የልጅነቴ ስነ-ልቦና እና አሁን ያለንበት ሁኔታ
ሁሌም ይጋጭብኛል፡፡ በልጅነቴ፣ ሰዎች ሌባን ወይም ጉልበተኛን ‹‹ኧረ በህግ አምላክ…›› ሲሉት ይቆማል፡፡ የዘረረውን በትር ወይም
መሳሪያ ወደ ሰገባው ይመልሳል፡፡ ሌባውም ‹‹ኧረ በህግ አምላክ ቁም…› ሲባል ቀጥ ብሎ ይቆማል፡፡ ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያ ህገ-ሰብዕን
ከህገ ህሊና ጋር አስተሳስራ ትኖር የነበረች ሀገር እንደሆነች ማሳያ ነው፡፡ ላለፉት ብዙ አስርት ዓመታት የሰማናቸውና ያየናቸው
‹‹አባቱ ዳኛ፣ ልጁ ቀማኛ›› አይነት ልሙጥ የሆነ የፍትህ ስርዓት ሂደት ሁላችንም ተስፋ ቆራጭ አድርጎናል፡፡ ‹‹ስልጣን እና ገንዘብ››
ኤልሻዳዮች ሁነው፤ ህግ ሲጣስ፣ ዳሃ ሲያለቅስ ማየት ብርቅ አይደለም፡፡ ፍትህ እውነትን የማስከበር ሂደት ነው፡፡ እውነት ደግሞ
በአደባባይ ተረግጣ ነበር፡፡ በፍትህ ስርዓቱ ተስፋም ሆነ እምነት ካልነበራቸው ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡ ይህን ስሜቴንም የዛሬ ሶስት ዓመት፣ ልክ በዚህ ወር ‹‹እውነትን ሰቀሏት›› በሚል አርዕስት የሚከተለውን ግጥም ከአባሪ የምስል ቅንብር ጋር በገፄ
ለጥፌ ነበር፡፡
‹‹እውነትን ሰቀሏት”
;
;
እንግዲህ ይሄ ነው
የትውልዴ ዕዳ
ገንዘብ አምላክ ሲሆን ህሊና ሲከዳ
በመንፈስ የፀና ታማኝ ለፈጣሪ
ከ'እውነት' የሚያስታርቅ ጠፋና መካሪ፤
ገንዘብ አምላክ ሲሆን ህሊና ሲከዳ
በመንፈስ የፀና ታማኝ ለፈጣሪ
ከ'እውነት' የሚያስታርቅ ጠፋና መካሪ፤
እጆቿን የኋሊት በሰንሰለት
ታስራ
ነፍጥ የያዘ ጄሌ ከቧት እያቅራራ
ከፊት እያስቆሙ ከኋላ እየገፉ
ልክ እንደ ክርስቶስ ቁልቁል እያዳፉ፤
ነፍጥ የያዘ ጄሌ ከቧት እያቅራራ
ከፊት እያስቆሙ ከኋላ እየገፉ
ልክ እንደ ክርስቶስ ቁልቁል እያዳፉ፤
በዳኞች ጉባኤ አቁመው
ፍርድቤት
በሐሰት ምስክር ጠበቃ-አልባ ሙግት
ከሳሽ ፈራጂ ሆኖ በቆመ ዝግ ችሎት
በውሸት አደባባይ እውነትን ሰቀሏት፤
በሐሰት ምስክር ጠበቃ-አልባ ሙግት
ከሳሽ ፈራጂ ሆኖ በቆመ ዝግ ችሎት
በውሸት አደባባይ እውነትን ሰቀሏት፤
(ጥቅምት 2008 ዓ.ም)
በአንድ ሀገር እንደ ሀገር የመቀጥል
ሂደት ውስጥ የፍትህ ስርዓት ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ‹‹ሐይማኖትን ከባህል፣ ህገ ሰብዕን ከህገ ህሊና›› አጣምሮ
ይዞ የቆዬ ማህበረሰብ ቢሆንም ባለፉት ዓመታት በነበረው ጎባጣ የፍትህ ስርዓት ፣ እነዚህ ወሳኝ እሴቶች መሸርሸራቸው የገበያ ሃቅ
ነው፡፡ ‹‹ሀገርን በጠራራ ፀሐይ ዘርፈው›› ….‹‹አረ እኔ አንድ ማንኪያ እንኳን አልነካሁም›› የሚሉ ሰዎች መበራከት፣ በየቤተ
እምነቶች ያለው የሙስና ጣጣ ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው፡፡
፤
ዛሬ በሙያቸው አንቱ የተባሉ ሰዎች
የፍትህ ስርዓቱን እንዲያስተካክሉ ለሲመት በቅተዋል፡፡ እኒህ ሰዎች ‹‹እውነትን ከተሰቀለችበት አውርደው›› የፍትህ ስርዓቱን ማስተካከል
ብቻ ሳይሆን ‹‹የማህበረሰቡን የሞራል እሴት የመገንባት ሂደትም›› ላይ ከባድ ስራ ይጠብቃቸዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ጉዟችን ሁሉ
‹‹ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ›› ከመሆን አይድንም፡፡ በተረፈ፣ ፍትህ የፍትህ አካላት ብቻ ሳትሆን የህዝብም ናት፡፡ ሁሉም ፍትሃዊ
የሆነች ሀገር ለመገንባት ድርሻ ያለው ይመስለኛል፡፡
ለተሾሙት፤ መልካም የስራ ዘመን
እና በጎ ህሊና!
ሀገሬንም ‹‹ፍርድ ተጓደለ፣ ደሃ
ተበደለ›› የሚል ህሊና ያለው መሪና ማህበረሰብ እንዲሰጣት….ምኞቴ ነው!
አሜን!
No comments:
Post a Comment