Sunday, February 25, 2018

የጠቅላዮች ምረጡኝ ቅስቀሳ

የጠቅላዮች ምረጡኝ ቅስቀሳ (ምረጧቸው ቅስቀሳ) ተጧጡፏል፡፡ የ<ለማ>ንና የ <ዶ/ር አብይ>ን 'ሲንግል' ዘፈኖች አደመጥሁ፡፡ ዘፈኖቹ ‹‹ሃሳብ አለው ለማ›› እና ‹‹አብይ ዜማ›› ይሰኛሉ፡፡  የ<ደመቀ> እና የ <ሲራጅ> ይቀረኛል፡፡ ያደመጣችሁ ጀባ በሉኝ፡፡ ዘፈን ለመስራት ያሰባችሁ ደግሞ ግጥሙን ከአዝማሪ፥ ዜማውን ከህዝብ አጣምሩና በቶሎ በሉ፡፡ በእርግጥ ደህዴንና ህዋሃት ያየር ሰዓቱን በዝረራ ያስረከቡ ይመስላል፡፡ እንቅስቃሴው ደከም ያለ ነው፡፡

አጋር ድርጅቶች ደግሞ እስከ ብብት እንጂ ጭንቅላት ድረስ መውጣት አልተፈቀደላቸውም፡፡ ጠ/ሚንስትር መሆን የሚፈልግ ባለምጡቅ ጭንቅላት ሶማሊያዊ፥ አዳል ወይም ጋምቤላዊ መጀመሪያ የዘር ካርዱን ከትግሬ፥ ከኦሮሞ ወይም ከአማራ የደም ማህተም ማስመታት ይኖርበታል፡፡ ይች ናት እንግዲ-የብሔር እኩልነት የነገሰባት ሀገር!
ጭንቅላት ብቻውን ጭንቀት ከመፍጠር ያለፈ ዋጋ የለውም፡፡
<<የሀገሬ ዳቦና፣ የዘር ፖተሊካ
ለአንዳንዱ ባካፋ፣ ለአንዳንዱ በሹካ>> አይነት ነገር ነው፡፡ ለማንኛውም፥ ኢህአዲግዬ የመጨረሻውን ጥይት ለመተኮስ የተዘጋጀ ይመስለኛል፡፡ ዶ/ር አብይ አህመድን!
ቀሪውን፥ ቀሪው ቀን ያውቃል!!!

Thursday, February 15, 2018

Ethiopian Prime Minister Resigned

The current Ethiopian Prime minster and EPDRF Leader, Hailemariam Desalegn resigned from his position 
የኢትዮጵያ መራሒ መንግስት ክቡር ሐይለማርያም ደሳለኝ ‹‹በሰለጠነ መንገድ›› መልቀቂያ አቅርበዋል-እሳቸው እንዳሉት፡፡ የእራሳቸውንም መልቀቅ አሁን ላለው የኢትዮጵያ ሁኔታ የመፍትሄ አካል አድርገው አቅርበዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት በታሪክ ስልጣኑን በፈቃዱ የለቀቀ ሰው ተብዬ እታወሳለሁ ብለዋል፡፡ ነገር ግን ትልቁ የህዝቡ ጥያቄ ከስርዓቱ ወይስ ከሐይለማርያም? የሐይለማርያም መልቀቅ አንድ እርምጃ ወደፊት ያስኬዳል ወይ?

ነገሮች መልካቸውን እየቀየሩ ሄዱ፡፡ በዚህ ሁሉ መሃል ሀገር ታሳዝናለች፡፡ ይች ሀገር የምታሳዝነኝ ግን ‹‹መንቀል እንጂ ማብቀል›› የሚችል ማህበረሰብ መፍጠር አለመቻላችን ነው፡፡ ሁሉም ሰው ‹‹ወደ ገደል መጎተቱ ላይ እንጂ››፣ ጎን ለጎን ‹‹ወደ ተራራው የሚወጡትን›› የመግፋት ነገር ላይ ሲሰራ አይታይም፡፡  ዛሬ እየፈረሰ መሆኑን ከተረዳን ነገን መስራት ላይ ማሰብና መዘጋጀት ያስልጋል፡፡




