Saturday, September 26, 2015

“ጴጥሮስ ያችን ሰዓት”

(ዛሬም ጀብራሬዎች በሐውልቱ እየሸኙ ነው)
ታላቁ ባለቅኔና ተውኔት አዘጋጅ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ዘመን ተሻጋሪ የሆነችውን “ጴጥሮስ ያችን ሰዓት” የምትለዋን ግጥም የፃፈው፡ አንድ ቀን ምሽት ከማዘጋጃ ቤት ሲወጣ ባየው ትዕይንት ምክንያት ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡ ፀጋዬ ገ/መድህን ከማዘጋጃ ቤት እንደወጣ ቁልቁል ወደ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ሲያመራ አንድ ጀብራሬ (በሎሬቱ አነጋገር) ከአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ላይ ሸንቱን ሲሸና ተመለከተ፡፡ ፀጋዬም በደም ፍላት ወደ ጀብራሬው ተንደረደረ፡፡ ጀብራሬው ግን “አንተ ድንጋይ እሸናብሃለሁ፡፡ ድንጋይ ነህ …. ድንጋይ ነህ ….” እያለ በሐውልቱ ላይ ይሸናል፡፡ በዚህ ሰዓት ነበር ሎሬቱ “ጴጥሮስ ድንጋይ አይደለም” ብሎ ጀብራሬውን በደም ፍላት ዘሎ ያነቀው፡፡ ከዚያም አብረውት የነበሩት ሰዎች ገላገሉትና እየተብሰከሰከ አራት ኪሎን ተሻግሮ ቀበና ገባ፡፡
ማታውን አልተኛም፡ አነሆ “ጴጥሮስ ያችን ሰዓት” የምትለዋን ግጥምና ኑዛዜ ሲጭር አደረ፡፡ አነሆ ከብዙ አመታት በኋላ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት የባቡር መስመሩን ዝርጋታ ተከትሎ ከቦታው ተነስቷል፡፡ ታዲያ ከተወሰኑ ሳምንታት በፊት የሎሬቱን ክስተት ያስታወሰኝ አንድ ነገር ተከሰተ፡፡ ምን አትሉኝም? ከጳውሎስ ወደ ፒያሳ በታክሲ እየሄድኩ ልክ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት የነበረበትን አደባባይ ስንዞር አንድ ጀብራሬ ሐውልቱ የነበረበት ቦታ ላይ ሽንቱን ያንቆረቁራል፡፡ አስቡት አስኪ ካልጠፋ ቦታ፡፡….”ካልጠፋ ገላ አይን ጥንቆላ” ማለት አዚ ላይ ነው፡፡ ወርጀ እንደ ፀጋዬ አልዠልጠው ነገር ሐውልቱ በቦታው የለም፡፡ እውነቱን ለመናገር የፀጋዬ ሞራል እኔና የኔ ትውልድ ውስጥ መኖሩንም እጠራጠራለሁ፡፡ በመስኮት ፎቶ እንኳ ሳላነሳው ታክሲው ይዞኝ ሸመጠጠ፡፡ በሌላ ጊዜ ያየሁት ለወሬም አይበቃ፤ ተውት ይቅር፡፡


አኔ ምለው፡ ይህ ቦታ አኮ እንደ ሐውልቱ እኩል ክብር ሊሰጠው ይገባል፡፡ ቢያንስ ሐውልቱ እስኪመለስ ታጥሮ መቀመጥ አለበት፡፡ እስከመቼ ነው ታሪክን በግራችን የምንረግጠው፣ እስከመቼ ነው ታሪካችንን ዳዋ የምናለብሰው፣ እስከመቼ ነው ታሪክ እየሸጥን ሆድ የምንሞላው፣ እስከመቼ ነው በታሪክ ላይ የምንሸናው?
አንድ ታሪክ ልንገራችሁ፡
በጥንት ዘመን አንድ አባት፣ ልጅና አያት አንድ ቤት ይኖሩ ነበር፡፡ አባት ሁሌም ለልጁና ለእራሱ በጥሩ ዕቃ ምግብ እያቀረበ ለአባቱ ግን በቆሸሸ እቃ ያቀርብለት ነበር፡፡ አንድ ቀን ግን ልጁ አባቱን ጠየቀ፡፡

ልጅ፡ ለምንድነው አባቴ በዚህ ቆሻሻ ዕቃ ለአባትህ ምግብ የምትሰጠው?

አባት፡ አባቴ ስላረጀ የተገኘውን ነገር በአለው ዕቃ መብላት አለበት፡፡ አባቴ ስላረጀ መብላቱን እንጂ እቃው መቆሸሹን አይመለከትም፡፡

ልጅ፡ አባቴ እንግዲያውንስ እቃውን በጥንቃቄ አኑረው፡፡

አባት፡ ለምን ልጄ?

ልጅ፡ ነገ አንተ ስታረጅ በዚሁ ዕቃ እንድሰጥህ ብዬ ነው፡፡

እነሆ ያለ ትላንት ዛሬ፣ ያለ ዛሬም ነገ የለም፡፡ ይህ ያለ የነበረና የሚኖር ነባራዊ ሐቅ ነው፡፡ ይህን ካመንን ለዛሬ ማንነታችን ዋጋ የከፈሉ ጀግኖቻችንና መታሰቢያቸውን ማክበር አለብን፡፡ እነሱን ካከበርን ነገ እኛን የሚያከብረን ትውልድ መፍጠር እንችላለን፡፡ አሊያ ከላይ ያየነው ታሪክ በእኛ ይደገማል፡፡ ታሪክ የህዝብ ነው፤ መጠበቅም ያለበትም ህዝብ ነው፡፡ ምንም እንኳ መንግስት የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ ቢኖርበትም፡፡ ክፉም ይሁን ደግ፣ ጎባጣም ይሁን ቀጥ ያለ፣ ሙሉም ይሁን ጎደሎ፣ ትንሽም ይሁን ትልቅ፤ ሁሉም የታሪካችን አካል ነው፡፡ መጥፎውን ማረም፣ መልካሙን መከተል ደግሞ የትውልዱ ድርሻ ነው፡፡
ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያ ጀግኖች!!!
   ሻሎም!!
        መልካም የመስቀል በዓል!!




1 comment: