልፍ መልካም ነው፡፡ መንግስትም ዘላቂ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ የመጨረሻው የአዲስ ዓመት መልክቴ፡
‹‹ በደሃ እናቶች እምባ እና ደሃው የኢትዮጵያ ህዝብ መከራ አይቶ ባሳደጋቸው ወጣቶች ደም የስልጣን ቁማር መጫወት ይብቃ!››  እላለሁ፡፡
ሃሳብ እንጂ፣ ነፍጥና ዱላ የማያሸንፍበት ዘመን እንዲሆን ከልብ እመኛለሁ!
መልካም አዲስ ዓመት!





No comments:

Post a Comment