Friday, June 29, 2018

ይድረስ ለባህርዳር የድጋፍ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ

(ጥብቅ ጥንቃቄ ስለማድረግና መፍትሄዎችን ስለመጠቆም (ምሳሌ የ 5-ለ5 አደረጃጀት)
በሩቁ ሁኖ የፍርሃት ድባብ መልቀቁ ብቻ መፍትሔ አልመሰለኝም፡፡ ሰልፉ እውን መሆኑ ካልቀረ ጥንቃቄው ላይ መነጋገር መልካም ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ከአዲስ አበባው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ያየኋቸው ክፍተቶች ባህርዳር ላይ እንዳይደገሙ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ በትህትና አመለክታለሁ፡፡

Saturday, June 16, 2018

ምን ነበር በደልህ?


(ለመ/ር እንደስራቸው አግማሴ)
ምን ቃል ተረፈና፣ በምን ልዘንልህ
የትርጓሜውን ስንክሳር፣ እልፍ ቅኔ ይዘህ ታስረህ፣
መቼ ነበር የጨለመ፣ ስንት ጥዋት ነጋ?
ስንት ክረምት ቆጠርህ፣ አለፈ ስንት በጋ?
ስንት ይሆናል እድሜህ፣ ከልጅነት እስከ አሳር?
ሳትኖር የኖርኸው ተቀንሶ፣ ያለፈው ክረምት ሳይቆጠር?
መቼ ይሆን ያንተ ጥዋት፣ መቼ ይሆን ያንተ በጋ?
ፍትህ በደጅህ ደርሶ፣ ጨለማ ቀንህ የሚነጋ?

ዶ/ር አብይ አህመድ በአለቃ ገብረሃና አምሳል


ምዕት ዓመት ተሻግረው በትውልድ ልብ የማይጠፉት ባለምጡቁ አእምሮ፣ ሊቅ፣ ፈላስፋ እና ጥበበኛው አለቃ ገብረሃና እንደ ልማዳቸው መንገድ ላይ ሲያዘግሙ በርቀት ሰዎች ተጣልተው ሲሰዳደቡ ያያሉ፡፡ በሀገሬው ልማድ ሰው ተጣልቶ እያዩ ማለፍ ነውር ነውና አለቃ ወደ እነሱ ሄዱ፡፡ አለቃ ቀረብ እያሉ ሲሄዱ ጠቡ እየበረታ ከስድብ ወደ ግልግል ደረሰ፡፡ አለቃም መሃል ገብተው ሁለቱን ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ እየገፉ ጠቡን ለማብረድ ሞከሩ፡፡ የተጣሉት አንድ በእውቀቱ አንቱ የተባለ ሊቅ እና ከእውቀት አርባ ክንድ የራቀ ሰው ነበሩ፡፡ ከእውቀት ነፃ የሆነው ሰው ሊቁን ‹‹አንተ ደደብ…አንተ ደደብ›› እያለ ይሰድበዋል፡፡ ‹‹ አለማወቅ ነፃነት ይሰጣል›› እንደሚሉት ማለት ነው፡፡ ወደ ጠቡ ቦታ አንድ ሌላ ሰው መጣ፡፡ የአለቃን ሁኔታ ተመለከተና ‹‹ አለቃ ምን እያደረጉ ነው?›› ሲል ጠየቃቸው፡፡ የቅኔ ሊቁ እና ፈሊጠኛው አለቃም ‹‹ስድብ ቦታውን ስቶብኝ …ቦታ ቦታውን እያስያዝሁ ነው›› አሉ ይባላል፡፡