እንደምንድን አላችሁ፡፡ አለበለዚያስ እንዴት ናችሁ፡፡
ሰሞኑን ነገሩ ሁሉ የጅብ እርሻ ሲሆንብኝ ከራሴ ጋር ለአንድ ሳምንት ሱባኤ ገባሁ፡፡ ከፌስቡክ ጡሉላትም ጦምሁ፡፡ ሱባኤ ገብቼ አንድ
ሀሳብ ይጄ መጣሁ፡፡ ‹‹አንድ ጉዳይ-በአንድ ፀሐይ›› የሚል! የሀገሬ ባለሃገር ‹‹ይችንማ በአንድ ፀሐይ እጨርሳታለሁ፣ ቢያቅተኝ
እንኳን እስከ ፀሐይ ግባት አፈፅማታለሁ›› ከሚለው የተወሰደ ነው፡፡ ነገሮቹን በየደቂቃው መስቀል ማውረዱ፣ መለጠፍ ማጋራቱ ብዙ
የሚያስቀጥለን አልመሰለኝም፡፡ የእስክንድርን ቃል ልዋስና ‹‹መከራችን ገና አላለቀም››፡፡ ላላለቀ መከራ ደግሞ ጅብ ተከትሎ
መጮህ ብቻ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ነገ ላለመጮህ ሰከን ብሎ በነገሮች ላይ አድምቶ መወያየት፣ መረጃ መለዋወጥ፣ ነገን ማደራጀት፣
አዳዲስ ሃሳቦች ማፍለቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በኋላ ሀሳቤን ከሚጋሩ የተወሰኑ የፌስቡክ ወንድምና አህቶቼ ጋር በሰከነ መልክ በአንድ
ቀን አንድ ጉዳይ ላይ የሰከነ ውይይት አደርጋለሁ፡፡ ያለኝን አካፍላለሁ፡፡ ከብዙዎች ብዙ እማራለሁ፡፡ መረጃዎችን አሰባስባለሁ፡፡
በጨዋ ወግ እንድንወያይ አለምናለሁ፡
ዛሬ ያነሳሁት ርዕሰ ጉዳይ ‹‹ ከመጋቢት-እስከ-መጋቢት›› እንዲሉ የዶ/ር አብይ የአንድ
አመት የስልጣን ጊዜ ላይ እንወያያለን፡፡
‹‹ዶ/ር አብይ አህመድ-ቲሸርት አልባው መሪ›› በሚል
ርዕስ መነሻነት የሆነ ነገር ልበል፡፡ አይዟችሁ የዶ/ር አብይን ውስጥ እንጂ አለባበስ ለማየት አልሞክርም፡፡ በወንጌል ‹‹ እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል…›› የሚለውን
ቃል ስለማውቅ እራሴን ለሸንጎ ዱላና ገጀራ ላለመጋበዝ ሰውን በአለባበሱ አልተችም፡፡
ከዓመታት በፊት ‹‹በህዝብ አመራር-Public Leadership›› ዙሪያ አንድ
ኮርስ ለሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች እንዲያስተምርልን ከአሜሪካ ያስመጣነው ተጋባዥ ፕሮፌሰር በትምህርቱ መሃል አንድ የ3 ደቂቃ ቪዲዮ
ለተማሪዎች ለቀቀላቸው፡፡ ርዕሱ ‹‹Leadership Lessons from Dancing Shirtless Guy›› ይሰኛል፡፡ ዩቲዩብ
ላይ ታገኙታላችሁ፡፡ ዶ/ር አብይ ለምን ያህል ጊዜ እንዳዬው ባላውቅም እንዳዬው ግን እርግጠኛ ነኝ፡፡
ስለ ቪዲዮው ትንሽ ልበላችሁ፡
ቪዲዮው ሲጀምር ብዙ ህዝብ የተሰበሰበበት አንድ አረንጓዴ መናፈሻ ያሳያል፡፡ በመሃል አንድ
ከወገብ በላይ እርቃኑን የሆነ ወጣት ሙዚቃ ከፍቶ መደነስ ጀመረ፡፡ ለተወሰነ ሰዓት ሰው በትዝብት ተመለከተው፡፡ ብቻውን ደነሰ፡፡
