Sunday, November 4, 2018

ባቀኑት ሀገር ስደተኛ የሆኑት ሊቅ እና የአዊ ሀገረ ስብከት ውዝግብ

                              (የአቡነ ቶማስ የመጀመሪያው በትር ያረፈባቸው ሊቀ ስዩማን መዝገቡ እስከዚያ)
‹‹ አንተን ምዕመኑ ስሚያምንህ መድረክ ላይ ወጠህ ማኅበረ ቅዱሳንን እያወገዝህ ስበክ››-----ብፁዕ አቡነ ቶማስ ለሊቁ
‹‹ እርስዎ ምን አሰቡ ኤኔታ››------እኔ
‹‹ላድርገው ብል እንኳን ህሊናዬ እንዴት ይቀበለዋል፡፡ በአይኔ ያየሁትን የማኅበሩን ስራ እንዴት እክዳለሁ፣ እንዴት እዋሻለሁ››----ሊቀ ስዩማን መዝገቡ
‹‹ታዲያ በምን መልኩ መቀጠል አሰቡ››----እኔ
‹‹ እስከሚያባርሩኝ ድረስ እሰራለሁ፣ ከተባረርሁም ፍትህን ከእግዚአብሔር እጠብቃለሁ››--ሊቀ ስዩማን መዝገቡ
-----------------------------------------------------------------------------------------------------
ማን ነበር ‹‹ብሸሸው ብሸሸው አለቀቀኝም›› ያለው፡፡ በአዊ ሀገረ ስብከት፣ ከሀገረስብከት አስተዳደርና ከሃይማኖት አስተምሮ ጋር ተያይዞ ስለተነሳው ውዝግብ ከማንሳቴ በፊት፣ የነገሩን ስረ መሰረት ለመረዳትም ያግዝ ዘንድ የኤንታ መዝገቡን ጉዳይ ላስቀድም፡፡ ከላይ መግቢያ ላይ የጠቀስሁት ‹‹ቃለ ምልልስ›› ከሊቁ ጋር ያደረግነው ልክ የዛሬ ዓመት (2010 ዓ.ም) ለጥቅምት ሲኖዶስ ወደ አዲስ አበባ መጠው ከእኔ ዘንድ ባረፉበት ወቅት ነበር፡፡ የኤኔታን እና የእኔን ግንኙነት ብዙ ሰው ያውቀዋል፡፡ ከላይ ያነሳሁትም አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ወደ ጉዳዩ በጥልቀት ከመግባቴ በፊት፣ እስካሁን ስለጉዳዩ ያልጻፍሁበትን ምክንያት ልናዘዝ፡፡ ሶስት ምክንያቶች ነበሩኝ፡-

   1) ስለእነደዚህ አይነት የቤተክርስቲያን ጉዳይ መጻፍ ‹‹የራስን ገመና አደባባይ›› የማስጣት ያህል ይከብደኛል፡፡ ሁሌም ያሳዝኛል፣ አንገቴን ያስደፋኛል…..‹‹ሞኝ ባያፍር….›› አይነት ሁኖ ቤተክርሰቲያኗን ሰድቦ ለሰዳቢ መስጠት ስለሚመስለኝ፤
   2)  ስላሳቸው ብፅፍ ሰው በገለልተኛ አይን አያየውም በሚል ፍራቻ፣
  3)  ‹‹ፍትህ ለእግዚአብሔር እና ለጊዜ›› ብዬ ፍትህን ከፈጣሪ በመጠበቅ ልጽፍ አስብና ዝምታን መረጥሁ፡፡ ጉዳዩን በቅርብ ብከታተልም፣ ላለፉት 12 ወራት ለሆነው ሁሉ ዝም አልሁ፡፡