Thursday, January 25, 2018

ቴዲ አፍሮ፣ ወልዲያ፣ ኢትዮጵያ






‹‹ኢትዮጵያ›› በሰቆቃ እንድትኖር የተፈረደባት ምድር ትመስለኛለች፡፡ ቅድመ አያቶቻችን ልጆቻቸውን በፋሽት አረር አጡ፡፡ ‹‹ጥዋ ተርታቸው እድል ፈንታቸው›› ገና የሆኑ አያቶቻችን በህይወት ተርፈው አባቶቻችንን ወልደው አሳድገው ለአብዮት እሳት ገመዱ፡፡ ከአብዮቱ የተረፉ አባቶቻችን በፈንታቸው ልጆችን ወልድው በዘረኝትነት ቋያ አቃጠሉ፡፡ የዘረኝነት ቋያ እያደረ ብዙዎችን ወደ እሳቱ ገመደ፡፡ እስከዛሬ ብዙ ህልም ጨነገፈ፡፡ ብዙ ተስፋ ነጠፈ፡፡ ብዙ የንፁሃን ነፍስ ተቀጠፈ-እዚች ባልቴት ሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ፡፡

እንዴት አንድ ሀገር ተመሳሳይ የሆነ ለቅሶ ከመቶ ዓመት በላይ ታለቅሳለች? እንዴት አንድ ሃገር ለመቶ ዓመት በተመሳሳይ በሽታ ታማ ትሞታለች? ውሎ ሲያደር ሞት ሲለመድ፣ የሰው ልጅ ደም እንደውሻ ደመ ከልብ እየሆነ ቀረ፡፡ እንዴት ሰው የራሱን ወገን ይገላል? ብዬ የሞኝ ጥያቄ አልጠይቅም ግን እንዴት ከመግደሉ በፊት ትንሽ ማሰብ ያቅተዋል?

Thursday, January 4, 2018

★አንዱ በር ሲዘጋ....★

ማዕከላዊን መዝጋት ጥሩ ጅምር ነው፡፡ ወደ ሙዚየም ሳይሆን ወደ ሆስፒታል/ትምህርት ቤት መቀየሩ ደግሞ የተሻለ ያስመሰግናል፡፡ ዓለም በቃኝ የአፍሪካ ህብረት /ቤት ሁኗል እንጂ 60 ጄራሎች የተሰውበት ቦታ ተብሎ ሙዚየም አልሆነም፡፡
መጪው ትውልድ የቂምና የበቀል ትዝታዎቹን በረሳ ቁጥር የበለጠ ለአንድነትና ለእድገት ይተባበራል፡፡ ኢትዮጵያም ወደ ቀደመ ክብሯ ትመለሳለች፡፡ ሙዚየም ሳይሆን /ቤት ይሆን፡፡ ትውልድ ይዳን፥ በእኛ ይብቃ ማለት እንልመድ፡፡ (ነገረኛ...ሙዚየሙንስ ማን አየብን የሚል አይጠፋም)፡፡ 

Sunday, December 24, 2017

አዲስ አበባ (በረራ)

እንዲህ ብሎ መጣፍ አሰኘኝ፡፡
የአዲስ አበባ ሰማይ ጎህ ሲቀድ፥ ካድሬም ቢሆን የሚያሳቅፈውን የታህሳስን ውርጭ እንደምንም ታግዬ ከምኝታዬ ታፋታሁ፡፡ፀጥ ባለው የአዲስ አበባ ሰማይ ስር፥ የሰንበት ቅዳሴ አድማሱን ተሻግሮ ከብርዱ ጋር የሚታገለውን የአማንያንን ልብ በሐሴት ይጠራል፡፡
"እምነ በሐ....ቅድስት ቤተክርስቲያን......አረፋቲሃ......"
;
ይቀጥላል፡፡
ከገደል ማሚቶው ቀጥሎ የሌላ ደብር ምስጋና የብርዱን ቆፈን እንደ ሰም ያቀልጣል፡፡ አማኒያን ነጠላቸውን መስቀለኛ አጣፍተው ውር ውር ይላሉ፡፡
አዲስ የሁላችንም ናት፡፡ የካድሬው፥ የወሬኛው፥ የሃብታሙ፥ የድሃው፥ የዘረኛው፥ የኢ-ዘረኛው፥ የለፍቶ አዳሪው፥ የአማኙ፥ የቀማኛው፥ የአሳሪው፥ የታሳሪው፥ የምሁሩ፥ የባዶ ጭንቅላቱ፥ የእግረኛው፥ የባለ ሐመሩ፥ የጦም አዳሪው፥ የሰክሮ አደሩ ከተማ ናት፡፡

