Saturday, June 16, 2018

ዶ/ር አብይ አህመድ በአለቃ ገብረሃና አምሳል


ምዕት ዓመት ተሻግረው በትውልድ ልብ የማይጠፉት ባለምጡቁ አእምሮ፣ ሊቅ፣ ፈላስፋ እና ጥበበኛው አለቃ ገብረሃና እንደ ልማዳቸው መንገድ ላይ ሲያዘግሙ በርቀት ሰዎች ተጣልተው ሲሰዳደቡ ያያሉ፡፡ በሀገሬው ልማድ ሰው ተጣልቶ እያዩ ማለፍ ነውር ነውና አለቃ ወደ እነሱ ሄዱ፡፡ አለቃ ቀረብ እያሉ ሲሄዱ ጠቡ እየበረታ ከስድብ ወደ ግልግል ደረሰ፡፡ አለቃም መሃል ገብተው ሁለቱን ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ እየገፉ ጠቡን ለማብረድ ሞከሩ፡፡ የተጣሉት አንድ በእውቀቱ አንቱ የተባለ ሊቅ እና ከእውቀት አርባ ክንድ የራቀ ሰው ነበሩ፡፡ ከእውቀት ነፃ የሆነው ሰው ሊቁን ‹‹አንተ ደደብ…አንተ ደደብ›› እያለ ይሰድበዋል፡፡ ‹‹ አለማወቅ ነፃነት ይሰጣል›› እንደሚሉት ማለት ነው፡፡ ወደ ጠቡ ቦታ አንድ ሌላ ሰው መጣ፡፡ የአለቃን ሁኔታ ተመለከተና ‹‹ አለቃ ምን እያደረጉ ነው?›› ሲል ጠየቃቸው፡፡ የቅኔ ሊቁ እና ፈሊጠኛው አለቃም ‹‹ስድብ ቦታውን ስቶብኝ …ቦታ ቦታውን እያስያዝሁ ነው›› አሉ ይባላል፡፡

 ኢትዮጵያ ላፉት 27 ዓመታት ሁሉም ያለቦታው የነገሰባት ምድር ሁና መቆየቷ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ፍቅር ላይ ጥላቻ፣ ማንነት ላይ ዘረኝነት፣ እውቀት ላይ አለማወቅ፣ በጎነት ላይ ክፋት፣ ብርሃን ላይ ጨለማ ቦታውን ይዞ ቆይቷል፡፡ የዚህ ሁሉ ቦታ መዛባት መሰረቱ ከእውቀት ጋር የተጣሉ ሰዎች የዘረጉት የጨበጣ አካሄድ ነው፡፡ በዚህ የመከራ አፋፍ ላይ የቆመችውን ሀገር ለመታደግ በመጥፎ ሰዓት የመጣው ዶ/ር አብይ አህመድ የአለቃ ገ/ሃና እጣ ፈንታ ገጥሞታል፡፡ ፈረንጆቹ <<The right person in the wrong time>> እንደሚሉት ዶ/ር አብይ በመጥፎ ሰዓት የመጣ መልካም ሰው ነው፡፡  ለመልካምነቱ ምስክር ህዝብ ነው (አብዛኛው ህዝብ)፡፡ እንደ አለቃ ገብረሃና ፍቅርንም፣ እውቀትንም ቦታ ቦታውን ለመስያዝ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ የዶ/ር አብይ ትልቁ ፈተና ከእውቀት ጋር የተጣሉ ድውያንን እና እብሪተኞችን ቦታ ለማስያዝ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የሚገጥመው ፈተና ነው፡፡ 

አስመስሎ እና አጭበርብሮ መኖር የለመደ ሰው እውነት ፊት ለፊት ስትመጣ አይኑ መፍጠጡ አይቀርም፡፡ ያኔ የለመደውን መንገድ ለመከተል የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም-ባልበላውም ጭሬ እበትነዋለሁ አይነት፡፡ ማንም ግን ከሀቅ በላይ አይሆንም፡፡ ሐቅ ደግሞ ከአብዛኛው የህዝብ ትርታ የሚቀዳ እውነት ነው፡፡ ብዙ ውዥንብር ባለበት የ21ኛው ክ/ዘመን እውነትን መለየት ከባድ ነው፡፡ እውነቱ ግን የህዝብ ልብ ነው፡፡ ህዝብ ምን ይላል?፣ ምን ይፈለጋል?፣ ማንኝ ይደግፋል? የሚሉት ጥቄዎች ወሳኝ ናቸው፡፡

ሊቁን ደደብ ብሎ የተሳደበው ሰው፣ ስድቡ ለራሱ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰውዬው ሊቅ እንደሆኑ የሚመሰክረው ዳኛ ህዝብ ነው፡፡  ወተትን ጥቁር ቢሉት፣ ወተት ማንነቱን አይቀይርም፡፡ የሚሳዝነው ግን ከሰል ወተትን ጥቁር ብሎ የሰደበው ጊዜ ነው፡፡ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ እንደ አለቃ ገ/ሃና፣ ከፍ ያለውን ዝቅ፣ ዝቅ ያለውን ከፍ በማድረግ በፍቅር ለማመጣጠን እየሞከሩ ነው፡፡ ነገር ግን በአንድ በኩል ሲሰፉ፣ በአንድ በኩል እየተተረተረ ነው፡፡ ሁሉን ነገር በፍቅር ማሸነፍ አይቻልም በተለይ ለፍቅር የማይነበረከኩ እብሪተኞችን፡፡ እናም እንደ አለቃ ገ/ሃና ቁጣ ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹አንዳድ የቀን ጅቦች›› የሚል ቅኔ ለበስ ፈሊጥ መናገር ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ እርምጃም ወሳኝ ይመስለኛል፡፡ አንዳዴ ‹‹ሳትገድል አስፈራርተህ ወደ ጫካው እንዲሄድ የተውከው ጅብ፣  ቀን ጠብቆ አንተን መናከሱ አይቀርም›› ፡፡ ከጫካው እንዳይወጣ ዙሪያውን ማጠር ወይም መመላለሻ መንገዱን መዝጋት መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥ ጅቡ አንተን የነከሰ ቀን፣ አሳዛኙ ክስተት ይፈጠራል፡፡   
 ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
    



No comments:

Post a Comment