አሁን ግን ‹‹ ከድንጋይ ክምር ላይ፣ ይበቅላል ደደሆ
የፈራሁት ነገር፣ መጣ ድሆ ድሆ›› እንዲሉ………………………ብፁዕ አቡነ ቶማስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ሆነው በተሾሙበት ማግስት የነበሩት ሁኔታዎችን በማጤን ነገሩ ሁሉ ወዴት እንደሚያመራ እገነዘብ ነበር፡፡ የፈራሁት አልቀረም የአዊ ምዕመናን በስታዲዮም ተሰብስበው የእምነት አባት እስከማውገዝ ደረሱ፡፡ የዚህ ፅሁፍ አላማ አንዱን ኮንኖ ሌላውን ለማፅደቅ ሳይሆን፣ ፍትሃዊ በሆነና የቤተክርስቲያኗን ስርዓትና ቃለአዋዲ በጠበቀ መልኩ የተፈጠረው ውዝግብ እንዲሻሻል ከመሻት ነው፡፡ ደሞዛቸው ተቋርጦ የተባረሩት ሊቅ ላለፉት 10 ወራት የቤተሰባቸውን አደጋ ላይ መውደቅም ፍትሃዊና ሃይማኖታዊ መሆን ባንችል እንኳን፣ ሰብዓዊ ሁነን እንድናየው በማሰብም ነው፡፡
                                     ብፁዕ አቡነ ቶማስ ( የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ)
                                       በስታዲዮም ተሰብስቦ ሊቀጳጳሱ እንዲነሱ የጠየቀው ምዕመን 
ሊቀ ስዩማን መዝገቡ ማን ናቸው?
ለምን የአቡነ ቶማስ ቀዳሜ በትር እሳቸው ላይ አረፈ?

ሊቀ ስዩማን መዝገቡ እስከዚያ ጎጃም፣ ሜጫ ውስጥ ከሚገኘው ናዳ ማርያም ከተሰኘው ታላቅ ገዳም ቅኔ አጥንተዋል፡፡ በገዳሙ ውስጥ ካሉት ከታላቁ ሊቅና መመህር ከኤንታ ይባቤ መፅሀፍትን ተምረው በመፅሐፍት መምህርነት ተመርቀዋል፡፡ ‹‹ሊቀ ስዩማን›› የሚል ማዕረግንም አግኝተዋል፡፡ ስለ ናዳ ማርያም እና ስለ ኤንታ ይባቤ ማወቅ የምትፈልጉ ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ ‹‹እመጓ›› በተሰኘው እውነት ወለድ (ልቦለድ ማለት ስለሚከብደኝ ነው) መፅሐፍ ላይ የተጠቀመውን መቼትና ገፀባህርይ ማንበብ የተሻለ ግንዛቤ ይሰጣችኋል፡፡ ኤንታ ይባቤ እኒህን ሊቅ እንደ መንፈስና የእውቀት ልጅ ብቻ ሳይሆን እንደ ስጋ ልጅም ይቆጥሯቸዋል፡፡

ሊቁ ትምህርታቸውን እንደአጠናቀቁ ቀጥታ የመጡት ወደ አዊ ዞን፣ እንጂባራ ከተማ ነበር፡፡ የመጡት ዞኑ በዘመን አመጣሹ የእምነት አስተምህሮ ከፍተኛ አጣብቂኝ በገባበት ወቅት ነበር፡፡ ሊቀ ስዩማን መዝገቡ ረጋ ብለው ይሰብካሉ፣ አንዳንዴ ቆጣ ይላሉ፡፡ ረጋ ብለው ከብሉይ፣ ከሐዲስ፣ ከመፅሀፍተ መነኮሳት፣ ከሊቃውንት፣ ከስንክሳር እና ከአዋልድ እየጠቀሱ በማስተማር አቻ የላቸውም፡፡ አንባቢ ናቸው፡፡ ‹‹የመፅሀፍ ቀበኛ›› ናቸው ማለት ይቀላል፡፡ ከዳቦ መፅሐፍትን ያስቀድማሉ (አንድ ማሳያ በኋላ እጠቅሳለሁ)፡፡ ላመኑበት ነገር ወደኋላ አይሉም፡፡ ብዙ ጊዜ ስለቤተክርስቲያን ዶግማና ቀኖና ባላቸው ፅኑ አቋም ይታወቃሉ፡፡ ይህ አቋማቸው እስካሁን ድረስ ብዙ ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ በረከታቸው ይድረሰንና ያረፉት ብፁዕ አቡነ ቶማስ ጋር በተወሰነ መልኩ፣ ሰሞኑን ከምስራቅ ጎጃም ሀገረስብከት ከተነሱት አቡነ ማርቆስ ጋር በብዙ መልኩ እና አሁን ካሉት ከአቡነ ቶማስ ዘንድ የከፋ መገፋት ደርሶባቸዋል፡፡ ፀሎተኛ ናቸው፡፡