Friday, December 8, 2017

የሰፊው ህዝብ ግጥሞች

አንቺን የለመዱ ብዙ ሰዎች ሳሉ
የቤቱ ሙሉ አዛዥ እንግዳ ነው አሉ
አንቺ አሽከር ነገርሽ ከኮሶ ባሰሳ
ያስቀምጠኝ ጀመር ሌሊት እያስነሳ
አዋዜው በዛና ምላሴን ተኮሰው
አነካክቶ መብላት፥ መች አውቅና እንደ ሰው
አየሁ አዝመራሽን አውሬ ሲጨርሰው
እንዲህ ሆነሽ ቀሪ፥ ይመስለዋል ለሰው
አጎንብሰሽ መሄድ አላውቅ ብዬ እንደ ሰው
እቀና ብዬ ነው ቤቴ የፈረሰው
እኔን ከፋኝ እንጂ ሀገሬን ምን ከፋው
ግራር አበቀለ ዝሆን የማይገፋው

እኔ ልኮራመት እኔ ከሰል ልምሰል
ስቀሽ አታስቂኝ የደላሽ ይመስል


ሌላ ጨምሩ እስኪ?

Monday, November 27, 2017

‹‹አንድም እናት በወሊድ ምክንያት…..››

-----------------------------------
‹‹
ሌሊት ላይ ታመመች
ምጤ መጣ ብላ፣ ሆስፒታል ውስጥ ገባች
አማጠች አማጠች
ሌሊቱ ጎህ ሳይቀድ፣ ሞት ተገላገለች፤
ሁሉም ሰው አዘነ፣ ዘመድ አለቀሰ
ሁለት ነፍስ፣ በአንድ ጉድጓድ፣ ቀብሮ ተመለሰ››
በቃ!

--------------------------------------------
ይህ ዜና በጓደኛዬ እህት ደርሶ ሐዘኑ ምን ያህል ልብ ሰባሪ መሆኑን በአይኔ ልመልከት እንጂ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ቅስም ለዘመናት ሲሰብር የኖረ ሰቆቃ ነው፡፡ የነፍሰጡር ሞት አንድ ሞት አይደለም፣ የብዙ ሞቶች ጥርቅም ነው፡፡

Tuesday, October 31, 2017

ኢትዮጵያ ማለት………

(ከታዋቂ ሰዎች አንደበት)
‹‹ኢትዮጵያዊነት እንደ እንጉዳይ በአንድ ማታ የበቀለ አይደለም››
‹‹
ኢትዮጵያ ውስጥ የመደብ እንጅ የብሔር ጭቆና ኑሮ አያውቅም››
‹‹
ኢትዮጵያ የአስተሳሰብ ቆሻሻን የማፅዳት ጦርነት የሚያስፈልጋት ሃገር ናት……››
‹‹
ኢትዮጵያዊነት ሁሉን የመሳብ አቅም ያለው ልዩ ሃይል ነው››
‹‹
ገዥው ኢህአዲግ ሁለት ምርኩዝ አለው፡ ጠብ መንጃና ምርጫ ቦርድ››

‹‹ኢትዮጵያዊነት ቢገፉት የማይወድቅ፣ ቢከፍሉት የማይሰነጠቅ፣  በፅኑ ዓለት ላይ ፀድቆ የኖረ፣ በአጥንትና በደም የተሳሰረ ህያዊነት ነው››
ኢትዮጵያ ዘላለም ትኑር!

Tuesday, October 17, 2017

ይወለዳል ገና!

 ይሄ ወጣትነት
ከሱስ ላይ ተጥደን፥ ያልፋል እንደዘበት፤
ይሄ ወጣትነት
ያልፋል እንደ ዋዛ
ለሃብታም ስናረግድ፥ ለውሸት ስንገዛ
ይሄን ወጣትነት
የኔ ቢጤ ሁሉ፥ ይሰዋል በከንቱ
አሸሸገዳሜ፥ ለሚጠፋ አምሮቱ


ጀግናው ተሜ ግን፥ የሀገሬ እንቆቆ
ስለ መራራ እውነት፥ ጣፋጭ ዓለም ንቆ

Saturday, October 7, 2017

ኧረረረረ ወገቤ……................

አንቺ ማንጠግቦሽ አተላውን ቶሎ አምጪው ባክሽ
ምን ይች ልጅ ተጨማሪ ህመም ሆነችብኝሳ!