ከሰኔ 15 ማግስት ጄኔራል አሳምነውን በተመለከተ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በፍትህ መፅሔት አንድ ሐተታ ፅፎ ነበር።ቃል በቃል ባይሆንም እንዲህ ይላል ተመስገን " ዝዋይ ማረሚያ ቤት ጄ/አሳምነው ጋር አብረን አንድ ክፍል ነበርን። እኛ ካርታ ጨዋታ እናበዛ ነበር። እኔ ሌሊት ተነስቼ ሁሉ እንጫወት ብዬ እቀሰቅስ ነበር። ጄ.አሳምነው ግን ፕሮግራም አውጥቶ ሌሎችን መፅሐፍ ቅዱስ ያስጠና ነበር። በጣም ይፆም ነበር። ለእኔ አሳምነው ይህንን ድርጊት ያደርጋል ብዬ ለማመን ይከብደኛል" በማለት የራሱን ብያኔ ያስቀምጣል።
ቀጥሎም አሳምነው ከአብይ ጋር ስለ ነበረው ግንኙነት እንዲህ ሲል ያትታል። ጄኔራል አሳምነው እስር ቤት እያለን ስለ አብይ አውርቶኝ ነበር። ቃል በቃል ያለውንም እንዲህ ሲል ያስቀምጣል
የተመስገንን ሀሳብ ይዘን የአብይን ሰሞነኛ ንግግር እንዬው። "አሳምነውን እኔ ወደ ስልጣን በመጣሁ በሳምንት ጊዜ ውስጥ አስፈታሁት" የሚለው ንግግር ነጭ ውሸት መሆኑ የገበያ ሐቅ ሁኗል። ምክንያቱም አብይ ወደ ስልጣን ሲመጣ ጄኔራሉ ከተፈታ ወር አልፎት ነበርና። ብዙ ሐተታ አያስፈልገውም። የFake News ህግ የፀደቀ ይመስለኛል። ህግ ተርጓሚ ቢኖር?
ከዚህ ይልቅ ትኩረቴን የሳበኝ ንግግር እንዲህ የሚለው ነው:
"በጄ. አሳምነው ምክንያት ልጆቼ ለስደት ተዳርገዋል።እሱን ለማስፈታት ጥረት አድርጌ ነበር። ቤቱን ሁሉ ጥረት አድርጌ አስመልሸለታለሁ። ይህን የእናት ልጅ አያደርግም" ካለ በኋላ "ከተፈታ በኋላ በፍፁም አግኝቼው አላውቅም" ይላል።
እዚህ ላይ እንጠይቅ
1)የእናት ልጅ የማያደርገውን ውለታ የዋሉለትን ሰው ሲፈልጉ ጠርተው፣ሲያሻቸው ያለበት ሄደው ለምን አላገኙትም?
2)በክፉ ዘመን ይህንን ሁሉ ያደረጉለትን ሰው እንዴት በደጉ ዘመን ማግኘት ፈሩ?
የሆነው ሆኖ ግን ከጄኔራሉ ጋር ደሴ ተገናኝተው ነበር የሚለውን ማስታወሱም አይከፋም። የአዲስ አበባውን እንተወው።
ዶ/ር አብይ ከተመስገን ጋር አንድ የሚያደርገው አንድ ሀሳብ አንስቷል:
"አሳምነው ሰው ይገድላል ብዬ አስቤ አላውቅም" በማለት ተመስገን ስለ አሳምነው ያነሳውን የሰብዓና ልኬት በተመሳሳይ አገላለፅ መስክሯል።
ይህን የምፅፈው ማንንም ነፃ ለማድረግ ወይም በሟች ወገኖች ቁስል ላይ እንጨት ለመስደድ ሳይሆን የሁለቱን ሰዎች #የእውነት_ጥግ ለመፈተን ነው። እንጂማ እኔም ዘንድ ቁስሉ አለ።
አሁን ማንን እንመን❓
ውሸታሙ ዓብይ ወይስ ተመስገን❓
ፍርዱ የህዝብ ነው። የፈለግሁትን አምናለሁ። የፈለጋችሁትን እመኑ።
እውነትና ንጋት እያደር መገለጡ አይቀርም። እስከዚያው ግን በወንዝና በተራራ እየተከፋፈሉ መባላቱ በተቀደደው ቦይ መፍሰስ ነው። በተለይ የአማራው ህዝብ አሁንም ከዚህ አጀንዳ መውጣት አለበት። ብርቅዬ ልጆች በግራም ነፈሰ በቀኝ አንዴ ላይመለሱ ሄደዋል። የአምባቸው ፈገግታ ሁሌም ከፊቴ አይጠፋም። በፈገግታ ያቀፉኝ እጆቹ ጫንቃዬ ላይ አሻራቸው ያለ ያህል ይሰማኛል።
"ጭር ሲል አልወድም" በሚል ይመስላል ተዳፍኖ የቀረውን እሳት ወይ አንዴ ገልጠው ለህዝብ አያሳውቁ አልፎ አልፎ እየጫሩ ለህዝብ አጀንዳ ይሰጣሉ። ህዝብ በጎራ እየተከፋፈለ እሳት ይጫጫራል። ነገውን በትናንት እየተነታረከ፣ ነገውን ትናንት ሲያደርግ ሌሎች ነጋቸውን ወደዛሬ አምጥተው እየሰሩ ነው። ከሰማችሁ ስሙ። ትናንት ትናንት ነው። ከትናንት ተምሮ ለነገ መዘጋጀት ጥበበኛነት ብቻ ሳይሆን ጀግንነት ነው። እንደ ሰፈር አሮጊት ባለፈ ነገር መነታርክ ለሌላ የቀውስ እዙሪት ዋዜማ ነው። ልብ ግዙ።
ጊዜ ለኩሉ‼️
No comments:
Post a Comment