ኤንታ መዝገቡ ወጣቱን በስነምግባር በማነፅ፣ ጎልማሶችን በስርዓተ ቤተክርሰቲያን በማፅናት ብዙ ውለታ ውለዋል፡፡ የእኔ ማንነት ውስጥ እርሾ ከጣሉ ሰዎች አንዱ ናቸው፡፡ የ ‹‹አዊ ቄርሎስ›› ነበሩ ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ ምዕመኑ በሃይማኖቱ እንዳይናወጥ ያደረጉትን ውለታ ማንም አይክደውም፡፡ ከስብከታቸው ጎን ለጎን የመጽሃፍትና የቅኔ ተማሪዎችን በማስተማርና በማገዝ አገልግለዋል፡፡ በተጨማሪም ጥር 2010 ዓ.ም ከስራቸው እስከተባረሩበት ጊዜ ድረስ የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች መምሪያ ሃላፊ፣ የካህናት አግልግሎት ኃላፊ እና የመሳሰሉት ሃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል፡፡

ኤኔታ ከሀይማኖት አገልግሎታቸው ባለፈ የነበራቸው ማህበራዊ አስተዋፅኦም የጎላ ነበር፡፡ ሰዎች ሲጣሉ ያስታርቃሉ፡፡ የአእምሮ መቃወስ ለደረሰባቸው ሰዎች ያደርጉት የነበረው የአእምሮ ህክምና (psychotherapy) ብዙዎችን ወደቀና መንገድ እንደመለሰ ያውቁታል፡፡ የቤተክርስቲያኑን አዳራሽ ለመሰናዶ እና ለሃይስኩል ተማሪዎች ቲቶሪያል እንድናስተምርበት እንዲፈቀድ በማድረግና እኛን በማበረታታትም ትልቅ ድርሻ ነበራቸው፡፡ (በነገራችን ላይ ቲቶሪያሉ በቤተክርስቲያን ግቢ ለሁሉም እምነት ተከታዮች ይሰጥ የነበረ ነው፡፡ ኡመርን ጠይቁት)
ኤንታ መዝገቡ መጀመሪያ ወደ እንጂባራ እንደመጡ መኖር የጀመሩት ገዳማዊ ሕይወት ነበር፡፡ ስላሴ ቤተክርሰቲያን ውስጥ ያለች ትንሽ ቤት ውስጥ ብቻቸውን ይኖራሉ፡፡ ለነፍሴ ያለ ምግብ ይወስድላቸዋል፡፡ የቻለ ተማሪ ሄዶ ምግብ ያበስልላቸዋል-የሚበሰል ካለ፡፡ ካለ ይቀምሳሉ፡፡ ከሌለ እራታቸው ፀሎት ነው-ቁርሳቸውም እንዲሁ፡፡ እዚህ ላይ ከጎናቸው የነበሩ ብዙ ደግ ሰዎችን ብጠቅስ መልካም ነበር (አሁን ባለው ሁኔታ ጫና እንዳይደረግባቸው ልተወው)