ወዲያው ግን የመጀመሪያውን ተከታይ አፈራ፡፡ አሁንም ሁለቱን በትዝብት ተመለከቷቸው፡፡ የመጀመሪያውን ተከታይ አይቶ አንድ ተከታይ
መጣ፡፡ ከዚያ በኋላ ሌላ ሶስት ተከታዮች ወደ ዳንሱ ተቀላቀሉ፡፡ ቀጥሎ ብዙ ሰዎች ወደ ዳንሱ ገቡ፡፡ በዚህ መልኩ እየቀጠለ ብዙ
ሰዎች ወደ ዳንሱ ተቀላቀሉ፡፡ ትንሽ ሰዎች ቀሩ፡፡ ትዝብት ውስጥ ላለመግባት እነሱም ወደ ዳንሱ ተቀላቀሉ፡፡ በመጨረሻም በመናፈሻው
ያለው ሰው ሁሉ ወደ ዳንሱ ተቀላቀል፡፡ ደርክ ሲቨር ይሄን ሲተነትን ‹‹አንድ ተከታይ ሳይኖርህ ይሄን ሁሉ ሰው ማፍራት አትችልም፡፡
ትልቁ የመሪነት አቅም ያለው የመጀመሪያውን ተከታይህን ወደ መስመር ማስገባት ላይ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው አንተን ሳይሆን ተከታዮችህን
አይቶ ይመጣል፡፡ ትልቅ የህዝብ ንቅናቄ መፍጠር የምትችለው ሌሎች መከተል የሚፈልጉትን ነገር በድፍረት ቆመህ መከተል ስትችልና ለሌሎች
ማመላከት ስትችል ነው›› ይላል፡፡
አሁን ወደ ዶ/ር አብይ እንመለስ፡፡ ዶ/ር አብይ ‹‹ኢትዮጵያን መጥራት ውርደት፣ ስለ አንድነት
ማውራት ኋላቀርነት ሆኖ በሚቆጠርበት ዘመን›› ብቅ አሉ፡፡ ከተናቁት ፈሪሳውያን ጎን በሃሳባቸው ቆሙ፡፡ የእድሜ ልክ ካቴና ካጠለቁ
እና እግር-ከወርች ከታሰሩ ሰዎች ጋር በአንድነት የምሴተ ሐሙስ ህብስት ተጋሩ፡፡ ባልተለመደና ባልታሰበ መልኩ ‹‹ኢትዮጵያ››ን
ደጋግመው በመጥራት መጋቢት 24፣ 2010 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አዳራሽ የትናንት ቲሸርታቸውን አውልቀው ራቁታቸውን ቆሙ፡፡
‹‹ኢትዮጵያ››ን በድፍረት ደጋግመው ጠሩ፡፡ በፍርሃትና በይሉኝታ
ቆፈን ፅኑ እንቅልፍ ላይ የነበሩት የህዝብ እንደራሴዎች ስሜታቸውን መቆጠብ አልቻሉም፡፡ አንድ ሁለት እያሉ ማጨብጨብ ጀመሩ፡፡ ሳያስቡት
የጭብጨባ ደቦ ውስጥ ገቡ፡፡ የለበሱትን የርዕዮተ-ዓለም ቲሸርት አውልቀው በአዲስ እሳቤ መደነስ ጀመሩ፡፡
ቀኑ ቀን እየወለደ ሲሄድ ሂደቱ ‹‹ለውጥ›› በሚል ቅኔያዊ ቃል መጥራት ተጀመረ፡፡ ቀመሩም
‹‹መደመር›› በሚል የቀላል ከባድ በሆነ የሂሳብ ስሌት ተሰየመ፡፡ ህዝብ ‹‹የለውጡ ደጋፊ›› እና ‹‹የለውጡ ነቃፊ›› በሚል መስፈሪያው
በማይታወቅ ሚዛን ተከፈለ፡፡ ህዝብ በራሱ ሜትር እየለካ እየቆረጠ፣ ያሻውን ሲደግፍ ያሻውን ሲነቅፍ ወራት ነጎዱ፡፡ ሰኔ 16፣
2010 ዓ.ም ዶ/ር አብይ በመስቀል አደባባይ አሮጌውን ቲሸርት አውልቀው ለዳንስ ወደ አደባባይ ወጡ፡፡ ሚሊዮኖች አንድ ሁለት እያሉ
ዳንሱን ተቀላቀሉ፡፡ የሆነው ሆነ (ስለ ሰኔ 16 ዘርዘር ባለ ሁኔታ ሌላ ጊዜ ካሉኝ መረጃዎች ጋር ልመለስ)፡፡ የሆነው ሆኖ ዳንሱን
