(ለመ/ር እንደስራቸው አግማሴ)
ምን ቃል ተረፈና፣ በምን ልዘንልህ
የትርጓሜውን ስንክሳር፣ እልፍ ቅኔ ይዘህ ታስረህ፣
መቼ ነበር የጨለመ፣ ስንት ጥዋት ነጋ?
ስንት ክረምት ቆጠርህ፣ አለፈ ስንት በጋ?
ስንት ይሆናል እድሜህ፣ ከልጅነት እስከ አሳር?
ሳትኖር የኖርኸው ተቀንሶ፣ ያለፈው ክረምት ሳይቆጠር?
መቼ ይሆን ያንተ ጥዋት፣ መቼ ይሆን ያንተ በጋ?
ፍትህ በደጅህ ደርሶ፣ ጨለማ ቀንህ የሚነጋ?
ወዴት ይሆን መዳረሻህ፣ የኖርክበት በርባኖስ?
ከሰው እርቆ የተዘጋው፣ ማንም ደጅህ እንዳይደርስ?
ከሰማይ ስንት ወደታች፣ ከመሬት ስንት ይዘልቃል?
ከሰውነት በስንት ጫማ፣ በስንት ክንድ ይርቃል?
፤
እስኪ አንዴ ስማኝ፣ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ
ከዘመን አዙሪት አርቆ፣ ከሰው ጥላ የከለለህ
ታውቀው እንደሁ በሞቴ፣ ምን ነበረ በደልህ?
፤
ከአቡጊዳ ሽታ፣ ከቅኔው ኑባሬ
በአዋፍት ከታጀበው፣ ከያሬድ ዝማሬ
መንፈስ ከሚያድሰው፣ ከቤተስኪያን ጓዳ
ማነው የነጠለህ፣ ከህይወት ማለዳ?
፤
ግዴለም አትድከም፣ ለእኔ ለመመለስ
በአለቀ ሰውነት፣ በደከመ መንፈስ
ልጠይቅ ብዬ እንጂ፣ አውቀዋለሁ እኔ
የሀገሬን ህመም፣ የሀገሬን ጠኔ
፤
ግን አሁን ወዴት ነህ?
ወይ ኮከብ ላክልን፣ ወይ ይምራን መንፈስህ?
ወዴት ነህ አንተ ሊቅ፣ ይበቃሃል በቃ?
ግፍም ልክ ይኑረው፣ ያየኸው ሰቆቃ
አደራ መምህሩ፡
ህልማችን ካልሰራ፣ በአካል ካልተያየን
ባክህ ይቅር በለን!
ችንካሩን ባንመታም፣ የአንተ እዳ አለብን!
No comments:
Post a Comment