ስላሳቸው ይህን ያህል በጨረፍታ ካነሳሁ፣ ከእኔ ጋር የተገናኘንበትን አጋጣሚ ላንሳ፡፡ የመሰናዶ ት/ት በምማርበት ወቅት ሁሌም ስበከታቸውን እከታተላለሁ፡፡ እሳቸውም ዘመናዊ ትምህርት እንደጀመሩና የሚያግዛቸው ሰው እንደሚፈልጉ ሰማሁ፡፡ ኤንታን ሁላችንም እንፈራቸውና እናከብራቸው ነበር ፡፡ አንድ ቀን እየፈራሁ ለመጀመሪያ ጊዜ እናገርኋቸው፡፡ በደስታ ተቀበሉኝ፡፡ ‹‹ማንዴላ›› ከተባለ ተቋም የሰባተኛ ክፍል የርቀት  ት/ት እየተማሩ ነበር፡፡ ጊዜ አልወሰድሁም፡፡ ፕሮግራም አውጥቼ ማስጠናት ጀመርሁ፡፡ ለት/ት ያላቸው ጉጉት ይገርመኝ ነበር፡፡ ሌሎች ልጆችንም መድበን እንዲያስጠኗቸው አደረግን፡፡ 10ኛ ክፍልን በዚህ መልኩ ጨረሱ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኤንታ መዝገቡ 1997 ዓ.ም አካባቢ ጀምሮ በከፋ ህመም ታመሙ፡፡ ህዝብ በነቂስ የአቅሙን አዋጦ አሳከማቸው፡፡ ለጊዜው ለውጥ ቢኖራቸውም፣ ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት አልቻሉም፡፡ ህመማቸው ከአመት አመት እየባሰ ሄደ፡፡ 2002 ዓ.ም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 4ኛ አመት ተማሪ ሁኜ እየተማርሁ ይመስለኛል ደወሉልኝ፡፡ ቀዶ ጥገና እንዲሰራላቸው መወሰናቸውን ነገሩኝ(ያማቸው የነበረው የሃሞት ጠጠር ነበር፡፡ ለረጅም ጊዜ ቀዶ ጥገና እንዲሰራላቸው አይፈልጉም ነበር)፡፡ እንዲመጡ ተስማማን፡፡ የጎንደር ግቢ ጉባኤ ፅ/ቤት እንዲያርፉ ተደረገ (በዚህ አጋጣሚ በወቅቱ የነበሩ ሰዎችን ዝቅ ብዬ ላመስግናቸው)፡፡