የጎሪጥ ያዩት የነበሩት በይሉኝታ ተቀላቀሉ፡፡ ኢትዮጵያ ደነሰች፡፡ ከዳንሱ ሰከን ስንል፣ ሙዚቃው ዙሩን ጨርሶ ችንጋ ነከሰ፡፡ ብዙ
ነገሮች መነሳት ጀመሩ፡፡ ብዙ ጥያቄዎች መወለድ ጀመሩ፡፡ ሙዚቃውን ትቶ ህዝብ የመሪውን ዳንስና የተከታዮቹን ዳንስ ማሄስ ጀመረ፡፡
‹‹ዶ/ር አብይ ቲሸርቱን አውልቆ ነበር የደነሰው››
አንዱ ይጠይቃል፡፡
‹‹ በፍፁም እሱ አላወለቀም ህዝብ ነው
አውልቆ የደነሰው›› ሌላው ይመልሳል፡፡
‹‹ለምን ነበር ይሄ ሁሉ ህዝብ የዶ/ር
አብይን ዳንስ የተቀላቀለው›› አንዱ ይጠይቃል፡፡
‹‹ አንዳንዱ በስሜት፣ አንዳንዱ በስሌት››
ሌላው ይመልሳል፡፡
‹‹ለውጡ ምንድን ነው…ይታያል…አይታይም››
አንዱ ይጠይቃል
‹‹ እንደ አቋቋምህ እና እንደ ዓይንህ
ቀለም ይወሰናል›› ሌላው ይመልሳል፡፡
‹‹ እኔ ምልህ ለውጡ የዲሞክራሲ ነው የዲሞግራፊ››
ሌላው ይጠይቃል
‹‹ ሁለቱም የህዝብ እስከሆነ ድረስ ምን
ችግር አለው›› ብሎ መላሹ ያላግጣል
‹‹የየትኛው ህዝብ›› የሚል ጥያቄ ጠያቂው
ይወልዳል
‹‹ይህ ጥያቄ ከተነሳ፣ መልሱ አዙሪት ነው፡፡
ለውጡም መልሱም ጥያቄው ውስጥ ተውጧል›› ብሎ በውስጠ-ዘ ይመልስለታል፡፡
በእንደዚህ አይነት ጥያቄዎች እና ንትርኮች
ሰው ጎራ ለይቶ ሲነታረክ፤ እልፍ አእላፍት ነፍሳት ደግሞ ‹‹ያልተለወጠው ለውጥ›› ሰለባ ሆነው ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው ጋሽ ጥላሁን
በህይወት እያለ ‹‹ዋይ ዋይ ሲሉ፣ የረሃብን ጉንፋን ሲስሉ›› ብሎ ያዜመውን ዜማ ሜዳ ላይ ወድቀው ህልው ሲያርጉት በማህበራዊ ሚዲያ
ስንቃርም ሰነባብተናል፡፡ ‹‹በሸንጎ ቢረታ፣ ሚስቱን ገብቶ መታ›› እንዲሉ አበው መቀሌ የመሸጉ ወንጀለኞችን ለመያዝ እጁን የሰበሰበው
‹‹ለውጥ›› እስክርቢቶ የጨበጡ ባለ ስስ ነፍሶች ላይ በልደት በዓሉ ዋዜማ የጦርነት ነጋሪት ሲጎስም ደጋግመን ሰምተናል፡፡ ከመጋቢት
እስከ መጋቢት እንዲህ እየሆነ በተስፋና በስጋት ዛሬ ደርሷል፡፡ ከመጋቢት እስከ መጪ መጋቢቶች ያለውን ክስተት ባናውቅም፡፡
‹‹የእውነት ቲሸርት አልባው መሪ ለውጥ
አምጥቷል፣ አላመጣም›› ብዬ የጅል ጥያቄ አልጠይቅም፡፡ ለመወያያ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ላንሳ፡
1) ቲሸርት አልባው መሪ ዳንሱን የጀመረው አምኖበት
ወይስ ሂሳብ ሰርቶበት? እንዴት ነው የምናውቀው?
2) ቲሸርት አልባውን መሪ ተከትለው ወደ ሜዳው
የገቡት አሁን የት ናቸው?
3) ወደ ዳንሱ ሲገቡ ሙዚቃው፣ ዳንሱ ወይስ
ደናሹ የሳባቸው? ከዳንሱ በኋላ ስለሚመጣው ነገር ያውቁ ነበር?
4) ሁሌ ሙዚቃ ለከፈተው ሁሉ በስሌት ሳይሆን
በስሜት ዳንሱን መቀላቀል የት ያደርሰን ይሆን?
ዘላለም ጥ
ሻሎም!
No comments:
Post a Comment