Friday, November 16, 2018

የአፄ ቴዎድሮስ የመጨረሻ ቃል


ባለቤታቸው / ጥሩወርቅ ልባቸው ፈራ፡፡ ንጉሱ ለእንግሊዞች እጁን ከሚሰጥ፣ እራሱን ማጥፋት እንደሚመርጥ ውስጣቸው ያውቃል፡፡ ከዚያም ወደ መቅደላ አምባ መልዕክት ላኩ፡፡ ምን ብለው? ‹‹ እባክህ በልዑል አለማየሁ ይሁንብህ፣ በራስህ ምንም እንዳታደርግ›› ብለው፡፡ የአለማየሁ ነገር እንደማይሆንላቸው ያውቃሉ፡፡ ቴዲ ግን በአለማየሁ እንኳን ጨከነ፡፡ ህልመኛው ተስፋ ቆረጠ፡፡ ዞር ሲል ሊያቆመው የሞከረውን ምሰሶ የሚገፉ፣ ግርግዳውን ለማፍረስ የሚለፉ ሰዎችን አዬ፣ አስተዋለ፡፡ ከሰው መሃል ሁኖ ብቻውን ሆነ፡፡
‹‹ተስፋ ባጣ ምድረ በዳ
ያንድ እምነት ይሆናል ዕዳ
››……እንዳለው ሎሬት ፀጋዬ /መድህን ከገብርዬ ሞት በኋላ ከቅርቡ ያለው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ሽጉጥ፡፡

‹‹ አየሽ አንቺ ኢትዮጵያ፣ አየሽ አንቺ እናት አለም
ቃል የእምነት ዕዳ ነው እንጂ፣ የእናት የአባት እኮ አይደለም
›› ይላል ጋሽ ፀጋዬ በምናብ የመጨረሻውን የንጉሱን የውስጥ እንጉርጉሮ ሲያዳምጠው፡፡
ግን ጨከነ፡፡ ለአለማየሁ ልቡ አልራራም፡፡ ለመልክተኛው ይችን የመጨረሻ ቃል በአደራነት ነገረው፡፡
‹‹
ለልጄ የማወርሰው አንዳች ነገር የለኝም፡፡ ሲያድግ ግን አባትህ አንዲት ኢትዮጵያ በዓይኑ እንደዞረችበት ሞተ ብለሽ ንገሪው›› በላት አለው፡፡ ቴዲ ከዚህ በኋላ ሌላ ነገር የተናገረ አይመስለኝም፡፡

‹‹ወዲ ዞር ሲል ሰው የለምና
ወዲያ ዞር ሲል ሰው የለምና
አረሩን ስቦ፣ ጠጣው ጀግና
›…..እንዳለው ቴዲ አፍሮ፣ በእጁ ለጨበጠው አረር ነፍሱን ሠጠ፡፡
‹‹መቅደላ አፋፉ ላይ፣ ጩኸት በረከተ
የሴቱን አናውቅም፣ ወንድ አንድ ሰው ሞተ
›› ብለው ሴቶች ስለብቸኝነቱ፣ ስለ ጀግንነቱ ሙሾ አወረዱ፡፡ አበቃ፡፡
140 ዓመታት በኋላ እንኳን እንዲህ አይነት አስተሳሰብ ያለው የህዝብ መሪ በዚች ሀገር ነጠፈ፡፡ ቴዲ የተመኛት አንዲት ኢትዮጵያ እኔነት በሰለጠነባቸው ሰዎች እጅ ወድቃ የኋሊት ሽምጥ የምታጋልብ ሀገር ሆነች፡፡ ቆዳዋ ተገፈፈ፣ ደሟ ተንጠፈጠፈ፣ አጥንቷ ተቀረጠፈ፡፡ ነጸብራቅ ታሪኳ ላይ አኬልዳማነት ጥቁር ሸማ ጋረደ፡፡ ልጆቿ የኤደን ስደተኞች ሆኑ፡፡ በዚህ ይበቃን ይሆን?
ያቆማት አይተኛምና ‹‹መለመሏን›› ቆማም ትልቅ ናት፡፡ ትልቅም ትሆናለች፡፡ ተስፋ አንቆርጥም፡፡
-----------------------///--------------------------------------------------------------

No comments:

Post a Comment