‹‹የቄስ እንግዳ የለውምና….››…ህክምናው እስኪሰጣቸው ድረስ ተማሪዎችን የምሽት ጉባኤ ላይ ያስተምሩ ነበር፡፡ ‹‹ ወጣት የነብር ጣት፣ አስተውል እንዳትሰሳት………አስተውል፣ እንዳትገባ ገደል›› በሚለው ቀሃ እየሱስ ያስትምሩት በነበረው ሃይለ ቃል ብዙዎች ያስታውሷቸዋል፡፡ በብዙ ሰዎች መልካም ትብብር ሆስፒታል እንዲተኙ ተደረገ፡፡ ከተኙ በኋላ ሆስፒታል ወለድ ኒሞኒያ (Hospital acquired pneumonia) ያዛቸው፡፡ ቀዶ ጥገናው ተራዘመ፡፡ ሙሉ በሙሉ ሳይድኑ ወደ ቀዶ ጥገናው ገቡ፡፡ እኛም ጭንቀት ውስጥ ገባን፡፡ ቀዶ ጥገናውን የሚሰሩላቸው ነፍሳቸውን ይማረውና እውቁ የቀዶ ጥገና ባለሙያው ዶ/ር በርናንድ አንድረሰን ( ዲ/ን ዳንኤል እንደሚለው -ጃማይካዊው ኢትዮጵያዊ ናቸው)፡፡ ረጅም ሰዓት በፈጀ ሂደት ቀዶ ጥገናው ቢያልቅም ቶሎ አልነቁም፡፡ ጉዳዩ ኒሞኒያው ካሳደረው የትንፈሳ ሂደት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ በሂደትም ወደ ሙሉ ጤናቸው ተመለሱ፡፡ ብዙዎች ተማሪዎችና ባለሙያዎች አቅፈው ደግፈው ወደ ሙሉ ጤናቸው እንዲመለሱ ቢያደርጉም፣ የዶ/ር በርናንድ እና የ ዲ/ን ደ/ር በውቀቱ አስተዋፅኦእጅግ የጎላ ነበር፡፡ እንደተለመደው የእንጂባራ ህዝብ ገንዘብ አዋጦ ለህክምና ድጋፍ እንዲሆናቸው መላኩን ማንሳት ግዴታዬ ነው፡፡ በጣም የገረመኝ ነገር ግን ከህመማቸውገና በአግባቡ ሳያገግሙ የተላከላቸውን ገንዘብ መፅሐፍትን ገዙበት፡፡ በእጃቸው የሌሉ ፣ ነገር ግን በግለሰብ እጂ ጎንደር ያገኗቸውን ጥንታዊ መፅሀፍት ኮፒ እያደረጉ መሰብሰብ ጀመሩ፡፡ ከዲ/ን ዶ/ር ሲሳይ፣ ማንዳባ መድሃኒዓለም ከሚገኘው ብቸኛ ኮፒ በእጅ የተገለበጠውን ‹‹መፅሐፈ ሐዊ››ን ኮፒ እንዳደረጉ አስታውሳለሁ፡፡ ‹‹መፅሀፈ ሐዊ›› ስለተሰኘ ገራሚ መፅሀፍ የሚያውቁ ሰዎች ምንአልባትም በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡ ሊቁን ከላይ ‹‹የመፅሐፍ ቀበኛ›› ያልሁት በምክንያት ነው፡፡

ከህመማቸው አገግመው፣ 2003 ዓ.ም በስርዓት ቤተክርሰቲያን ስርዓተ ተክሊል ፈፀሙ፡፡ ሶስት ልጆችንም አፈሩ፡፡ አድሮ ውሎ ግን በባለሙያዎች ብርቱ ጥረት የተገላገሉት ህመም መልኩን ቀይሮ የመድሃኒት ጥገኛ ሲያደርጋቸው ብዙ አልቆዬም፡፡ የስኳር በሽተኛ ሆኑ፡፡ ያም ሆኖ ግን ከአግልግሎት አላዘናጋቸውም፡፡ 2005 ዓ.ም ለመስክ ጥናት በሄድሁበት አጋጣሚ ልፋታችን ፍሬ አፍርቶ፣ የቋንቋ ዲፕሎማ ከእንጂባራ መምህራን ኮሌጅ ሲቀበሉ ደርሼ የደስታቸው/የደስታዬ ተካፋይ ሁኛለሁ፡፡ በዚህ አላቆሙም፣ በአሁኑ ሰዓት የዲግሪ ትምህርታቸውን ጎን ለጎን ይከታተላሉ፡፡
በዚህ ሁሉ ፈተና ያለፉና ህመም ሳይገታቸው ቤተክርስቲያንን እያገለገሉ ያሉ ሊቅ ለምን የአቡነ ቶማስ ቀዳሚ በትር አረፈባቸው?
ለምን በግፍ ተባረሩ?
ምክንያቱ ምንድን ነው?
(ከመረጃዎች ጋር እመለሳለሁ)
ይቀጥላል
(ማሳሰቢያ፡ ከዚህ ላይ ለማነሳቸው ሃሳቦችና መረጃዎች ሃላፊነቱን እወስዳለሁ፡፡ ተጨማሪ መረጃዎች ያሏችሁ በውስጥ መስመር ላኩልኝ)

1 comment:

  1. ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም፣ወሰኝ ሰው በወሰኝ ሰዓት የሰባዊ መብት ተሟገች አስናሳልን።

    ReplyDelete