Sunday, January 24, 2016

“ከ አሜን ባሻገር”

እውቀቱ ስዩም ትክክለኛው የጥበብ ሰይጣን ከለከፋቸው ጥቂት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱና የወቅቱ ፈርጥ ነው፡፡ ክቡር ዶ/ር ሐዲስ አለማየሁ (በዕውቀቱ እንደሚለው ‘አዲስ ህልም አየሁ’) ምን አልባት ፍቅር እስከ መቃብርን ሲፅፉ የመቼታቸው መነሻ የሆነውን ማንኩሳን ከአንዴም ሁለት ሶስቴ መጎብኘታቸው አይቀርም፡፡ በእርግጥ ማንኩሳ ከትውልድ ቦታቸው ከእንዶደም ኪ/ምህረት በእግር ጉዞ ቀናትን የሚፈጅ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን በመኪና የ ሰዓት ጉዞ በቂ ነው፡፡ ወደ መላምቴ ልምጣና፣ ክቡር ዶ/ር ሐዲስ አለማየሁ በወቅቱ ማንኩሳን ሲጎበኙ ከቤተክርስቲያኑ ጎን ቁጭ ብለው ስለ ቦጋለ መብራቱ፣ ውድነሽ በጣሙ እና ስለበዛብህ ሲያሰላስሉ ከዚያ ቦታ ወደፊት አንድ የጥበብ ሰው እንዲነሳ አምጠዋል (ወይም በዩኒቨርስ ህግ ሃይል አጋርተዋል (energy sharing)::
ወይ ደግሞ ከዚያ ቦታ አድርባይ ያልሆነ የጥበብ ሰው እንዲነሳ በይፋ አምላካቸውን በንፁህ ልቦና ለምነዋል፡፡ ይህ የተመኙት ሰው በዕውቀቱ ስዩም ነው፡፡ ይህ የእኔ መላምት ነው፡፡ እውነቱን የሚያውቁት ግን ክቡር ዶ/ር ሐዲስ አለማየሁ ብቻ ናቸው፡፡

ምንአልባትም በዕውቀቱ እንደዚህ አስቦ ሊያውቅም/ላያውቅም ይችላል፡፡ ይህን የሚያውቀው ራሱ በዕውቀቱ ነው፡፡ ይህ መላምቴ ግን በዕውቀቱ ወደኋላ ተመልሶ ስለራሱና ስለ ክቡር ዶ/ር ሐዲስ አለማየሁ እንዲመራመር በር ከፋች ነው ብዬ አልመፃደቅም፡፡ በእርግጥ ስለ ክቡር ዶ/ር ሐዲስ አለማየሁ ጥልቅ ጥናት ቢያደርግና ዝክረ ታሪካቸውን ቢፅፍልን አጀብ ማለቴ አይቀርም፡፡ ሐዲስ አለማየሁ ይፋ ያላደረጓቸው ብዙ ምስጢሮችን ይዘው የተለዩን ሰው ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡ ሚስታቸው ከአረፉ በኋላ ሌላ ሚስት አላገቡም፡፡  “የፍቅር እስከ መቃብር ታሪክ የራሳቸው ታሪክ ነው” የሚለው መላምት እስካሁን መልስ አላገኘም፡፡ ስለጉዳዩ የተጠየቁት የቅርብ ወዳጃቸው መምህር፣ ደራሲና ሐያሲ አስፋው ዳምጤ እንኳ የሰጡት ምላሽ “ጠይቄአቸው አላውቅም” የሚል ነበር፡፡

ለማንኛውም በዕውቄ በደፋር ብዕሩ “ከአሜን ባሻገር” ላይ ምን ሊያስነብበን እንደሚችል አላውቅም፡፡ ግን የሽፋን ስዕሉን በጥልቀት ስመረምረው ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ከነገ በጥልቀት የመረመረበት መጣጥፍ ሊሆን አንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ያልተፈታ ቅኔን፣ የተደበቀ ገድልን፣ ያልተሰማ እውነትን፣ ያልተቃኘ መንገድንም ይገልጣል ብየ አስባለሁ፡፡ ቀሪውን ከንባቡ በኋላ፡፡


No comments:

Post a Comment